ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በዋይት ሃውስ የጀመሩት አዲስ ግንባታ ለጊዜው እንዲቋረጥ ፍርድ ቤት ወሰነ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን በዋይት ሃውስ የጀመሩት የአዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክት ተገቢ ሂደቶችን ተከትሎ ባለመጀመሩ ለጊዜው እንዲቋረጥ አንድ አገሪቱ ፍርድ ቤት ዳኛ ወሰኑ።
ውሳኔው የተላለፈው 'ናሽናል ትረስት ፎር ሂስቶሪክ ፕሬዘርቬሽን' በተባለ የቅርስ ጠባቂ ተቋም ዋይት ሃውስ ላይ ክስ በመመስረቱ ነው።
ዳኛው ሪቻርድ ሊዮን፤ "ኮንግረሱ ለዚህ ፕሮጀክት ሕጋዊ ፈቃድ እስካልሰጠ ድረስ ግንባታው መቆም አለበት" ሲሉ ውሳኔ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ዳኛው ኮንግረሱ ግንባታውን ማጽደቅ እንዳለበት በመግለጽ የሰጡትን ውሳኔ ለመቀልበስ ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል። ትራምፕ፤ አሁን ባለው ይዞታ ቤተመንግሥቱ፤ በሚቀጥለው ወር አሜሪካን እንደሚጎበኙት ንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ ያሉ ታዋቂ ሰዎችን ለማስተናገድ በቂ እንዳልሆነ አክለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ቀደም ሲል ዕቅዱ የቤተ መንግሥቱን የምስራቅ ክንፍ ለማደስ ከሚወጣው ወጪ ያነሰ እንደሚሆን ተናግሯል። በርካታ ፕሬዚዳንቶች ቤተ መንግቱ ላይ ለውጥ ማድርጋቸውንም አክለዋል።
ማክሰኞ ዕለት በወጣው የዳኛው ባለ 35 ገጽ ውሳኔ፤ "ለፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ለመስጠት የሚያስችል ምንም ዓይነት የቀረበ ሕግ ስለማይገኝ [ክስ አቅራቢው] ናሽናል ትረስት ሊሳካለት እንደሚችል ደምድሜያለሁ" ብለዋል።
"የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ለቀጣዮቹ ፕሬዝዳንታዊ ቤተሰቦች የዋይት ሃውስ ጠባቂ እንጂ ባለቤት አይደሉም!" ሲሉም አክለዋል። ፕሮጀክቱ እንደገና እንዲጀመር ኮንግረስ ማፅደቅ እንዳለበትም ተወስኗል።
ክሱን ያቀረበው ናሽናል ትረስት፤ ዋይት ሃውስ ለብሔራዊ የካፒታል ፕላን ኮሚሽን ዕቅዶችን እንዳላስገባ እና የፕሮጀክቱን የአካባቢ ጥበቃ ግምገማ እንዳላከናወነ በመግለጽ ተከራክሯል። የትራምፕ አስተደዳር ከኮንግረስ ፈቃድ ለመጠየቅ ፈቃደኛ አልነበረም ሲሉም በፍርድ ቤት ተናግሯል።
"ኮንግረሱ የዩናይትድ ስቴትስ ሀብት የሆኑ ንብረቶችን የማስወገድ እና የመጠበቅ መብት" አለው የሚለውን ሕግም ትራምፕ ጥሰዋል ብሏል። ።
ዳኛው ሊዮን ሲያጠቃልሉ፤ ኮንግረሱ ለዋይት ሃውስ በሚሰጠው ፈቃድ አማካኝነት "የመንግሥት መዋቅሮች በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች መሠረት ሚናቸውን ስለሚወጡ የአሜሪካ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል" ብለዋል።
"ይህ ደግሞ መጥፎ ውጤት አይደለም።"
በ1902 የተገነባው የዋይት ሃውስ የምስራቅ ክንፍ ትራምፕ ላቀዱት ባለብዙ ሚሊዮን ዶላር ለሚገመት አዳራሽ ሲባል ጥቅምት ላይ ፈርሷል።
መጀመሪያ 500 ሰዎች የመያዝ አቅም እንዲኖረው የቀረበው ዕቅድ ተሻሽሎ አዳራሹ 1,350 እንግዶችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ 400 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ እና ሙሉ በሙሉ በግል ለጋሾች እንደሚደገፍ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
ናሽናል ትረስት ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጠበቅ በአሜሪካ ኮንግረስ የሚደገፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።
የቡድኑ ፕሬዝዳንት ካሮል ኩዊለን "ዳኛ ሊዮን አስተዳደሩ ሕጉን እስኪያከብር እና ወደፊት ለመቀጠል ግልጽ ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስ ተጨማሪ ግንባታ እንዲቆም በመወሰናቸው ተደስተናል" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
"አገራችን ውስጥ በጣም ተወዳጅ እና ታዋቂ የሆነን ምልክት ለዘላለም የሚነካ ፕሮጀክት ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ለአሜሪካ ሕዝብ ድል ነው።"
ትራምፕ ለዳኛው ውሳኔ ትሩዝ ሶሻል ላይ በሰጡት ምላሽ "ናሽናል ትረስት ታክስ ከፋዩ ምንም ገንዘብ ሳያስወጣ በሚገነባ እና በዓለም ላይ ምርጡ እንደሚሆን የሚጠበቀውን ሕንፃ በተመለከተ ክስ መስርቶብኛል" በማለት ጽፈዋል።
ትራምፕ በቅርቡ በራሳቸው ስም የሰየሙትን የኬኔዲ ማዕከል ዕድሳት ለማስቆም ትረስቱ ክስ መመስረቱንም ተችተዋል።
ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ስለሚገኘው የኪነጥበብ ማዕከል "እኔ የማደርገው ለብዙ ዓመታት ጥበቃ ያልተደረገለትን ማዕከል ማስተካከል፣ ማጽዳት እና 'ማደስ' ብቻ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
ዋይት ሃውስ ውሳኔውን ይግባኝ እንደሚል ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት ትራምፕ፤ ግንባታውን ለመቀጠል ከኮንግረሱ ፈቃድ ያስፈልጋል መባሉን አስተባብለዋል።
ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት በማስታወስም፤ ድንኳኑ ዝናብ ሲዘንብ ምን ያህል እርጥብ ሊሆን እንደሚችል በማስገንዘብ ለማስተናገድ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"ንጉሥ ቻርልስ በጣም ጥሩ ሰው ሲሆን በውሃ ገንዳ ውስጥ እንዲቀመጥ አንፈልግም" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በፕሮጀክቱ ላይ የሚደርስ ማንኛውም መዘግየት የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነት እንደሚጎዳ ጠቅሶ ቢከራከርም ዳኛው ግን "ውሃ የማያነሳ" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
"በእርግጥ ከዋይት ሃውስ አጠገብ 'ትልቅ ጉድጓድ' መኖሩ የፕሬዚዳንቱ የራሱ ችግር ነው!" ሲሊ ጽፈዋል።
ትራምፕ እሑድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የአሜሪካ ጦር በአዳራሹ ስር "ግዙፍ ማ"ዕከል እየገነባ ነው።
"አዳራሹ ከስር ለሚገነባው ማዕከል ሽፋን ይሆናል" ብለዋል።
የቤተ መንግስቱ ምስራቃዊው አዳራሽ ግንባታው በጥሩ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል።
የማፍረስና የመሠረተ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን ከመሬት በላይ ያለው ግንባታ በሚቀጥለው ወር ይጀመራል።