የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የእስራኤል-አሜሪካ እና የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት እየሠሩ ላሉ አሸማጋዮች
ቴህራን ምላሽ ማዘጋጀቷን ተናገሩ።
ይህ የኢራን አስተያየት የመጣው ሮይተርስ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳቸው ምንጮች ፓኪስታን ጦርነቱን ለማስቆም አዲስ ዕቅድ
በመንደፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው የሚል ዘገባ ካወጣ በኋላ ነው።
በኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዋቢ የተደረጉት እስማኤል ባጊ በአሸማጋዮች በኩል የቀረበው የአሜሪካ ባለ 15 ነጥብ ዕቅድ “በምንም መንገድ ለእኛ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ጦርነቱን ለመቋጨት ያለሙ ድርድሮች “የጦር ወንጀል ለመፈፀም በማስጠንቀቂያ እና በዛቻ የተሞሉ ናቸው” ሲሉ ለፕሬዝዳንት
ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ ይልቁንም “በራሳችን ፍላጎት እና ግምገማ” ኢራን አቋሟን የምታሳውቅበትን ሰነድ አጠናቅራለች ብለዋል።
“ከመጀመሪያው ጀምሮ ምን እንደምንፈልግ እና እንዲታለፉ የማንፈቅዳቸው ቀይ መስመሮች ምን እንደሆኑ እናውቃለን። እናም
አሁንም አቋማችን ግልፅ ነው። ይህ ንግግር ከተጀመረበት ቅፅበት አንስቶ መልሶቻችን ዝግጁ ነበሩ” በማለት ኢራን የራሷን ምላሽ ማዘጋጀቷን
ጠቁመው፤ “ጊዜው ሲደረስ ዝርዝሩን እናሳውቃለን” ሲሉ አክለዋል።
ሮይተርስ
እና አክሲዮስ የተኩስ አቁም ዕቅድ ለአሜሪካ እና ለኢራን መቅረቡን ዘግበዋል
እንደ ዘገባዎች ከሆነ የቀረበው ዕቅድ ሁለት ደረጃዎች አሉት። ዕቅዱ አፋጣኝ ተኩስ
አቁም ስምምነት የሚል ሲሆን፤ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ የተጠናከረ ስምምነት ይከተለዋል። የአሜሪካው የዜና ምnእጭ አክሲዮስ አደራዳሪዎች የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መምከራቸውን ጠቁሟል።
እንደ አክሲዮስ ከሆነ በድርድሩ ፓኪስታን፣ ግብፅ እና ቱርክ እየተሳተፉ
ነው። የፓኪስታን የጦር አዛዥ አሲም ሙኒር “ምሽቱን ሙሉ” ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መረጃ ሲለዋወጡ እንደነበር
ሮይተርስ የዜና ወኪል አክሏል።
አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት የጊዜያዊ የተኩስ አቁም
ስምምነቱ አካል መሆኑን ውድቅ አድርገዋል።
የድርድር ወሬዎች እየተሰሙ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን
እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ቀነ ገደብ መጣላቸውን ተከትሎ ነው።
የተኩስ አቁም ዕቅዱን በተመለከተ የኢራን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስተያየት
እየተጠበቀ ነው።
የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ የጥቃቶች ዛቻ እና የኒውክሌር መርሃ ግብርን የመሰሉ ቁልፍ የጦርነቱ
ማጠንጠኛ ነጥቦች በስምምነቱ እንዴት እንደታዩ አይታወቅም።
አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ከዚህ ቀድም ያልተሳኩትን የስምምነት ዕቅዶች ለአብነትም
ባለ 15 ነጥቡን የአሜሪካ የስምምነት ሃሳብ ምን ያህል እንደሚያንፀባርቅ አይታወቅም።
በጦርነቱ በርካታ ጥቃቶች እየተፈፀመባቸው ያሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት በዚህ ስምምነት
እንዴት እንደታዩም የሚታወቅ ነገር የለም።
በሁለቱም ወገኖች ምላሽ ለመስጠት የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ ስለመኖሩም እንዲሁ።