እስራኤላውያን ላይ ጥቃት የፈጸሙ ፍልስጤማውያንን በሞት የሚቀጣ ሕግ ጸደቀ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ፓርላማ ከባድ የሽብር ጥቃቶችን ፈጽመዋል ተብለው የሚፈረድባቸው ፍልስጤማውያን በቀጥታ በሞት እንዲቀጡ የሚያደርግ ሕግን አጸደቀ።

የተለያዩ ተቋማት ሕጉ አድልዎ የሚፈጥር ነው ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ በርካታ የአውሮፓ አገራት ደግሞ "የዴሞክራሲ መርሆዎችን" ሊያዳክም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ሕጉ በእስራኤል ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች "የሽብርተኝነት ድርጊቶች" ተብለው የሚታሰቡ ከባድ ጥቃቶችን ፈጽመዋል ተብለው የተፈረደባቸው ፍልስጤማውያን እስከ 180 ቀናት ሊራዘም የሚችል ሆኖ በ90 ቀናት ውስጥ በስቅላት እንደሚቀጡ ይደነግጋል።

በንድፈ ሀሳብ ደረጃ በሕጉ መሠረት አይሁድ እስራኤላውያንም ቅጣቱ ሊፈጸምባቸው ቢችልም በተግባር ግን ተፈጻሚ አይሆንባቸውም።

ምክንያቱ ደግሞ የሞት ቅጣት ሊፈጸም የሚችለው የጥቃቱ ዓላማ "የእስራኤልን መንግሥት ኅልውና ውድቅ ለማድረግ" ከሆነ ብቻ ነው።

ሕጉ በቀኝ አክራሪዎቹ ጠንካራ ግፊት የተደረገበት ሲሆን፣ የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ጋቪር ዋነኛ አቀንቃኝ ናቸው።

በፓርላማው ድምጽ ከተሰጠ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ታሪክ ሠራን!!! ቃል ገብተናል። ፈጽመናል" ሲሉ ጽፈው ነበር።

የቤን ጋቪር ፓርቲ አባል የሆኑት ከፍልስጤማውያን ጥቃት የተረፉት እና ባለቤታቸው የተገደሉባቸው ሊሞር ሶን-ሃር-ሜሌች፣ ጥቃቱን ከፈጸሙት ሰዎች መካከል አንዱ እንዴት እንደተፈታ እና በኋላ ላይ በመስከረም 26 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ በተፈጸመው ጥቃት እንዴት እንደተሳተፈ የሚያሳይ ምሳሌን በመጥቀስ ሕጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተከራክረዋል።

በእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) በተደረገው ክርክር ወቅት "ለዓመታት በጭካኔ የተሞላ የሽብር ዑደት፣ በእስር፣ በግዴለሽነት በተደረጉ ስምምነቶች መፈታት እና እነዚህ የሰው ጭራቆች እንደገና አይሁዶችን ለመግደል መመለሳቸውን ስናይ አሳልፈናል።"

የተቃዋሚ ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ የሆኑት ያየር ጎላን ግን ሕጉን ተችተው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ተናግረዋል።

"ሽብርተኞች ላይ የሚጫነው የሞት ቅጣት ሕግ ቤን-ጋቪርን የበለጠ ተወዳጅነት እንዲያገኙ የተነደፈ አላስፈላጊ ሕግ ነው" ብለዋል። "ለእስራኤል ደኅንነት አንድ ቅንጣት አስተዋጽኦ አያደርግም።"

ድምጽ በሚሰጥበት ዋዜማ ላይ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን "ጥልቅ ስጋታቸውን" ገልጸዋል፤ ረቂቅ ሕጉ "እስራኤል በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት ሊያዳክም ይችላል" ብለዋል።

ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም ባለሥልጣን የሕጉን መጽደቅ አውግዞ "በዘፈቀደ የሚፈጸም ግድያን ሕጋዊ ለማድረግ የቀረበ" ሲል ኮንኖታል።

ጋዛን የሚቆጣጠረው ሐማስ በበኩሉ ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ የሕጉ መጽደቅ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚማቅቁ ፍልስጤማውያንን ሕይወት "አደጋ ላይ የሚጥል" መሆኑን በመግለጽ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "የእስረኞቻችንን ጥበቃ እንዲያረጋግጥ" ሲል ጥሪ አቅርቧል።

የእስራኤል የሲቪል መብቶች ማኅበር ቀደም ሲል የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጉን ውድቅ እንዲያደርግ አቤቱታ አቅርቧል።

"ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ፣ ሆን ብሎ አድልዎ የሚፈጥር እና በዌስት ባንክ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ ሕጋዊ ሥልጣን ሳይኖረው የፀደቀ ነው" ሲል በመግለጫው ላይ አውግዞታል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሕጉ ላይ የሚቀረበውን ክርክር ይሰማል ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል በታሪኳ በሞት የቀጣችው ሁለት ሰዎችን ብቻ ነው። አንደኛው በአይሁዶች ጅምላ ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) ትልቅ ሚና ነበረው የተባለው ታዋቂው የናዚ ባለሥልጣን አዶልፍ ኤክማን ነው።