አሜሪካ የኢራንን ኻርግ ደሴት እንዴት ልትቆጣጠር ትችላለች?

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜናዊ ባሕረ ሰላጤ በኻርግ ደሴት የሚገኘውን እና ኢራን ነዳጅ ለውጭ ገበያ የምትልክበት ቁልፍ መተላለፊያን ለመቆጣጠር ወታደሮችን ሊልኩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ከዚህ ጀርባ ያለው ምንድን ነው? እንዴት ይሠራል? እና ምን አደጋዎችስ አሉ?

የኻርግ ደሴት ለረዥም ጊዜ ኢራን ወደ ቀሪው ዓለም የምትልከው ነዳጅ ዋና መዳረሻ መተላለፊያ ሆኖ ቆይቷል።

ደሴቲቱ በባህር ዳርቻ ላይ የምትገኝ ሲሆን ወደ ሁለት ሚሊዮን በርሜል መጫን የሚችሉ በጣም ግዙፍ ድፍድፍ ነዳጅ ተሸካሚ መርከቦች ላይ ለመጫን የሚያስችል ጥልቅ የውሃ ክፍል አላት።

ወደ 90 በመቶ የሚሆነው ኢራን ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ነዳጅ በኻርግ ደሴት በኩል ያልፋል።

እአአ በ1980ዎቹ ቴህራን ከኢራቅ ጋር ጦርነት ባካሄደችበት ወቅት በኢራቅ አየር ኃይል ተደጋጋሚ የቦምብ ድብደባ ደርሶበታል።

በአሁኑ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ደግሞ እአአ መጋቢት 13 አሜሪካ በደሴቲቱ ላይ 90 ወታደራዊ ዒላማዎችን ደብድባለች። ሆኖም የነዳጅ መሠረተ ልማቱን ከጥፋት አድናዋለች።

አሜሪካ የኻርግ ደሴትን ለመውረር ከወሰነች፣ እርምጃው ኢራን የዘጋችውን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እስክትከፍት እና የዋሽንግተንን ጥያቄ እስክትቀበል ድረስ ወደ ውጭ የምትልከውን ነዳጅ በማቋረጥ ጫና ለመፍጠር የታሰበ ጊዜያዊ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

የኢራን አገዛዝ ያለውን ጽናት እና እምቢተኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ይሳካል የሚለው በጣም አጠራጣሪ ነው።

የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ የአገራቸው ጦር በማንኛውም ወራሪ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ "እሳት እንደሚያዘንቡ" አስጠንቅቀዋል።

ኢራን በደሴቲቱ ላይ የነበራትን መከላከያዎች፣ ከምድር ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳዔሎችን ጨምሮ አጠናክራለች ተብሎ ይታመናል።

ቴህራን አሜሪካ በአንድ ወገን የሰላም ድርድር እያለች በሌላ በኩል ወደ ቀጣናው ወታደሮቿን እያሰማራች ነው በማለት ክስ ታሰማለች።

አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከላከቻቸው ወታደሮች መካከል 5,000 የሚጠጉ የባህር ኃይል አባላት እንዲሁም 2,000 የሚያህሉ አየር ወለዶች ይገኙበታል።

ይህ ደግሞ ኻርግን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከሁለት አንዱን ወይንም ሁለቱንም ልትጠቀም ትችላለች የሚል ሰፊ ግምት አስከትሏል።

በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የአየር ወለድ አባላቱ 20 ካሬ ኪ.ሜ ብቻ በምትሸፍነው በዚህች ትንሽ ደሴት ላይ ቁልፍ ቦታዎችን ለመያዝ ምናልባትም በሌሊት ከአየር ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ።

የአሜሪካ የባህር ኃይል መርከቦች ተዋጊ ጄቶችን እና አነስተኛ ተዋጊ ጀልባዎችን የጫኑ ሲሆን መጀመርያ ኢራን ወደ ምትቆጣጠረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት የተደበቁ ድሮኖችን እና የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

ከአየርም ሆነ ከባህር የሚመጣ ማንኛውም ጦር ጸረ ሰው ፈንጂዎች እና የድሮኖች ጥቃት እንደሚገጥመው ይጠበቃል።

የአሜሪካ ጦር በእርግጠኝነት ይህንን ጥቃት ማለፍ የሚችል ሠራዊት ቢኖረውም ነገር ግን ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ሊያስከፍለው ይችላል።

አሜሪካ ደሴቲቱን ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥራ ለመቆየት የሚገጥማት ሌላው ተግዳሮት ከዋናው የኢራን ክፍል ለሚደርስባት የቦምብ ድብደባ መጋለጧ ነው።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ሁኔታ ሩሲያ እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ መጀመሪያ ላይ የተቆጣጠረችው በጥቁር ባህር ውስጥ የምትገኘዋን የስኔክ ደሴትን ነበር።

ነገር ግን ከዩክሬን ዋና መሬት በተደጋጋሚ በሚመጣ ጥቃት ምክንያት ደሴቲቱን ለቅቃ ለመውጣት ተገድዳለች።

አሜሪካ ለረዥም ጊዜ የኢራንን ግዛት ተቆጣጥራ መቆየቷ በአሜሪካውያን ዘንድ ይሁንታን ላያገኝ ይችላል።

ይህም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በምንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ ዳግም እንደማይሳተፉ በመናገራቸው ጫናው ከመረጧቸው አንዳንድ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ጭምር ሊመጣ ይችላል።

በስተመጨረሻም በኻርግ ላይ ሊፈጸም ስለሚችል የአሜሪካ ጥቃት ብዙ የድምጽ ወጀብ መሰማቱን ልብ ሊባል የሚገባው ሲሆን፣ ይህም የማደናገር ዕቅድ አካል ሊሆን ይችላል።

ደሴቲቱ ለኢራን እና ለእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ያላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ምንም ጥርጥር የለውም።

ነገር ግን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በአሜሪካ ዕይታ ውስጥ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ደሴቶችም አሉ።

ከእነዚህም መካከል ከባንዳር አባስ ቁልፍ ወደብ ዳርቻ የምትገኘው እና በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ያለቸው ላራክ ደሴት አንዷ ናት።

ኢራን በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም የመርከብ እንቅስቃሴ በዚህ ደሴት በኩል እንዲያልፉ እያደረገች ሲሆን፣ መርከቦች እንዲያቋርጡ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ታስገድዳለች።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኢራን ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ከምድር በታች ደብቃበታለች ተብሎ የሚታመነው እና ከኻርግ ደሴት 75 እጥፍ የሚበልጠው ቄሽም የሚባል በባሕረ ሰላጤው ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ደሴት ሌላው ነው።

ሌሎች የአሜሪካን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ሦስት ተጨማሪ ደሴቶች አሉ፤ እነሱም አቡ ሙሳ እና ዘ ግሬተር እና ሌሰር ቱንብስ ናቸው።

እነዚህ ደሴቶች በኢራን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው ቢሆንም ሁሉም በቴህራን ስር ናቸው።

እነዚህ የባሕረ ሰላጤ ደሴቶች ከሌሎች የኢራን ደሴቶች ጋር ሲጣመሩ ለኢራን የመከላከያ ጋሻ ሆነው ያገለግላሉ።

ይህም የመርከብ ጉዞን አደጋ ላይ የሚጥል እና የአሜሪካን የላቀ ወታደራዊ ኃይል ለመገዳደር የሚያስችል መልከዓ ምድራዊ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች ውስጥ አንዳቸውም የማይከሰቱበት ዕድል አለ።

ትራምፕ ወደ ቀጣናው ተጨማሪ ወታደሮችን በመላክ እና የእግረኛ ጦር ዘመቻ የማካሄድ ዕድል መኖሩን በሚያመላክቱበት ወቅት፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር "ከባድ ውይይት" እያካሄደች ነው ሲሉ ሰኞ ዕለት በድጋሚ ተናግረዋል። ይህም "ወታደራዊ እንቅስቃሴያችንን ሊያስቆም ይችላል" ብለዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመረው ጦርነት አምስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በአሁኑ ወቅት፣ ትራምፕ ስለ ቀጣዩ ትልቅ እርምጃቸው ብዙም ፍንጭ አይሰጡም።

ነገር ግን ብዙዎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራናውያን ይልቅ በጣም እንደሚፈልጉት የሚጠረጥሩት "ስምምነት" ላይ መድረስ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካ እና በኢራን አቋም መካከል ያለውን ከፍተኛ ክፍተት ማጥበብን ይጠይቃል።