በሀብታሟ ደቡብ አፍሪካ በውሃ ጥም የሚቃጠሉት ዜጎች እና በወንጀል ቡድኖች የተያዘው የውሃ አቅርቦት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በጆሃንስበርግ ግሪንሳይድ ከተማ ዳርቻ ከሁሉም የዕድሜ ክልል የተውጣጡ የተቃውሞ ሠልፈኞች መፈክሮች የተለጠፈባቸው ባዶ የፕላስቲክ ባልዲዎችን በማወዛወዝ ተቃውሟቸውን ያሰማሉ።

"ውሃ እንፈልጋለን! ውሃ እንፈልጋለን!" እያሉ መፈክር ያሰማሉ።

አረንጓዴ በሆነችው ሰሜናዊ ጆሃንስበርግ በደቡብ አፍሪካ ለዓመታት የዘለቀ የውሃ እጥረት ከተከሰተ በኋላ ነዋሪዎች ተስፋ መቁረጣቸውን ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ከአንድ ወር በላይ የመጠጥ ውሃ አላገኙም።

"ቧንቧዎቻችን ክው ብለው ደርቀዋል፤ ውሃም ጨርሶ አይተው አያውቁም" ይላሉ ኮሊን ሬጅስኪ። "ሁሉም ሰው ያለ ንጹህ ውሃ ሊታመም ስለሚችል ይህ ጤናማ አይደለም። እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ውሃ ማግኘት መብታችን ነው።"

ሌላኛዋ ተቃዋሚ ጄኒ ጊሊስ በአካባቢው ለ40 ዓመታት ኖራለች። "ዛሬ እዚህ የተገኘሁት በጣም አሳፋሪ ስለሆነ ነው" ትላለች። "ውሃ ለመለመን እና የተቃውሞ ድምጻችንን ለማሰማት ተገድደናል።"

በአውሮፓውያኑ ከ2022 እስከ 2024 መጀመሪያ ድረስ የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችው ጆሃንስበርግ ከባድ የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟት ነበር፤ ይህም ኃይል በፈረቃ እንዲከፋፈል አስግዶ ነበር።

በቀን እስከ ስምንት ሰዓታት የሚዘልቀው የመብራት መቆራረጥ የተራ ደቡብ አፍሪካውያንን እና የንግድ ድርጅቶችን ሕይወት በእጅጉ ጎድቷል። ባለሙያዎች በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ለረጅም ጊዜ እድሳትም ሆነ ግንባታ ባለመካሄዱ የተነሳ የተፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የውሃ እጥረት የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። አንዳንድ ነዋሪዎች ንፁህ ውሃ ለጤና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ የከፋ መሆኑን ይናገራሉ።

በውሃ እትረት የምትሰቃው ጆሃንስበርግ ብቻ አይደለችም። ከከተማው በስተሰሜን ከ100 ኪ.ሜ በላይ ርቃ በምትገኘው ሃማንስክራል፣ የ35 ዓመቱ ፓስተር ሼፖ ማህላውሌ በጓሮው ውሃ ካየ ወራት ያለፈውን ቧንቧ ያሳያል።

"በሃማንስክራል እየሆነ ያለው ይህ ነው፤ ውሃ የለም። ሰዎች ውሃ ለማግኘት እየጣሩ ነው። ለሁለት ወራት ውሃ የለም። ልጆቻችን በየቀኑ መታጠብ አለባቸው፤ ዩኒፎርማቸው መታጠብ አለበት፤ እኛ ደግሞ ውሃ የለንም።"

የከተማዋ ነዋሪዎች ከአስር ዓመታት በላይ፣ አንዳንዴ ስለሚቆራረጥም ጭምር፣ አስተማማኝ የንፁህ ውሃ አቅርቦት አላገኙም።

ማዘጋጃ ቤቱ ለነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ለማድረስ ለውሃ ጫኝ መኪኖች መክፈል ጀምሯል። የአካባቢው ተቃዋሚ ዴሞክራቲክ አሊያንስ የውሃ ማፍያዎች በመባል የሚታወቁት የወንጀል ቡድኖች የውሃ ማከፋፈል ኢንዱስትሪውን በቁጥጥራቸው ስር እያዋሉ ነው ሲል ከሷል፤ ነገር ግን ይህ እየተከሰተ ስለመሆኑ ለቢቢሲ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረበም።

"የውሃ ማፊያዎች ለማዘጋጃ ቤቱ ሥራ ለመሥራት ጨረታ የሚያቀርቡ ሰዎች ናቸው" ሲሉ የደቡብ አፍሪካን የውሃ ሀብቶች ለመጠበቅ የሚሠራው የዋተርካን ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ፌሪያል አዳም ያስረዳሉ።

"ሙያዊ ብቃት የላቸውም፣ ወይም አማራጭ ውሃ ለማቅረብ ጨረታ ካሸነፉ በኋላ እስከ መጠናቀቂያው ጊዜ ድረስ አይቆዩም፤ ከዚያ ይልቅ ሥራቸው እንዲቀጥል መሠረተ ልማቶችን ይዘርፋሉ፣ ያበላሻሉ።"

"እናም ሰዎችን ማስከፈል ሳይኖርባቸው ለሚያቀርቡት ውሃ የሚያስከፍሉም አሉ።"

ሌላው የሃማንስክራል ነዋሪ የ62 ዓመቱ ኤሪክ ሴቦትሳን በአካባቢያቸው ውሃ የሚያከፋፍሉ አንዳንድ የጭነት መኪናዎች በነጻ ማደል ያለባቸውን ውሃ ነዋሪዎች እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉ ይናገራል።

"በየቦታው ወንጀለኞች አሉ። አንዳንድ የውሃ አከፋፋይ አሽከርካሪዎች ውሃውን ይሸጣሉ። ውሃ እንደምትፈልግ ስትናገር መግዛት አለብህ ይላሉ። ምክንያቱም እዚህ ሁሉ ነገር ገንዘብ ስለሆነ የምትከፍለው ከሌለህ ምንም ማድረግ አትችልም።"

ባለፈው ዓመት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሕግ አስከባሪ አካላት እና የአካባቢ መንግሥታት የውሃ ማከፋፈል ሥራ የሚሠሩ የወንጀል ቡድኖችን እንዲያስቆሙ አሳስበዋል።

ዶ/ር አዳም እንደሚለው የውሃ ማፍያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰቱት በኩዋዙሉ-ናታል እና በምሥራቅ ኬፕ ግዛቶች ነው።

"በገጠሪቱ አካባቢ ውሃ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሕዝቦች አሉ፤ ምክንያቱም መሠረተ ልማት የለም። በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ እና ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በመከሰቱ ብዙ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል። ስለዚህ እነዚህ ማፊያዎች በታንከር ውሃ ማቅረብ የጀመሩት በዚህ መንገድ ነው።"

ባለሥልጣናቱ ችግሩን ለማስቆም ምንም አላደረጉም እና በጣም በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ፍርሃት እንደሚሰማቸው ተናግራለች።

"ይህ አሁን ውሃ የምታገኝበት መንገድ ስለሆነ ፍርሃትን ይፈጥራል።"

"ሰዎች በአካባቢያቸው ስለሚከሰቱ ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት አይነግሩህም። ወጥተው እየተከሰቱ ያሉትን ነገሮች ለመናገር ይፈራሉ፤ ምክንያቱም ያኔ ውሃ አያገኙም። ማፊያው ከእንግዲህ ወደ አካባቢያቸው እንደማይመጣ ይሰማቸዋል።"

እንደ የኤሌትሪክ ኃይል እጥረት ሁሉ፣ የውሃው መቋረጥ ዋና ምክንያት በደቡብ አፍሪካ የውሃ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንት አለመኖሩ እንደሆነ አክላለች። ነገር ግን የውሃ ማፍያዎች መጥፎውን ችግር ያባብሳሉ ትላለች።

ሃማንስክራልን የሚያስተዳድረው የጽሽዋን ከተማ ከንቲባ የነበሩት የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፖለቲከኛ ሲሊየርስ ብሪንክ፣ የአካባቢው መንግሥት የራሱን ውሃ ማመላለሻ መኪኖች መግዛት የሚችልበት አማራጭ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

"ይህ አሁንም ለአንዳንድ ምዝበራዎች ክፍት ይሆናል። ሆኖም ግን፣ ለኮንትራክተሮች የሚሰጠውን ማበረታቻ ማስቀረት ይቻላል። ማዘጋጃ ቤቱ እነዚህን ታንከሮች ብቻውን የሚያስተዳድር ከሆነ፣ ከውጭ የሚገኘውን ማበረታቻ ማንሳት ይቻላል። ይህም ብዙ ገንዘብ ይቆጥባል። የረጅም ጊዜ መፍትሔው ግን መሠረተ ልማትን መጠገን መሆን አለበት።"

ከ2023-4 ከንቲባ የነበሩት እና እንደገና በኃላፊነት ለመሥራት የሚወዳደሩት ብሪንክ፣ የአሁኑ የማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ሁኔታውን መቆጣጠር እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ለፌሪያል አዳም፣ ውሃ ማመላለሻ መኪኖችን መግዛት ዘላቂ መፍትሔ አይደለም።

"ይህ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። በጆሃንስበርግ ከተማ ያንን ማድረግ ሊኖርባቸው ይችላል። ግን በመላ አገሪቱ ሊከናወን ይችል እንደሆነ አላውቅም።"

"በትንንሽ ከተሞች ውስጥ እንደ የጉድጓድ ውሃ መጠቀም ያሉ በመኪና ከሚቀርብ ውሃ የተሻሉ መፍትሄን ማግኘት እንችላለን። ነገር ግን የውሃ መኪኖች ለድርቅ ወይም ለአጨር ጊዜ በሚኖር መቆራረጥ ወቅት መሆን አለባቸው። የሁልጊዜ መሆን የለባቸውም። በአሁኑ ጊዜ ግን በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተለመዱ ሆነዋል።"

በሃማንስክራል፣ ሁለት የመኪና ማጠቢያ ሥፍራዎች በጋሪ እያመላለሱ ውሃ ሲሞሉ በታንከሮች ከሚከፋፈለውም ያገኛሉ።

ለእያንዳንዱ የሚታጠብ መኪና ሠራተኞቹ ከባድ የውሃ መያዣዎችን በጋሪ እየገፉ 2 ኪ.ሜ ይጓዛሉ። የውሃ እጥረት የአገሪቱን ምንዱባን የዕለት ተዕለት ኑሮ የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ችግሩን እንዴት እየፈታው እንደሆነ ለመጠየቅ ቢቢሲ የሽዋን አካባቢ ባለሥልጣንን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ራማፎሳ በየካቲት ወር ባደረጉት ንግግር ለውሃ ችግር የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ብሔራዊ የውሃ ቀውስ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱን የውሃ ችግር ለመፍታት "ባለብዙ ዘርፍ ምላሽ " እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በብሔራዊ የውሃ ሕግ መሠረት ግዴታቸውን መወጣት ያልቻሉ የከተማ አስተዳዳሪዎች የወንጀል ክስ እንደሚመሠረትባቸው አስታውቀዋል።

ራማፎሳ እንዳሉት መንግሥታቸው በውሃ ቀውስ ውስጥ የወሰዳቸው እርምጃዎች "በሰዎች ሕይወት ላይ እውነተኛ እና ዘላቂ ለውጥ ማምጣት አለባቸው" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግን የውሃ ቀውስ በቅርቡ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል ብለው አያስቡም።