ትራምፕ አስካሁን ምን ያህል ጊዜ ለኢራን የጊዜ ገደብ አስቀመጡ?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።
ጦርነቱ በጀመረ በመጀመሪያው ሳምንት ኢራን እጅ የማትሰጥ ከሆነ ከባድ ውድመት እንደሚደርስባት በመገልጽ ፕሬዝዳንቱ ከማስጠንቀቅ አልፈው ከስድስት ሳምንት በኋላ የኢራንን ሥልጣኔ በአንድ ሌሊት ዶግ ዓመት እንደሚያደርጉት እየዛቱ ነው።
ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያወጧቸው ማስጠንቀቂያዎች እና የጊዜ ገደቦች እየተራዘሙ አሁን ዛሬ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሚጠናቀቀው የመጨረሻው የኢራን መሪዎች ያላቸው ዕድል መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምን ያህል ጊዜ ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብን አስቀመጡ?
- መጀመሪያ፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም. ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች “ከትልቁ ጀምሮ ያሏት የኃይል ማመንጫዎች ፍረስርሳቸው ይወጣል” ብለው ዝተው ነበር።
- ሁለተኛው፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ከኢራን ጋር “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ንግግር’ መደረጉን በመግለጽ የጥቃቱን ቀነ ገደብ በአምስት ቀናት አራዘሙት።
- ሦስተኛው፡ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም. ደግሞ “በኢራን መንግሥት ጥያቄ መሠረት” የኃይል መሠረተ ልማቶችን የማጥቃት ቀነ ገደባቸውን በ10 ቀናት ማራዘማቸውን ሰኞ መጋቢት 28ን የመጨረሻው ቀን አደረጉት።
- የ48 ሰዓታት ማስጠንቀቂያ፡ የሰኞው ቀነ ገደብ በተቃረበበት ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ “መአት” ከማዝነቸባው በፊት “48 ሰዓታት” እንደቀሩ አስጠንቅቀው ነበር።
- ባለፈው ዕሁድ፡ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሰዓታት ውስጥ የማይከፈት ከነሆ ኢራን ‘ሲኦል” እንደምትሆን ዝተዋል።
- የማክሰኞው ማስጠንቀቂያ፡ ዛሬ ማክሰኞ አስከ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ኢራን የቀረበላትን የድርድር ሃሳብ የማትቀበ ከሆነ "ሥልጣኔዋ ተመልሶ እንዳይመጣ ሆኖ ይሞታል" ሲሉ ዝተዋል።