ኢራንን በመደገፍ በቀይ ባሕር ላይ መርከቦችን እንደሚያጠቁ ያሳወቁት የየመን ሁቲዎች እነማን ናቸው?

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

እስራኤል በጋዛው ላይ ካካሄደችው ጦርነት ጋር ተያይዞ በቀይ ባሕር ላይ በሚተለላፉ መርከቦች ላይ ጥቃት በመክፈት የሚታወቁት የሁቲ አማጺያን አሁንም በቀይ ባሕር ላይ ስጋት ፈጥረዋል።

አብዛኛውን የየመንን ክፍል የቆጣጠሩት የሁቲ አማጺያን በሐማስ እና በእስራኤል ጋዛ ውስጥ ጦርነት ሲካሄድ በነበረበት ጊዜ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ እስራኤል ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ናቸው ያሏቸውን መርከቦችን የጥቃት ዒላማ አድርገው ነበር።

አሁን ደግሞ አጋራቸው የሆነችው ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ከተከፈተባት ከአንድ ወር በኋላ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።

የኢራን ወዳጅ ሆነው ለአንድ ወር ዝምታን መርጠው የቆዩት ሁቲዎች ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው ባሏቸው የእስራኤል "ወታደራዊ ይዞታዎች" ላይ በሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን ሲገልጹ እስራኤልም ይህንኑ አረጋግጣለች።

የየመንን ዋና ከተማ ሰነዓን ጨምሮ ሰሜናዊውን እና ሌሎችምን የአገሪቱን ግዛቶች የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች የተጠናከረ ወታደራዊ ኃይል እና የጦር መሳሪያ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም በእስራኤል እና በሳዑዲ ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች አሳይተዋል።

ቡድኑ በኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት በመቃወም አሁን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመክፈቱ ባሻገር በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም ማስታወቁ ስጋት ፈጥሯል።

በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የተናጋው የዓለም የነዳጅ እንቅስቃሴ ባለበት ሁኔታ ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ ቀውሱ እንደሚባባስ እየተነገረ ነው።

የሁቲዎች የቀደመ ጥቃት በቀይ ባሕር ላይ

እስራኤል በሐማስ ለተፈጸመብኝ ጥቃት ምላሽ በጋዛ ላይ ለሁለት ዓመታት የካሄደችውን የማያባራ ጥቃትን ተከትሎ የሁቲ አማጺያን በርካታ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፈዋል።

አሜሪካም በቀይ ባሕር ላይ ያሉትን የጦር መርከቦች በመጠቀም የተወሰኑትን በማክሸፍ ሌሎቹን ደግሞ አቅጣጫቸውን በማስቀየር ጉዳት በማያደርሱባቸው ቦታዎች ላይ እንዲወድቁ ማድረጓን አሳውቃ ነበር።

ሁቲዎች ተቆጣጥረዋቸው በሚገኙት ከየመን የባሕር ዳርቻዎች በሚያስወነጭፏቸው ባለስቲክ ሚሳዔሎች እንዲሁም ድሮኖች ነው በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ዒላማ የሚያደርጉት።

በዚህም ሳቢያ የዓለማችን ታላላቅ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ተቋማት የመርከቦቻቸውን የጉዞ አቅጣጫ በመቀየር በደቡብ አፍሪካ በኩል በመዞር ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ ማድረግን ምርጫቸው አድርገው ነበር።

በመከከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻን የሚመራው ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በእስራኤል ላይ ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ የሚደገፉት በኢራን መሆኑን አሳውቋል።

ሁቲዎች አሁንም ለኢራን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በቀይ ባሕር የሚያልፉ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ ዝተዋል። ይህንንም ተከትሎ የአውሮፓ የባሕር ጉዞ ደኅነንት ተቋም መርከቦች ከየመን የባሕር ክልል እንዲርቁ አሳስቧል።

የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ትራንስፖርት ደኅንነት ተቋም "በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ" ስለሚችሉ በተለይ ከቀይ ባሕር እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ተልዕኮ ጨምሮ እንዳስጠነቀቀው ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ መርከቦች ያለው "ስጋት እስኪቀንስ ድረስ" ከየመን የባሕር ክልል መራቅ ለደኅንነታቸው ጠቃሚ መሆኑን መክሯል።

የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ላይ በቀይ ባሕር ለሚተላለፉ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች የስጋት ደረጃቸው "ከፍተኛ" ሲሆን ሌሎች ደግሞ "በመካከለኛ" የስጋት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የሁቲ አማጺያን እነማን ናቸው? ዓላማቸውስ ምንድን ነው?

ሁቲዎች የየመን ታጣቂ ቡድን ሲሆኑ መሠረታቸውም ዛይዲስ በመባል የሚታወቁት የአገሪቱ የሺዓ ሙስሊም ነው።

ቡድኑ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ሲቋቋም በወቅቱ የየመን ፕሬዝዳንት በነበሩት አሊ አብደላህ ሳሌህ አገዛዝ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለመዋጋት በሚል ነበር።

ስማቸውንም የወሰዱት ከንቅናቄው መሥራች ከሁሴን አል ሁቲ ነው። ራሳቸውንም ‘አንሳር አላህ’ ወይም የአምላክ ደጋፊዎች ብለው ይጠራሉ።

በአሜሪካ መሪነት ምዕራባውያኑ ኢራቅን መውረራቸውን ተከትሎ ሁቲዎች “አምላክ ታላቅ ነው፣ ሞት ለአሜሪካ፣ ሞት ለእስራኤል። እርግማን ለአይሁዶች፣ ድል ለእስልምና’ የሚልም መፈክርን ማሰማት ጀመሩ።

እስራኤል አሜሪካ እና ሰፊውን ምዕራባዊ ክፍል የሚቃወም እና በኢራን የሚመራው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ አባል መሆናቸውንም አስታወቁ። ከሁቲ በተጨማሪ ሐማስ እና ሄዝቦላህ የዚህ ጥምረት አካል ናቸው።

ሁቲዎች በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕረ በኩል ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የተነሱበት ምክንያት ዋናዋ ደጋፊያቸው በተከፈተባት ጥቃት ምክንያት ነው።

ምንም እንኳን በኢራን ላይ ጥቃቱ ከጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ኢራንን ደግፈው በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። እንዲሁም በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ "የጠላት" የሚሏቸውን መርከቦች እንደሚመቱ አሳውቀዋል።

ሁቲዎች ሰፊውን የየመንን ክፍል እንዴት ተቆጣጠሩ?

ሁቲዎች በመጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥንካሬ ማግኘት የቻሉት ፕሬዝዳንት አሊ አብደላህ ሳሌህን በተኩት በፕሬዝዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ ላይ በተነሱበት ወቅት ነው። ይህም በአውሮፓውያኑ 2014 ወቅት ነው።

ከቀድሞው ጠላታቸው እና ከሥልጣን ከተነሱት ፕሬዝዳንት ሳሌህ ጋር ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም እሳቸውን ወደ ሥልጣን ለመመለስ አስበው ነበር።

በቀጣዩ ዓመትም በየመን በሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የሳዓዳ ግዛትን ተቆጣጠሩ። ይህም ዋና ከተማዋን ሰንዓን መቆጣጠር ያስቻላቸው ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ሃዲንም ወደ ውጭ እንዲሰደዱ አስገደዷቸው።

የየመን ጎረቤት የሆነችው ሳዑዲ አረቢያም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በመፈጸም ፕሬዝዳንት ሃዲን ወደ ሥልጣን በመመለስ የሁቲዎችን ኃይል ለማሸነፍ ሞከረች።

ሳዑዲ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን በመደገፍ ነበር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱን በየመን ውስጥ የፈጸመችው።

ነገር ግን ሁቲዎች ከአገር ውስጥ ባሻገር በውጭ ኃይሎች የተፈጸመባቸውን ጥቃቶች በመቋቋም ሰፊውን የየመንን ግዛት በመቆጣጠር ቀጥለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ወደ ሳዑዲ ጎራ ለመቀላቀል ሲሞክሩም በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ።

የሁቲ አማጺያን በማን ይደገፋሉ?

የሁቲ አማጺያን በሊባኖስ ውስጥ ከሚገኘው ከሺዓው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።

ሄዝቦላህም ለሁቲ አማጺያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ሰፊ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ኮምባቲንግ ቴሬሬዚም ሴንተር’ የተሰኘው የአሜሪካው የምርምር ተቋም አስታውቋል።

ሁቲዎች ኢራንን በአጋርነት የሚያይዋት ሲሆን፣ ሳዑዲ አረቢያን ደግሞ ሁለቱም የጋራ ጠላታቸው አድርገው ነው የሚመለከቷት።

ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሳሪያ ታቀርባለችም የሚሉ ጥርጣሬዎችም ጎልተው ይሰማሉ።

ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2017 በሳዑዲ መዲና ሪያድ ላይ ያስወነጨፉትን ባለስቲክ ሚሳዔል ያቀረበችው ኢራን ናት በማለት አሜሪካ እና ሳዑዲያ አረቢያ ከስሰው ነበር።

በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2019 ሁቲዎች የሳዑዲ ነዳጅ ማምረቻዎችን ለማጥቃት የተጠቀሙባቸውን የክሩዝ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን የሰጠችው ኢራን ናት በሚልም ሳዑዲ አረቢያ ትከሳለች።

ሁቲዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአጭር ርቀት ሚሳዔሎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያስወነጨፉ ሲሆን፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዒላማዎችም ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

እነዚህን መሳሪያዎች ለሁቲ አማጺያን ማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት በኢራን ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ እገዳን የሚጥስ ቢሆንም ኢራን በጭራሽ ክሱን አትቀበለውም።

ሁቲዎች አቅም አና የመንን ምን ያህል ይቆጣጠራሉ?

ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠው የየመን መንግሥት የፕሬዝዳንቱ አመራር ምክር ቤት ነው። ፕሬዚዳንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ በአውሮፓውያኑ 2022 ሥልጣናቸውን ለምክር ቤቱ አስተላልፈዋል።

የምክር ቤቱ መቀመጫም በሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ነበር። ሆኖም አብዛኛው የየመን ሕዝብ የሚኖረው በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ነው።

ሁቲዎች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ግብር የሚሰበስቡ ሲሆን፣ የአገሪቱንም መገበያያ ገንዘብ ያትማሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2010፣ ከ100 ሺህ እስከ 200 ሺህ የታጠቁ ወታደሮች እና ያልታጠቁ ደጋፊዎች እንዳላቸው ገልጿል።

ምክር ቤቱ ይህንን መረጃ በሁቲ እንቅስቃሴ ላይ ባለሙያ የሆኑትን አህመድ አል ባህሪን ዋቢ አድርጎል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጨማሪም በየመን ሁቲ አማጺያን የተመለመሉ 1500 ሕጻናት በውጊያ ከአምስት ዓመት በፊት ሞተዋል ብሏል።

የሁቲ አማጺያን ረጅሙን የየመን የቀይ ባሕር ጠረፍ ይቆጣጠራሉ። ከእነዚህ አካባቢዎች ነው በመርከቦች ላይ ጥቃቶችን የሚፈጽሙት።

ሁቲዎች ለቀሪው ዓለም እና ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወሳኙን የቀይ ባሕር መተላለፊያ የሆነውን ባብ ኤል ማንዳብን መዝጋት እንደሚችሉ በማሳየት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጫና ማሳረፍ እንደሚችሉ ማሳየት ይፈልጋሉ።

በተጨማሪም ሐማስን እና ኢራንን ለመሰሉት አጋሮቻቸው ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት የመፈጸም አቅም እንዳላቸው በተግባር አሳይተዋል።

በተጨማሪም በጋዛ ጦርነት ወቅት እና አሁን ደግሞ ኢራንን በመደገፍ ከየመን ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ ጥቃት ፈጽመዋል።

ቀደም ሲል በእስራኤል ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከእስራኤል በኩል የተሰጣቸው አጸፋ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በተፈጸመባቸው የአየር ድብደባዎች ከባድ ቁሳዊ ጉዳትን ከማስተናገዳቸው በተጨማሪ በርካታ መሪዎቻቸው ተገድለውባቸዋል።