ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተጠቁ “የማያዳግም” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንደዛቱት በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ “የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ” ምላሽ እንደምትሰጥ ኢራን አስጠነቀቀች።
ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማክሰኞን በቀነ ገደብነት ካስቀመጡ በኋላ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በአገራቸው ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ ምላሻቸው ከባድ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
አራግቺ “ያለጥርጥር [አሜሪካ] ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ ምላሽ ይጠብቃታል” በማለት ለፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን-ኖዌል ባሮት ተናግረዋል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረውም የአሜሪካ ዛቻ “የጦር ወንጀልን እና የዘር ማጥፋትን ተቀባይነት የሚያደርግ ነው” በማለት ከስሰዋል።
ከፈረንሳዩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ስለተደረገው ውይይት በኢራን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል የወጣው ዘገባ ላይ ባሮት በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በቀጣናው ያለውን ውጥረት የሚያባብስ መሆኑን በመጥቀስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲደረግ ጠይቀዋል።