ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን እንዴት ትራምፕን አሳምና ሳይጠበቅ የኢራን ጦርነት አሸማጋይ ሆነች?
በዚህ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ውስጥ ፓኪስታን ራሷን በአደራዳሪነት ማቅረቧ ብዙዎችን አስገርሟል።
ግን ምናልባት ሊያስገርም አይገባ ይሆናል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፓኪስታን መከላከያ ዋና አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ወዳጅ ናቸው።
ትራምፕ በተደጋጋሚ "ተወዳጅ" ፊልድ ማርሻል ብለው ይጠሯቸዋል።
እንዲሁም ሙኒር ኢራንን "ከአብዛኛዎቹ በተሻለ ሁኔታ" እንደሚያውቋት ቀደም ሲል ተናግረዋል።
ኢራን የፓኪስታን ጎረቤት ብቻ ሳትሆን 900 ኪ.ሜ ወይም ከዚያ በላይ ድንበርም ትጋራለች።
ነገር ግን ሁለቱ አገራት ድንበር ከመጋራት ባሻገር ጥልቅ የባሕልና የሃይማኖት ትስስር ያለው የ"ወንድማማች" ግንኙነት አላቸው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የአሜሪካ የአየር ኃይል የጦር ሠፈሮች በአገሪቱ ውስጥ የሉም።
በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ካሉት ብዙ የተለመዱ አሸማጋዮች በተለየ መልኩ እስካሁን ድረስ ወደ ግጭት ተስባ አልገባችም።
ፓኪስታን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሰላም እንዲወርድ ለማሸማገል ብርቱ ፍላጎት አላት።
ያም ሆኖ ኢስላማባድ ከሁለት ጎረቤቶቿ አፍጋኒስታን እና ሕንድ ጋር ግጭት ውስጥ የገባች አገር ራሷን የሰላም መልዕክተኛ አድርጋ እንዴት እንዳስቀመጠች ጥያቄዎች ተነስተዋል።
አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታንን በቦምብ እየደበደበች ሲሆን፣ ከሕንድ ጋር ያለው ውጥረት ባለፈው ዓመት ብቻ የኒውክሌር ጦርነት እንዳያስነሳ የሚል ፍርሃት ቀስቅሶ ነበር።
ፓኪስታን እስካሁን ድረስ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለውን አጣብቂኝ መስመር በመከተል በሁለቱ ወገኖች መካከል መልዕክቶችን በማቀባበል ላይ ብቻ አተኩራለች።
ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሙስሊም አገራት የተወጣጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አስተናግዳለች። እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ የስልክ ውይይቶችንም አድርጋለች።
ነገር ግን በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄድ ግንኙነት ከአደጋ የፀዳ አይደለም።
ሁሉንም ነገር ላለማጣት
ፓኪስታን ከውጭ በምታስገባው ነዳጅ ላይ በጣም ጥገኛ ናት።
ይህ የነዳጅ ዘይት ደግሞ አብዛኛው የሚመጣው በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል ነው።
"ፓኪስታን ከመካከለኛው ምሥራቅ ውጪ ካሉ ሌሎች አገሮች ሁሉ በተለየ እዚህ ግጭት ውስጥ ብዙ ትኩረቷን የሚስቡ ነገሮች አሉ" ሲሉ በአትላንቲክ ካውንስል የደቡብ እስያ ከፍተኛ ፌሎ የሆኑት ማይክል ኩገልማን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ግጭቶች እንዳይባባሱ ለማድረግ ከበቂ በላይ የሆነ አሳማኝ ምክንያት አላት"
የፓኪስታን መንግሥት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የቤንዚን እና የናፍጣ ዋጋን በ20 በመቶ አካባቢ ጨምሯል።
ነዳጅ ለመቆጠብ በሚል እና የመንግሥት ሠራተኞች በሳምንት ለአራት ቀናት ብቻ እንዲሰሩ የሚል ውሳኔዎችንም አስተላልፏል።
"ጦርነቱ ከቀጠለ በፓኪስታን ያለው የኢኮኖሚ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል" ይላሉ በካራቺ የቢዝነስ አስተዳደር ተቋም የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ፋርሃን ሲዲቂ።
እንዲሁም የግጭቱ እየተባባሰ መሄድ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ፓኪስታን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የመከላከያ ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ስምምነት "በሁለቱ አገሮች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት በሁለቱም ላይ እንደተቃጣ ይቆጠራል" የሚል አንቀጽ ይዟል።
ይህ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ጦርነቱን ብትቀላቀልና ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ብትጠይቅ ፓኪስታን ምን ታደርጋለች የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ሲድቂ "ለእኛ ያለው ችግር በሳዑዲ ወደ ጦርነቱ እንድንቀላቀል ከተጠየቅን መላው የምዕራብ ድንበራችን በአብዛኛው ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል" ብለዋል።
ፓኪስታን ከአፍጋኒስታን ጋር "ሁሉን አቀፍ ጦርነት" ውስጥ ገብታለች።
የአፍጋኒስታኑ ታሊባን በድንበሮቿ ውስጥ የሽብር ቡድኖችን እንደሚያስቀምጥ ትከስሳለች፤ ይህንን ግን የታሊባን መንግሥት ይክዳል።
ፓኪስታን በገባችባቸው ጦርነቶች ዲፕሎማሲ ላይ ያላት አቋሟ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን ስትጠየቅ፣ ለዓመታት የሚያስፈልገውን ደህንነት ያላስገኙ ውይይቶችን እንዳካሄደች በመግለጽ ትመልሳለች።
ነገር ግን ሲዲቂ ያላቸው ስጋት ፓኪስታን ወደ ጦርነቱ ልትሳብ ትችላለች የሚል ብቻ ሳይሆን "በአገር ውስጥ ያለ ቅቡልነትም" ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ በአሜሪካ እና በእስራኤል የጋራ የአየር ድብደባ ከተገደሉ በኋላ ባሉት ቀናት፣ ኢራንን የሚደግፉ ሰልፈኞች በፓኪስታን ጎዳናዎች ላይ ተካሂደዋል።
በዚህ ወቅትም በካራቺ የሚገኘውን የአሜሪካን ቆንስላ ጽ/ቤት ለማጥቃት የሞከሩትን ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል።
"በፓኪስታን ያለው የሕዝብ ስሜት ኢራንን በእጅጉ የሚደግፍ ነው" ይላሉ የቀድሞዋ የአሜሪካ፣ የዩኬ እና የተባበሩት መንግሥታት የፓኪስታን አምባሳደር ማሊሃ ሎዲ።
"የፓኪስታን ውሳኔ ሰጪዎች ለዚህ በጣም ስሱ እንደሆኑ እርግጠኛ ነኝ።"
የሆነ ነገር ለማግኘት
ከዚህ ውጭ ደግሞ ፓኪስታን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ቁመና አለ።
"ፓኪስታን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ እንደሌላት ለሚሰነዘርባት ትችት በጣም ስሱ ናት" ሲሉ ኩገልማን ተናግረዋል።
"ራሷን አሸማጋይ አድርጋ ያቀረበችበት ዋናው ምክንያት ይህ አይመስለኝም፣ ነገር ግን ከዚህ ጋር የተያያዘ ነገር አለው።"
"ይህ ከፍተኛ ዲፕሎማሲ ነው፤ ስለሱ ምንም ጥያቄ የለውም" ሲሉ ሎዲ አክለዋል። "ከፍተኛ አደጋ ያለው እና ከፍተኛ ሽልማት ያለው ተግባር ነው። ከተሳካ በእርግጥ ፓኪስታንን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አናት ላይ ያስቀምጣታል።"
ካልተሳካስ?
ሎዲ ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን አያስቡም።
"ፓኪስታን አሁንም በጎ ጥረት እንዳደረገች ልትታይ ትችላለች። ባይሳካላት ደግሞ የፓኪስታን የክህሎት እጥረት ሳይሆን እጅግ በጣም የማይገመት እና ሙሉ በሙሉ እምነት የማይጣልበት ሰው ስለገጠማት ነው።"
ሆኖም ኩግልማን ከዚህ ሁሉ ውይይቱ ይደረጋል ከሚል ግምት በኋላ ሁለቱም ወገኖች የበለጠ ጦርነታቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ተቃውሞ ሊፈጠር እንደሚችል ይገምታሉ።
"ፓኪስታን ገራ ገር ነበረች ለሚሉ ክሶች ተጋላጭ ልትሆን ትችላለች" ሲሉ ተናግረው "ሁለቱም ወገኖች ወደ ፍጥጫ የሚያመሩበትን ቀጣይ እርምጃዎች ለማሰብ የሚያስችል የመተንፈሻ ዕድል ለመፍጠር በመሞከር ወደ ድርድር መጥተዋል" ይህንን ደግሞ ፓኪስታን አላስተዋለችም በሚል ትችቶች ሊደርስባት ይችላል ይላሉ።
'ያልተለመዱ የዲፕሎማሲ ጨዋታዎች'
ነገሮች እንዴት ሊሄዱ እንደሚችሉ ግልጽ ባይሆንም፣ ፓኪስታን ከትራምፕ ጋር ያላትን ግንኙነት በፍጥነት ለማሻሻል ጥረት ማድረጓ ግልፅ ነው።
እአአ በ2025 ፓኪስታን ከሕንድ ጋር በነበራት ፍጥጫ ወቅት ትራምፕን "ወሳኝ የዲፕሎማሲ ጣልቃ ገብነት" አሳይተዋል በሚል ለኖቤል የሰላም ሽልማት መርጣለች።
ከዚህም ባሻገር አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ስትወጣ የካቡል አየር ማረፊያ የቦምብ ፍንዳታን በማቀድ የተከሰሰውን ሰው ለዩኤስ አሳልፋ ሰጥታለች።
"ፓኪስታን ለትራምፕ ሁለት ድሎችን አስቀድማ ሰጥታለች፤ እነዚህም ለእርሳቸው በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይህም ግንኙነቱን እንዲጠናከር እና አዲስ ግለት እንዲያገኝ አድርጓል" ብለዋል ሎዲ።
ኩገልማን አክለውም "ከሕንድ በተለየ መልኩ ያልተለመዱ የዲፕሎማሲ ጨዋታዎችን ለመጫወት ፈቃደኛ ነች" ብለዋል።
"የፓኪስታን ከፍተኛ መሪዎች ፕሬዚዳንቱን ለመማረክ ከመንገድ ወጥተው መሄዳቸው፣ ይህ በዋሽንግተን ዘንድ ያላቸውን ዓላማ በእጅጉ አግዞታል፤ እናም ፓኪስታን በአስተዳደሩ ፊት የበለጠ ማራኪ አደራዳሪ እና አስታራቂ እንድትሆን አድርጓታል።"
ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት የፓኪስታን ብቸኛ መጫወቻ ካርድ አይደለም።
"ፓኪስታን በቀጣናው ዲፕሎማሲ ውስጥ አደጋን መቀነስ ከሁሉ የተሻለው መንገድ መሆኑን ተገንዝባለች" ሲሉ ሲዲቂ ተናግረዋል።
"አሁን የምንኖርበት ዓለም መንግሥታት፣ በተለይም መካከለኛ ኃይሎች፣ ባለብዙ አሰላለፍ ፖሊሲን ለመከተል የበለጠ ዕድል የሚሰጡበት ነው።"
"ፓኪስታን ከኢራን ጋር ለመነጋገር በጣም ተመራጭ የሆነችው እስራኤልን ወይም አሜሪካን ደጋፊ የመሆን ስሜት ስለሌላት ይመስለኛል።"
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዲፕሎማሲ ውይይቶች ቀጥለዋል።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር ማክሰኞ ዕለት ከቻይና አቻቸው ዋንግ ዪ በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ቻይና ይጓዛሉ።
ግን አሁንም ለፓኪስታን ትልቅ ጥያቄዎች አሉ፤ ተፋላሚ ወገኖች የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው።
"በግልጽ ስንነጋገር በአሜሪካውያንና በኢራናውያን መካከል ምን ያህል አለመተማመን እንዳለ እና በአሜሪካም ሆነ በኢራን በኩል የሚቀርቡት ጥያቄዎች ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የስምምነት ዕድሉ ያን ያህል አጓጊ አይደለም" ሲሉ ኩግልማን ተናግረዋል።
"ፓኪስታን አሁን ያወጣቻቸው ዕቅዶች ካልተሳኩ ምን ማድረግ እንዳለባት ማሰቡ እጅግ በጣም አስቸጋሪው ስሌት ይመስለኛል።"