ቀጥታ, ጥቃት ከተፈጸመባት “እጅግ የከፋ” አጸፋ እንደምትመልስ የዛተችው ኢራን የአብዮታዊ ዘቧ የደኅንነት አዛዥ መገደላቸውን አስታወቀች

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት አዛዡ ማጂድ ኻዴሚ መገደላቸውን በአገሪቱ የዜና ማሠራጫዎች በኩል ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል የሄዝቦላህ አመራርን ለመግደል በፈጸመችው ጥቃት በስህተት ቡድኑን የሚቃወም ፖለቲከኛ ተገደለ

    እስራኤል እሁድ ዕለት በሊባኖስ የሄዝቦላህ አባልን ለመግደል ባደረገችው ሙከራ በስህተት ቡድኑን አጥብቆ የሚቃወም ከፍተኛ የፖለቲካ ቡድን መሪ ተገደለ።

    በጉዳይ ላይ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ጥቃቱ የታሰበውን ዒላማ መግደል እንዳልቻለ ገልጾ፣ በሲቪሎች ላይ “ለደረሰው ጉዳት መጸጸቱን" ገልጿል።

    በአብዛኛው ክርስቲያኖች በሆኑ ግለሰቦች የተዋቀረው የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ፣ በአንድ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር ፒየር ሞኡዋድን እና ባለቤቱን ፍላቪያን እንደገደለ አስታውቋል።

    የመኖሪያ ሕንጻው የሚገኘው ከቤይሩት በስተምሥራቅ በምትገኘው አይን ሳዴህ በምትባል በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች መኖሪያ በሆነችው ከተማ ውስጥ ነው።

    የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ጥቃቱ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶችን እንደገደለ አስታውቋል።

    የአካባቢው ከንቲባ ሟቾቹ ይኖሩ የነበረው ከዒላማው በታች ባለ አንድ ፎቅ ውስጥ ነበር ብለዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "በርካታ የማይመለከታቸው ግለሰቦች በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው መመልከት ችለናል" ብሏል።

    የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ ፒየር ሞአዋድ "ተዋጊም ሆነ ወታደራዊ ዒላማ አልነበረም" ካለ በኋላ ከአሰቃቂው ጥቃት በፊት ከቤተሰቡ ጋር የትንሳዔ በዓልን እያከበረ እንደነበር ተናግሯል።

    ፓርቲው ሄዝቦላህን አውግዞ ጥቃቱ የተከሰተው ወታደራዊ ግጭቶች ወደ መኖሪያ መንደሮች ዘልቀው እየመጡ በመሆናቸው ነው ብሏል።

  2. እስራኤል የኢራን ቁልፍ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካን መደብደቧን አስታወቀች

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በኢራን የፔትሮኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ላይ ድብደባ መፈጸሙን ገለጹ።

    ሚኒስቴሩ አክለውም ጦሩ “በሙሉ ኃይሉ” የኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንዲቀጥል ታዝዟል ብለዋል።

    “የእስራኤል መከላከያ በኢራን ግዙፉ የሆነውን እና [በአሳሉያህ] የሚገኘውን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽሟል ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በሌላ ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጨምረው ገልጸዋል።

    “ለኢራን የፔትሮኬሚካል የውጭ ንግድ በጥምረት 85 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል ስለዚህ አገልግሎት አይሰጡም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

    ካትዝ አክለውም በአሳሉያህ የሚገኘው ፋብሪካ የአገሪቱን ግማሽ የፔትሮኬሚካል ምርቶች የሚያመርት ነበር ብለዋል።

    ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ሁለት የፔትሮኬሚካል ኩባንያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዘግቧል።

    ካትዝ የኢራን ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሟን የገለጹት የፋርስ የዜና ወኪል በአሳሉያህ ከሚገኘው በሳውዝ ፓርስ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ብዙ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

  3. ኢራን በእስራአል ሃይፋ አካባቢ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

    የኢራን ሚሳዔል በሃይፋ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ አራት ሰዎች መግደሉ ተገለጸ።

    የጸጥታ አካላት ቦምቡ ከወደቀ በኋላ ባለመፈንዳቱ የሕይወት አድን ሠራተኞችን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ገልጸዋል።

    እንደ የእስራኤል ባለሥልጣናት ገለጻ በጥቃቱ የተመታው ቤት ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎችን ለማውጣት የጎረቤት ግድግዳን መሰርሰር አስፈልጎ ነበር።

    ጥቃቱ ከደረሰበት ሕንጻ ማዶ የምትኖረው ሞር ባረል፣ የእስራኤል በርካታ የአየር መቃወሚያዎች እያሉ እንኳን የኢራንን የሚሳዔል ጥቃት እያሰጉ መኖር በአደጋ የታጀበ ነው፤ ምናልባት ደህንነትህ የተጠበቀ ወይንም በማንኛውም ሰኮንዶች ለአደጋ እንደመጋለጥ ያለ የሕይወት ቁማር ነው ብላለች።

    እስራኤል የቴህራንን ባሌስቲክ ሚሳዔል መምታት በመቻሏ ውጤታማ አንደሆነች ብትገልጽም ኢራን ግን ዒላማ የምታደርገው የእስራኤልን የደህንነት ስሜት ነው ሲሉ ነዋሪዎቿ በምሬት ይናገራሉ።

    ያንን ደግሞ አንድ ሕንጻ ላይ በሚፈጸም ጥቃት መምታት ይቻላል ሲሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

  4. ኢራን በኩዌት የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

    ኢራን በኩዌት ከዚህ ቀደም 'የደረሰባቸውን ጥቃት በመሸሽ' ወደ ቡቢያን ደሴት የተወሰዱ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

    የአሜሪካ ጦር ኩዌት ወደሚገኘው ቡቢያን ደሴት ከተወሰደ በኋላ የኢራን ሚሳዔል ዒላማ መሆኑን የቴህራን ባለሥልጣናት በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለት የኢራን ካታም አል አንቢያ ዋና መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በቪዲዮ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በደሴቱ ላይ የሚገኙ የሳተላይት እና ጦር መሣሪያዎችን መምታታቸውን ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ኢብራሂም ዞልፋቅሪ ጥቃቱን የፈጸሙት በድሮን በመታገዝ መሆኑን መግለጻቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ ወታደሮቿን ከዚህ ቀደም የነበሩበት አሪፍጃን የጦር ሠፈር በቴህራን ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ወደ ደሴቲቱ ማዛወሯን ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

    ቡቢያን የኩዌት ትልቁ ደሴት ሲሆን በባሕረ ሰላጤው ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ላይ ይገኛል።

    ኢራን በኩዌት ላይ የሚሳዔል ጥቃት ከፈጸመች በኋላ በስብርባሪዎች ስድስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር።

  5. ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ለአሸማጋዮች ምላሽ ማዘጋጀቷን አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የእስራኤል-አሜሪካ እና የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት እየሠሩ ላሉ አሸማጋዮች ቴህራን ምላሽ ማዘጋጀቷን ተናገሩ።

    ይህ የኢራን አስተያየት የመጣው ሮይተርስ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳቸው ምንጮች ፓኪስታን ጦርነቱን ለማስቆም አዲስ ዕቅድ በመንደፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው የሚል ዘገባ ካወጣ በኋላ ነው።

    በኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዋቢ የተደረጉት እስማኤል ባጊ በአሸማጋዮች በኩል የቀረበው የአሜሪካ ባለ 15 ነጥብ ዕቅድ “በምንም መንገድ ለእኛ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

    ጦርነቱን ለመቋጨት ያለሙ ድርድሮች “የጦር ወንጀል ለመፈፀም በማስጠንቀቂያ እና በዛቻ የተሞሉ ናቸው” ሲሉ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ቃል አቀባዩ ይልቁንም “በራሳችን ፍላጎት እና ግምገማ” ኢራን አቋሟን የምታሳውቅበትን ሰነድ አጠናቅራለች ብለዋል።

    “ከመጀመሪያው ጀምሮ ምን እንደምንፈልግ እና እንዲታለፉ የማንፈቅዳቸው ቀይ መስመሮች ምን እንደሆኑ እናውቃለን። እናም አሁንም አቋማችን ግልፅ ነው። ይህ ንግግር ከተጀመረበት ቅፅበት አንስቶ መልሶቻችን ዝግጁ ነበሩ” በማለት ኢራን የራሷን ምላሽ ማዘጋጀቷን ጠቁመው፤ “ጊዜው ሲደረስ ዝርዝሩን እናሳውቃለን” ሲሉ አክለዋል።

    ሮይተርስ እና አክሲዮስ የተኩስ አቁም ዕቅድ ለአሜሪካ እና ለኢራን መቅረቡን ዘግበዋል

    እስካሁን የምናውቀው፦

    እንደ ዘገባዎች ከሆነ የቀረበው ዕቅድ ሁለት ደረጃዎች አሉት። ዕቅዱ አፋጣኝ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚል ሲሆን፤ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ የተጠናከረ ስምምነት ይከተለዋል። የአሜሪካው የዜና ምnእጭ አክሲዮስ አደራዳሪዎች የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መምከራቸውን ጠቁሟል።

    እንደ አክሲዮስ ከሆነ በድርድሩ ፓኪስታን፣ ግብፅ እና ቱርክ እየተሳተፉ ነው። የፓኪስታን የጦር አዛዥ አሲም ሙኒር “ምሽቱን ሙሉ” ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መረጃ ሲለዋወጡ እንደነበር ሮይተርስ የዜና ወኪል አክሏል።

    አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አካል መሆኑን ውድቅ አድርገዋል።

    የድርድር ወሬዎች እየተሰሙ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ቀነ ገደብ መጣላቸውን ተከትሎ ነው።

    እስከአሁን የማናውቀው፦

    የተኩስ አቁም ዕቅዱን በተመለከተ የኢራን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስተያየት እየተጠበቀ ነው።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ የጥቃቶች ዛቻ እና የኒውክሌር መርሃ ግብርን የመሰሉ ቁልፍ የጦርነቱ ማጠንጠኛ ነጥቦች በስምምነቱ እንዴት እንደታዩ አይታወቅም።

    አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ከዚህ ቀድም ያልተሳኩትን የስምምነት ዕቅዶች ለአብነትም ባለ 15 ነጥቡን የአሜሪካ የስምምነት ሃሳብ ምን ያህል እንደሚያንፀባርቅ አይታወቅም።

    በጦርነቱ በርካታ ጥቃቶች እየተፈፀመባቸው ያሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት በዚህ ስምምነት እንዴት እንደታዩም የሚታወቅ ነገር የለም።

    በሁለቱም ወገኖች ምላሽ ለመስጠት የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ ስለመኖሩም እንዲሁ።

  6. ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተጠቁ “የማያዳግም” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንደዛቱት በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ “የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ” ምላሽ እንደምትሰጥ ኢራን አስጠነቀቀች።

    ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማክሰኞን በቀነ ገደብነት ካስቀመጡ በኋላ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በአገራቸው ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ ምላሻቸው ከባድ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

    አራግቺ “ያለጥርጥር [አሜሪካ] ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ ምላሽ ይጠብቃታል” በማለት ለፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን-ኖዌል ባሮት ተናግረዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረውም የአሜሪካ ዛቻ “የጦር ወንጀልን እና የዘር ማጥፋትን ተቀባይነት የሚያደርግ ነው” በማለት ከስሰዋል።

    ከፈረንሳዩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ስለተደረገው ውይይት በኢራን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል የወጣው ዘገባ ላይ ባሮት በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በቀጣናው ያለውን ውጥረት የሚያባብስ መሆኑን በመጥቀስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

  7. የአብዮታዊ ዘቡ የደኅንነት አዛዥ ዛሬ መገደላቸውን ኢራን አስታወቀች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት አዛዡ ማጂድ ኻዴሚ መገደላቸውን በአገሪቱ የዜና ማሠራጫዎች በኩል ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው የደኅንነት አዛዡ ዛሬ ጠዋት መገደላቸውን ገልፆ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ማጂድ ኻዴሚን ኢላማ በማድግ ከስሷል።

    እስራኤል ለኢራን አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት አዛዥ ግድያ ኃላፊነቱን ወስዳለች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በቴሌግራም ላይ ባወጣው የጽሑፍ መልዕክት ግድያውን ለኢራን አብዮታዊ ዘብ “ሌላ ከባድ ኪሳራ” ብሎታል።

    ኢራን አብዛኛውን ጊዜ የከፍተኛ ባለሥልጣኖቿን ግድያ ስታረጋግጥ የነበረ እስራኤል እና አሜሪካ ግድያዎቹ መፈጸማቸውን ከገለጹ በኋላ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ ግድያ ቀድማ አሳውቃለች።

    ማጂድ ኻዴሚ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በተካሄደው የኢራን እና የእስራኤል የ12ቱ ቀናት ጦርነት ወቅት የተገደሉትን ሞሐመድ ካዜሚን ተክተው ሲሠሩ የነበሩ አዛዥ ናቸው።

    ማጂድ ኻዴሚ ባለፈው ጥር የተቀሰቀሰውን ኢራን ውስጥ በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በማቀጣጠል ከስሰዋቸው ነበር።

    የደኅንነት አዛዡ በተቃውሞው ወቅት የእስራኤል የሳይበር ስለላ ክፍልን ጨምሮ 10 የውጭ አገራት የደኅንነት ተቋማት መላው ኢራንን ባዳራሰው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈዋል ብለዋል።

    መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች የዜና አገልግሎት በጥር ወሩ የኢራን መንግሥት እርምጃ ቢያንስ 7,000 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

  8. በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለስድስተኛ ሳምንት ቀጥለዋል

    በመካከለኛው ምሥራቅ የአደጋ ጊዜ ደወሎች መሰማታቸውን ቀጥለዋል።

    ዛሬ ሠኞ የተፈፀሙ ጥቃቶች፦

    ኢራን፡ በቴህራን ግዛት የመኖሪያ አካባቢ ላይ በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈፀመ ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ በአካባቢው ከተገደሉት ውስጥ ስድስቱ ሕፃናት ናቸው ብሏል።

    ጥቃቱ በቴህራን በሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎች ላይም ጉዳት አድርሷል።

    በርካታ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በጥቃቱ ተስተጓጉሎ የነበረው የጋዝ አቅርቦት አሁን መመለሱን ዘግበዋል።

    እስራኤል፡ እሁድ ምሽት በአገሪቱ ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በርካታ ጉዳቶችን ሪፖርት አድርጓል።

    በ40ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንድ ወንድ እና ሴት እንዲሁም ሁለት የአምስት ዓመት ሴት ልጆች በሃይፋ በጭስ ታፍነው ሕክምና ተከታትለዋል።

    በማዕከላዊ እስራኤል አንድ የ34 ዓመት ግለሰብ ከባድ ጉዳትን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል።

    ቆየት ብሎ የእስራኤል ጦር ከኢራን የተወነጨፈን ሚሳዔል ለማክሸፍ እየጣረ መሆኑን ገልጾ ነበር። ይህን ካለ ከአጭር ጊዜ በኋላ ጦሩ በጥበቃ ስር ባለው በመላው አገሪቱ መንቀሳቀስ እንደሚቻል አስታውቋል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፡ በአቡ ዳቢ የኢንዱስትሪ ዞን በቴክኖሎጂ ኩባንያ ላይ ፍርስራሾች ወድቀው አንድ የጋና ዜግነት ያለው ግለሰብ መጎዳቱን የግዛቱ የሚዲያ ቢሮ አስታውቋል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት በኤምሬትስ ሁለት ዋነኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች መካከል በአንደኛው ላይ የተፈጸመን የኢራን የድሮን ጥቃት እየተከታተለ መሆኑን ገልፀዋል።

    በጥቃቱ የተጎዳ ሰው እንደሌለም አክለው ተናግረዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ፡ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሁለት ድሮኖች መያዛቸውን እና መውደማቸውን አስታውቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌባኖስ እሁድ ዕለት በእስራኤል ተጨማሪ የአየር ጥቃቶች ከተፈፀመ በኋላ ሰዎች የደረሰውን ጉዳት እየመረመሩ ነው። ትናንት በተፈፀሙት ጥቃቶቹ በመላው አገሪቱ ቢያንስ 11 ተገድለዋል።

    የሌባኖስ ባለሥልጣናት ከየካቲት መጨረሻ ወዲህ 1,461 ሰዎች በእስራኤል መገደላቸውን ተናግረዋል።

  9. አሜሪካ እና ኢራን የአስቸኳይ ተኩስ አቁም ዕቅድ እንደቀረበላቸው ተዘገበ

    አሜሪካ እና ኢራን ከዛሬ ጀምሮ ተኩስ እንዲቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚጠይቅ የስምምነት ዕቅድ በአሸማጋዮች እንደቀረበላቸው የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበ፤ ሌሊት ላይ ለኢራን እና ለአሜሪካ ደረሰው ግጭቶችን ለማቆም የሚያስችል ማዕቀፍ የተዘጋጀው በፓኪስታን ነው።

    ሁለት ደረጃ ያለው ይህ የስምምነት ማዕቀፍ በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን በመቀጠል ደግሞ ወደ አጠቃላይ ስምምነት እንዲያድግ ያደርጋል ተብሏል።

    አሸማጋይ አገራት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኤነርጂ መሠረተ ልማት እንደሚያወድሙ በመዛት እስከ ማክሰኞ ድረስ የሰጡት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት ነው።

    ኢራንም በሲቪል መሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ “እጅግ የከፋ” የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች። አደራዳሪዎች ግጭቱ በድጋሚ ጡዘት ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ውጥረቱን የሚያረግብ መፍትሔ ለማግኘት ላይ ታች እያሉ መሆኑ ተዘግቧል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጭ “ሁሉም [የዕቅዱ] ክፍሎች ዛሬ ስምምነት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል” ማለታቸው ተዘግቧል። ዕቅዱ መጀመሪያው ላይ በፓኪስታን በኩል በኤሌክትሮኒክ መንገድ በመግባቢያ ስምምነትነት እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሀሳብ እንዳለም ተገልጿል።

    አሸማጋዮች የ45 ቀናት ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው የአሜሪካው ዜና ምንጭ አክሲዮስ ነው። እንደ ዘገባው ይህንን ጥረት እያደረጉ ያሉት የፓኪስታን፣ የግብፅ እና የቱርክ አደራዳሪዎች ናቸው።

    የትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺም የጽሑፍ መልዕክት እንደተለዋወጡ ዘገባው ጠቅሷል። አክሲዮስ ዕሁድ ዕለት ያነጋገራቸው ምንጮች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ስምምነት ላይ የመደረስ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር “ጥልቅ ድርድር” እያደረጉ መሆኑን እና የማክሰኞው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ለዜና ምንጩ ተናግረዋል።

    “[ስምምነት ላይ ለመድረስ] ጥሩ ዕድል አለ፤ ነገር ግን ስምምነት የማይፈጽሙ ከሆነ ግን እዚያ ያለውን ሁሉንም ነገር አጋያለሁ” ብለዋል።

  10. በ24 ሰዓታት ውስጥ 15 መርከቦች በሆርሙዝ በኩል ማለፋቸው ተዘገበ

    ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ “በኢራን ፈቃድ” 15 መርከቦች ሆርሙዝ ወሽመጥን መሻገራቸውን ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ የባሕር የትራፊክ እንቅስቃሴው ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በ90 በመቶ ዝቅተኛ መሆኑንም አክሏል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺን ጨምሮ አንዳንድ የኢራን ባለሥልጣናት ወሳኙ የመርከቦች መተላለፊያ እንዳልተዘጋ በተጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን፤ ሆኖም “ለጠላት አገራት” የተዘጋ ነው ይላሉ።

    ለአብነት ያህል ኢራን ከጣለቻቸው ገደቦች ኢራቅ ነፃ መሆኗን ትናንት አስታውቃለች።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ባለሥልጣናት እና ሕግ አውጭዎች ወሽመጡን ሚጠቀሙ መርከቦች ላይ ታክስ ለመቅረጥ ስለመወጠናቸው ጠቁመዋል።

    አንድ የኢራን ፕሬዝዳንት ቢሮ ረዳት የሆርሙዝ ወሽመጥ በጦርነቱ ለደረሰው ጉዳት ካሳ የሚውል ቀረጥ ሲከፈል “በድጋሚ ይከፈታል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኢራን ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ በሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ላይ የተመሠረተ ሲሆን አስከ ነገ ማክሰኞ ድረስ ኢራን የባሕር መስመሩን ካልከፈተች ከባድ ውድመት እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀዋል።

  11. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የጦር ወንጀል እንደሚፈጽሙ እየዛቱ ነው?

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ የነዳጅ ጉድጓዶች እና የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች እንደሚያጋዩ ዝተዋል። በዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች እና ስምምነቶች መሠረት እነዚህ ድርጊቶች የጦር ወንጀል ለመፈጸም እንደተሰነዘሩ ዛቻዎች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ።

    የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ወታደራዊ ወይም መንግሥታዊ አገልግሎት እንዳላቸው ክርክር ተነስቶ ቢሆንም እንኳ፤ እንደዚህ ዓይነት ተቋማትን ሆነ ብሎ ማውደም በንጹኃን ዜጎች ሕይወት ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል።

    ሉዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ፤ አሜሪካም ሆነች ኢራን አባል ባልሆኑበት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መሥራች ዋና ዐቃቤ ሕግ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ትራምፕ የሚደበድቧቸው የኢራንን የኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ኢራን እና እስራኤል ጥቃት የሚፈጽሙባቸው የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ሕጋዊ የጥቃት ዒላማ ተደርገው አይቆጠሩም።

    ፍርድ ቤቱ ባወጣው የሮም ሕግ መሠረት “ሆነ ብሎ ጥቃቶችን ወታደራዊ ግብ ወደሌላቸው የሲቪል ተቋማት ማዞር” የጦር ወንጀል መሆኑን ሞሬኖ ኦካምፖ አስረድተዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም “ዓለም አቀፍ ሕግ እንደማያስፈልጋቸው” እና “በራሳቸው ሥነ ምግባር” እንደሚመሩ ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምንት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ይህ ጉዳይ የጦር ወንጀል ሊሆን የሚችል ስለመሆኑ በተጠየቁበት ወቅት ሀሳቡን ውድቅ አድርገዋል።

    “በእርግጥም፤ ይህ አስተዳደር እና የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ሁሌም ቢሆን የሚንቀሳቀሱት በሕጉ ውስጥ ሆነው ነው። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ [በኢራን ላይ የሚካሄደው] የኤፒክ ፊውሪ ዘመቻን ግቦች ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የሚያደርጉትን ግስጋሴ አይገቱም። የኢራን አገዛዝ ከአስተዳደሩ ጋር ስምምነት እንደሚፈጽም ነው የሚጠብቁት” ብለዋል።

  12. በኢራን መኖሪያ ሕንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት “13 ሰዎች” ተገደሉ

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን አቅራቢያ በሚገኘው የባህሬስታን አውራጃ ዛሬ ሰኞ ጠዋት በተፈጸመ ጥቃት “13 ሰዎች” መገደላቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናገሩ።

    ቢቢሲ ፐርዢያን ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ጥቃቱ የተፈጸመው በመኖሪያ አካባቢ ላይ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

    የተመታውን ሕንጻ ፍርስራሽ የማስወገድ ሥራ መቀጠሉን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ፍርስርሹ ሥር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

    የፋርስ የዜና ወኪል በበኩሉ በዚሁ ከተማ በሚገኘው ‘ቃሌ ሚር’ የተባለ አካባቢ ውስጥ የሚገኙ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ዒላማ መደረጋቸውን ዘግቧል። ቴህራን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ትናንት ምሽት እና ዛሬ ጠዋት ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመውባቸዋል።

    ቴህራን ውስጥ ሌላኛው ጥቃት የደረሰው በሻሪፍ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ላይ ነው። የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ማዕከል ሕንጻ፣ እንዲሁም ትምህርት ተቋሙ ውስጥ የሚገኘው መስኪድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ የወጡ ፎቶዎች በዋና ከተማዋ ከሚገኘው የዩኒቨርሲቲው አከባቢ ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የቴህራን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሻሂድ ቤሄሽቲ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ኢራን ውስጥ የሚገኙ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

  13. ኢራን በሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከተፈጸመባት “እጅግ የከፋ” አጸፋ እንደምትመልስ ዛተች

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአጸያፊ ቃላት በታጀበ ጽሁፋቸው ኢራን ላይ መዛታቸውን ተከትሎ፤ ቴህራን አሜሪካ እና እስራኤል በሲቪል ዒላማዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ “እጅግ የከፋ” አጸፋ እንደምትመልስ አስጠነቀቀች።

    በኢራን ከፍተኛ የወታደራዊ ዘመቻ ዕዝ የሆነው ኻታም አል አንቢያ ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “የሲቪል ዒላማዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚደገሙ ከሆነው፤ የማጥቃት እና የአጸፋ ዘመቻችን ቀጣይ ደረጃ እጅግ የከፋ እና መጠነ ሠፊ ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋል።

    በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ላይ ይህ ማስጠንቀቂያ የተላለፈው ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እስከ ማክሰኞ ዕለት ድረስ የማትከፍት ከሆነ በአገሪቱ የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ከዛቱ በኋላ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ወደ 10 ቀናት አራዝመውት የነበረው ቀነ ገደባቸው የሚጠናቀቀው በዛሬው ዕለት ነበር። ይሁን እንጂ ትናንት በማኀበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ማክሰኞ ከምሽቱ 8፡00” በማለት የጻፉ ሲሆን ይህም ቀነ ገደቡን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ወደ ማክሰኞ ሌሊት 10 ሰዓት እንዳዛወሩት ያመላከተ ሆኗል።

    ፕሬዝዳንቱ ከዚህ አስቀድሞ ባሰፈሩት መልዕክት አጸያፊ ቃላትን ተጠቅመው ኢራንን “ሲኦል” እንደሚያደርጉ ዝተዋል። ከመልዕክቱ በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ደግሞ ሰኞ ዕለት ስምምነት ላይ ሊደረስ የሚችልበት “ጥሩ ዕድል” እንዳለ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ነገር ግን ጦርነቱን ለማመቋጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ በቶሎ ካልተደረሰ “ሁሉንም ነገር ማፈንዳት እና ነዳጁን መቆጣጠርን” ጉዳይ እያሰቡበት እንደሆነ ተናግረዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች። ከዓለም የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶው ያህል የሚተላለፍበት ይህ መስመር መዘጋቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር እና በመላው ዓለም የዋጋ ግሽበት ይጨምራል የሚል ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል።

  14. የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አገልግሎት በዋይት ሀውስ አካባቢ የተሰማን ተኩስ እየመረመረ ነው

    የአሜሪካ የሹማምንት ጠባቂ የሆነው ሴክሬት ሰርቪስ እሁድ ጠዋት በዋይት ሐውስ አቅራቢያ የነበረን ተኩስ እየመረመረ ነው።

    የፖሊስ መኮንኖች በዋሽንግተን ዲሲ ላፋይት ፓርክ አካባቢ ሪፖርት የተደረገን ተኩስ ምላሽ ለመስጠት ያቀኑ ሲሆን ከፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት በስተ ሰሜን በሚገኘው በበፓርኩ እና በዙሪያው አካባቢ ፍተሻ ማድረጋቸውን ተቋሙ አስታውቋል።

    እስካሁን ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪ ያልተያዘ ሲሆን በተኩሱ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ሴክሬት ሰርቪስ ገልጿል። ተቋሙ እና አጋሮቹ ከተኩሱ ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ የተነሳባቸውን ሰዎችን እና ተሽከርካሪን እየፈለጉ ነው።

    በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ነበሩ። አገልግሎቱ በዋይት ሐውስ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን “የተጠናከረ የደኅንነት ዝግጁነት ሥራ ላይ ውሏል” ብሏል።

    ምርመራው በአካባቢው የተወሰኑ መንገዶች ዘግቶ መቆየቱን እና አሁን መከፈታቸውን የአገልግሎቱ ቃል አቀባይ አንተኒ ጉሊለሚ በኤክስ ገፃቸው አስታውቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ እሁድ እና ቅዳሜን አብዛኛው ወደሚያሳልፉበት ማራ ላጎ ፍሎሪዳ ለፋሲካ በዓል እንዳልተጓዙ ታውቋል።

    የዋይት ሐውስ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ስቲቨን ቻንግ ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገፃቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፋሲካ በዓል “ያለማቋረጥ በዋይት ሐውስ እና በኦቫል ቢሯቸው እየሰሩ ነው” ብለዋል።

    ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጠው ላቀረበው ጥያቄ ዋይት ሐውስ ምላሽ አልሰጠም።