ቀጥታ, ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

ኢራን የቀረበላትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ "ሙሉ ሥልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ይሞታል" ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቁ። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሌሊት የሚጠናቀቀውን ለኢራን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ባለፉት ቀናት ሲሰጡ የነበረውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን አጠናክረው ደግመውታል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ኢራን የቀረበላትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ "ሙሉ ስልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ይሞታል" ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቁ።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሌሊት የሚጠናቀቀውን ለኢራን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ባለፉት ቀናት ሲሰጡ የነበረውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን አጠናክረው ደግመውታል።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባሰፈሩት መልዕክት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት ያበቃለታል” ሲሉ በኢራን ላይ ዝተዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም:

    "ያ እንዲሆን አልፈልግም፣ ነገር ግን ሳይከሰት አይቀርም። ቢሆንም ግን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ እና አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ አለ፤ የተለዩ ብልህ እና ብዙም ጽንፈኛ ያልሆኑ የበላይነትን ይይዛሉ፤ ምናልባትም የሚያስደንቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ ማን ያውቃል?" በማለት ጽሁፋቸው ላይ የጠየቁት ትራምፕ ዛሬ ሌሊት ሊከሰት የሚችለውን አመልክተዋል።

    "በዓለም ረጅም እና ውስብስብ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነውን ነገር ዛሬ ማታ የምናየው ይሆናል። የ47 ዓመታት ጭቆና፣ ሙስና እና ሞት በመጨረሻም ያበቃል። እግዚአብሔር ታላቁን የኢራን ሕዝብ ይባርክ!”

    ትራም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ሃሳብን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ያበቃል።

    ኢራን የተኩስ አቁም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት እና የሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላትን በመጠየቅ የራሷን ቅድመ ሁኔታዎች አቅርባለች።

    በሌላ በኩል ደግሞ በፓኪስታን መሪነት ዲፕማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ በቀሩት ሰዓታት አንዳች ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ለስድስት ሳምንታት የተካሄደው ጦርነት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

  2. የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ ፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሳዑዲ አረቢያን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካዎችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ከፍተኛ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።

    በጥቃቱ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአሜሪካ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ በመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች እና በአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች “የተሳካ ጥቃት” መፈጸሙን አመለክቷል።

    ዘቡ እንዳለው ከተቋማቱ በተጨማሪ “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጥቅሞች እና ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላት” ዒላማ መሆናቸውን ገልጿል።

    በመግለጫው ላይ ኢራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ሰኞ ዕለት “በአሳሉዬህ የፔትሮኬሚካል ማዕከል” ላይ የተፈጸመባትን ጥቃት ለመበቀል መሆኑ ተጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ “ቀይ መስመራችንን የምታልፍ ከሆነ ምላሻችን ከመካከለኛው ምሥራቅም የሚያልፍ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ እና አጋሮቿ ኢራን ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች ውስን ሆነው ቆይተው” የነበረ መሆኑን ገልጿል።

    ይህ ለመልካም ጉርብትና ሲባል ኢራን አሳይታው የነበረው “ቁጥብነት” ዒላማዎችን እንድትለይ አድርጓት መቆየቱን፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ “ይህ ቁጥብነት እንደማይኖር” በመጥቀስ አስፈላጊ በተባሉ ዒላማዎች ላይ “ያለማወላወል” እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።

  3. በቱርክ ኢስታንቡል የእስራኤል ቆንስላ አካባቢ "ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው" ተገደሉ

    በቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በተኩሱ ሁለት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    መገናኛ ብዙኃኑ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች “እርምጃ ተወስዶባቸዋል’ ያሉ ሲሆን ቢያንስ ሁለቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    የቱርክ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በፖሊስ ጋር ተኩስ የከፈቱት ሦስት ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

    የኢስታንቡል አስተዳዳሪ ከአጥቂዎቹ ውስጥ አንዱ መገደሉን እና ሁለቱ ላይ ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ለሲኤንኤን ተርክ ተናግረዋል።

    "በፖሊስ ኃይላችን ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ሁለቱ ፖሊሶቻችን ቆስለዋል። ከአሸባሪዎች ውስጥ አንዱ ተገድሏል። ሁለቱ ደግሞ በተወሰደባቸው እርምጃ ቆስለዋል" ያሉት ገዢው ጥቃቱ ትልቅ ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አነስተኛ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

    በቱርክ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የእስራኤል ዲፕሎማት አለመኖሩን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።

    የእስራኤል ኤምባሲ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኝ ሲሆን በኢስታንቡል ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ነው።

    የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር በቆንስላው አካባቢ ስለተከፈተው ተኩስ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

    በርካታ የፖሊስ አባላት በቆንስላው አካባቢ ታይተዋል። ቆንስላው የሚገኘው በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል ሰሜናዊ ክፍል ነው።

    ጥቃቱ የተፈጸመው በቀጣናው እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ውጥረቶች በተባባሱበት ወቅት ነው።

  4. አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች

    እንደ አሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እና የምሥል ትንተናዎች ከሆነ አሜሪካ እስካሁን ድረስ በጦርነቱ ቢያንስ ዘጠኝ አውሮፕላኖችን አጥታለች።

    መጋቢት 27 2018 ዓ.ም.- ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄትን ለማገዝ የተጓዙ ሁለት የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ከኢራን መነሳት አልቻሉም። አውሮፕላኖቹ በጠላት እጅ እንዳይወድቁ በሚል እንዲወድሙ መደረጉ ተዘግቧል። የተረጋገጡ ምሥሎች አውሮፕላኖቹ በማዕከላዊ ኢራን እንደወደሙ አሳይተዋል። ቢቢሲ ቨሪፋይ የአውሮፕላኖቹን ዓይነት ለመለየት ባለሙያዎችን ጠይቋል።

    መጋቢት 25- በማዕከላዊ ኢራን ተዋጊ ጄት ተመትቶ ወድቋል። ባለሙያዎች ከስብርባሪው ባገኙት መረጃ ተመትቶ የወደቀው ጄት “ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኤግል” የተባለው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት መሆኑን ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ቀን ኒዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤ-10” የተባለ ጄት በባሕረ ሰላጤው ተከስክሷል። አብራሪው ቀድሞ ተመንጥቆ በመውጣት ሊተርፍ ችሏል።

    መጋቢት 20- ማረጋገጥ የቻልነው ምሥል “ኢ-13” የተባለ አውሮፕላን የኢራንን ጥቃት ተከትሎ በሳዑዲ አረቢያ ልዑል ሱልጣን አየር ጣቢያ ለሁለት መከፈሉን ያሳያል።

    መጋቢት 3- “ኬሲ-135” የተባለ የነዳጅ መሙያ አውሮፕላን በምዕራብ ኢራቅ ተከስክሶ ስድስት ወታደሮች ሕይወታቸው ማለፉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) አስታውቋል። ክስተቱ እየተመረመረ ቢሆንም ኮማንዱ በጠላት አሊያም በወዳጅ አገራት ተኩስ አለመውደቁን ግን ጠቁሟል።

    የካቲት 23- ሦስት የአሜሪካ “ኤፍ-15ኢ” ጄቶች ሴንትኮም “በወዳጅ አገራት ያልተጠበቀ ክስተት” ሲል በገለፀው ሁነት በኩዌት ወድቀዋል። ስድስቱም አባላት አስቀድመው መውጣት መቻላቸውንም አክሏል። ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተንቀሳቃሽ ምሥል ማረጋገጥ እንደቻለው ጄቶቹ በኩዌት ከተማ ምዕራባዊ ክፍል ወደ መሬት ሲሽከረከሩ ነበር።

  5. በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ ዓለም በስጋት የሚጠብቃቸው ቀጣይ ሰዓታት

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ አውዳሚ ጥቃት ይፈጸማልበማለት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በአንድ በኩል ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘው ጥቃታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ ኢራንም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ አገራት ላይ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ካልተከበረ ኢራንን “ወደ ድንጋይ ዘመን” ይመልሳታል ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ሰዓት እየተቆጠሩ ናቸው።

    ይህ የኢራንን የሲቪል የኃይል ማመንጫ ተቋማትን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደርጋል የተባው የትራምፕ ዛቻ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ “የጦር ወንጀል ነው” በማለት ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።

    ይህ ሁሉ የጥቃት እና የውድመት ዜና እየተሰማ ባለበት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው። በፓኪስታን መሪነት የሚደረገው ጥረት ወደ ወሳኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

    ፓኪስታን ጦርነቱን ለማብቃት በአሸማጋይነት “አዎንታዊ እና ውጤታማ ጥረት” እያደረገች መሆኑን በኢስላማባድ የኢራን አምባሳደር ጠቅሰው በሂደቱም “ወሳኝ እና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ደረጃ ላይ እየተደረሰ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል አሜሪካ በአስቸኳይ ከተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣላችው ዕቀባ ካነሳች በኋላ ቀጣይ የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ ሃሳብ ብታቀርብም፤ ኢራን ግን የራሷን የድርድር ሃሳብ በመቅረብ ውድቅ አድርጋዋለች።

    ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት የተከፈተባት ጦርነት በዘላቂነት እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና በጥቃቱ ለደረሰባት ውድመት የመልሶ ግንባታ ሃሳብን አቅርባለች።

    እየተካሄዱ ያሉት ንግግሮች በፍጥነት ተቋጭተው በቀጣይ ሰዓታት ውስጥ ከስምምነት ካልደረሰ አሜሪካ ባላት ኃይል ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ እርምጃ እንደምትወስድ፣ ኢራንም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ አጸፋ እንደምትመልስ እየዛቱ ነው።

    ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ያሉት መጪዎቹ ሰዓታት ለኢራን ብቻ ሳይሆን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ብሎም ለመላው ዓለም መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች የሚተላለፉበት ሊሆኑ ይችላሉ።

    መላው ዓለምም ምን ሊከሰት እንደሚችል በስጋት እና በጉጉት እየጠበቀ ነው።

  6. የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 13 ሺህ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች

    እስራኤል በኢራን ተጨማሪ ጥቃቶችን መፈፀሟን ሪፖርት ካደረገች በኋላ የአሜሪካ ጦር ጦርነቱ ከተጀመረ ከየካቲት 21 ወዲህ 13 ሺህ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን እያካሄደች ባለችው እና “ኤፒክ ፉዩሪ” ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ዘመቻ ከ155 በላይ የኢራን መርከቦችን መውደማቸውን አሊያም መጎዳታቸውንም አስታውቃለች።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) ከደበደባቸው ዒላማዎች መካከል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና መስሪያ ቤት፣ የአየር መቃወሚያ ስርዓት፣ የባላስቲክ ሚሳኤል ጣቢያዎች እና የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ሰርጓጅ መርከቦች ይገኙበታል ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ዜና ወኪል የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,665 ንፁሃንን ጨምሮ 3,500 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

  7. ኢራን ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት” እንደተፈፀመባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን ገለፀ

    የእስራኤል-አሜሪካ ጦርነት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,600 የሚሆኑ ንፁኃንን ጨምሮ 3,500 የሚሆኑ ሰዎች በአገሪቱ እንደተገደሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የዜና ወኪል (ሀራና) አስታውቋል።

    ትናንት ሠኞ ብቻ 59 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 58 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን በምሽት ዳሰሳው ገልጿል።

    ያለፉት 24 ሰዓታት “ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ከተፈፀሙት ጥቃቶች ከፍተኛ መጠን ነው” ብሏል።

    ሠኞ ዕለት በቴህራን የሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርስቲ፣ በመኖሪያ ሕንፃ እና በኬሚካል ፋብሪካ ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ትላልቅ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

    ቡድኑ በመስክ ሪፖርት፣ ከአካባቢው ምንጮች፣ ከሕክምና እና ድንገተኛ አደጋ ምንጮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረቶች እንዲሁም ከፎቶግራፎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ከመንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫዎች በመጭመቅ አሃዛዊ መረጃውን እንደሚያጠናክር ገልጿል።

  8. የፀጥታው ምክር ቤት በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን ለመጠበቅ ድምፅ ሊሰጥ ነው

    የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢራን ለአብዛኛው መርከቦች የተዘጋውን ቁልፍ የባሕረ ሰላጤው መተላለፊያ ለማስከፈት ድምፅ ይሰጣል።

    የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በሆነቸው ባሕሬን የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት ቀርቦ የነበረ እና ወደዚህ ሳምንት የተላለፈ ነው።

    የውሳኔ ሀሳቡ ይዘት መጀመሪያ ከቀረበ በኋላ ማሻሻያ እንደተደረገበት ታውቋል።

    በመጀመሪያው ረቂቅ አባል አገራት “ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እና ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃዎችን እንዲወስዱ “ይፈቅዳል።”

    አዲሱ ማሻሻያ ደግሞ ደኅንነት የተሞላበት ጉዞ ለማድረግ “ጥረቶችን ማቀናጀት፣ ተፈጥሯዊ መከላከል፣ ከሁኔታው ጋር የሚመጣጠን እርምጃ” “በጥብቅ እንደሚያበረታታ” ይጠቅሳል።

  9. የእስራኤል ጦር ኢራናውያን ዛሬ ባቡር እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀ

    የእስራኤል ጦር በይፋዊ የማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ በፋርስ ቋንቋ ባሰፈረው መልዕክት በኢራን የሚኖሩ ሰዎች “ለደህንነታችሁ” በማለት ”በባቡር ከመጓዝ ተቆጠቡ” ብሏል።

    ማስጠንቀቂያው በመላው አገሪቱ ለሚኖሩ ኢራናውያን መሆኑን የገለጸው ጦሩ በኢራን ሰዓት አቆጣጠር “እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት” ድረስ ማስጠንቀቂያው እንደሚቆይ ገልጿል።

    አክሎም “በባቡር ውስጥ መሆን አና በባር ሃዲዶች አቅራቢያ መገኘት ሕይወታችሁን አደጋ ላይ ይጥለዋል” ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ኢራን የሚገኘው የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛታቸውን ተከትሎ ነው።

    ሠኞ ምሽት የእስራኤል ጦር ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ያላቸውን "የቴህራን መሠረተ ልማቶችን" ዒላማ በማድረግ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀሙን እና የሄዝቦላህ አባላትን መግደሉንም ገልጿል።

    ከዚህ ውጭም የእስራኤል ጦር ከኢራን ወደ እስራኤል የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን መቀልበሱን አስታውቋል።

  10. የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ቡድን በኢራን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ነው ሲል አስጠነቀቀ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ጥቃቶች በመላው ኢራን እየተፈጸሙ በመሆናቸው ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታወቀ።

    እአአ ከመጋቢት 17 እስከ ሚያዚያ 3 ባለው ጊዜ ውስጥ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ ገበያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች እና የባህል ቅርስ ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲል ቡድኑ ገልጿል።

    ኦቻ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጋቢት 30 ድረስ ከ2,100 በላይ ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን፣ ከ27,900 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ 3.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጦርነቱ እንደጎዳቸው አስታውቋል።

    እናም ከጦርነቱ መጀመሪያ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ሳምንታት ከ115,000 በላይ የሰላማዊ ሰዎች መገልገያዎች ተጎድተዋል ሲል አክሎ ተናግሯል።

    ኦቻ በተጨማሪም "ወሳኝ በሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና የኢንዱስትሪ መንደሮች ላይ የተካሄደው ጥቃት የመብራት፣ የውሃ እና የቴሌኮሙኒኬሽንን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስተጓጎሉ ፈጣን እና ረዥም ጊዜ የሚቆይ የአካባቢ እና የጤና አደጋዎችን አስከትሏል" ብሏል።

  11. በኩዌት ሌሊቱን በተፈጸመ ጥቃት አሜሪካውያን ተጎዱ

    ኢራን በኩዌት አሊ አለ ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት 15 አሜሪካውያን ጉዳት እንደረሰባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ተናገሩ።

    አንድ ባለሥልጣን አብዛኛዎቹ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 373 የአሜሪካ ጦር አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    ከእነዚህ መካከል 330ዎቹ ወደ ሥራቸው ሲመለሱ አምስቱ ግን ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ለሲቢኤስ ተናግሯል።

  12. ትራምፕ በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ላይ ምን አሉ?

    ትናንት ምሽት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት፣ የሲአይኤ ዳይሬክተሩ ጆን ራትክሊፍ እንዲሁም የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄነራል ዳን ኬይን በዋይት ሐውስ መግለጫ ሰጥተዋል።

    መግለጫው ያተኮረው አርብ ዐዕለት በኢራን ተመትቶ የተከሰከሰው ተዋጊ ጄት ውስጥ የነበሩ ሁለቱ የአሜሪካ አየር ኃይል አባላትን ለማዳን ስለተካሄደው ዘመቻ ማብራራት ነበር።

    የትራምፕ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የበረራ አባላቱን ለማዳን የተደረገውን "ጀግንነት" ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ማክሰኞ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደገና ካልተከፈተ አሜሪካ በኢራን የኃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።

    "መላው አገሪቱ በአንድ ሌሊት ሊጠፋ ይችላል፤ ያ ምሽት ደግሞ ነገ ማታ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

    የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ኢራን ወደ "ድንጋይ ዘመን" ትመለሳለች ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።

    "ድልድይ አይኖራቸውም" ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ምንም አይነት የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም" ሲሉም ዝተዋል።

    በዜና መግለጫው ላይ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች እነሆ፡

    • ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለይ ሁለተኛውን የአየር ኃይል አባል ፍለጋ ለማግኘት በተካሄደው የ48 ሰዓታት የሕይወት አድን ጥረት ሁሉም የሠራዊቱ አባላት ሙሉ ዕምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
    • “በጣም አደገኛ ተልዕኮ” መሆኑ እንደተነገራቸው ያስረዱት ትራምፕ ነገር ግን “የሚገባው እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” ብለዋል።
    • አንድ የዜና ተቋም አንድ ፓይለት መጥፋቱን ከዘገበ በኋላ ተልእኮው ችግር ገጥሞት እና ከባድ አድርጎት ነበር ያሉት ትራምፕ የኢራን ባለሥልጣናትም ከዘገባው በኋላ የአየር ኃይል አባሉን ለመያዝ የራሳቸውን ዘመቻ መክፈታቸወን ተናግረዋል። ዋናውን የመረጃ ምንጩን ለማግኘት የአሜሪካ ባለስልጣናት ጠንክረው እየሰሩ ነው ብለዋል።
    • ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ከኢራን ጋር የሚደረግ ማንኛውም አዲስ ስምምነት በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ በኩል “ነፃ የነዳጅ ዘይት ፍሰት” መፍቀድን ማካተት አለበት ብለዋል ።
    • አሜሪካ የኢራን መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዳግመኛ ከዛቱ በኋላ የአሜሪካ ዘመቻ “ነፃነታቸውን ለማግኘት ለመሰቃየት ፈቃደኞች ለሆኑ” ኢራናውያን ጠቃሚ ነው ብለዋል።
  13. ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢራን ለጋዜጠኞች ምን አሉ?

    ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ዓመታዊ የትንሳዔ በዓል ላይ ተገኝተው የኢራን ጦርነትን በሚመለከት ምላሽ ሰጥተዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ምን አሉ?

    • ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ የኢራንን ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በድጋሚ ዝተዋል። “የማይከፍቱ ከሆነ ድልድይ አይኖራቸውም፤ የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም። ምንም አይኖራቸውም” ካሉ በኋላ “ከዚህ በላይ መሄድ አልችልም፤ ከእነዚህ ከሁለቱ በላይ የከፋ ነገር አለ” ብለዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የአሜሪካን ተዋጊ አውሮፕላን መትታ የጣለችው በክህሎት ሳይሆን “በአጋጣሚ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ሆኖም “አሁን ምናልባት በውስጣቸው ብዙ ጥይት ቀዳዳ ያላቸው አንዳንድ ሄሊኮፕተሮች አሉን” ብለዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም ያሉ ሲሆን፣ "እብዶች ናቸው እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በእብዶች እጅ ማስገባት አንችልም" ብለዋል።
    • አክለውም እንደ "እኔ ቢሆን ኖሮ የኢራንን ሰፊ የነዳጅ ዘይት ክምችት እወስድ ነበር" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው “በርካታ ገንዘብ አገኝበት ነበር” ብለዋል።
    • ትራምፕ በርካታ አሜሪካውያን በኢራን የሚያካሄዱትን ጦርነት ቢቃወሙም አሁንም ጦርነቱን የሚቃወሙ “ጅሎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ድረስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ የመጨረሻው መሆኑን ተናግረው፤ ኢራን ለአሜሪካ ጦርነቱ እንዲያበቃ ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ የሰጠችውን ምላሽ “ወሳኝ” ነገር ግን “በቂ ያልሆነ” ሲሉ ገልጸውታል።
  14. ኢራን አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ዕቅድ ውድቅ አደረገች

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ኢርና ቴህራን አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ ምላሽ መስጠቷን ዘገበ።

    እንደ ኢርና ዘገባ ከሆነ ኢራን የቀረበላትን የተኩስ አቁም ጥሪ በቋሚነት ጦርነቱን ማቆም አስፈላጊ ነው በሚል ውድቅ አድርጋለች።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቴህራን አሜሪካ ላቀረበችው የተኩስ አቁም ምክረ ሃሳብ ምላሿን በፓኪስታን በኩል ማስገባቷን ዘግበዋል።

    የዜና ወኪሉ ኢራን ለአሜሪካ ያቀረበችው ባለ አስር ነጥብ ምላሽ የተኩስ አቁምን ውድቅ የሚያደርግ እና በቋሚነት ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት መኖር አለበት የሚል መሆኑን ዘግቧል።

    ኢራን ለአምስት ሳምንታት የዘለቀው ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም በመጠየቅ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት የቀረበላትን የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ አድርጋለች።

    ኢራን ለአሜሪካ በሰጠችው ምላሽ ውስጥ "በቀጣናው ያለው ጦርነት እንዲቆም ፣ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ውስጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድን የሚያረጋግጥ አሰራር እንዲኖር፣ እንዲሁም መልሶ ግንባታ እና ማዕቀቦችን ማንሳትን እንዲካተቱ" የሚሉ ፍላጎቶቿን ዘርዝራለች።

    ኢርና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በተደጋጋሚ የጊዜ ገደብ በማራዘም ከቀድሞ ዛቻዎቻቸው ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን" አክሎ ዘግቧል።

    ትራምፕ እስከ ማክሰኞ ዕለት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፈት ከሆነ በቴህራን ላይ “ሲኦል” ይወርዳል ሲሉ “ድልድዮችን እና የኃይል ማመንጫዎችን” እንደሚያጠቁ ዝተዋል።

  15. ዩኤኢ የኢራን እርምጃ የባሕረ ሰላጤውን አገራት ወደ አሜሪካ የሚገፋ ነው አለች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን እና “በእኛ እና በሌሎች አገራት ላይ እየዘነበ ያለውን ሚሳዔል እና ድሮን” ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮችን መፍታት የማይችል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረግ አስጠነቀቀች።

    የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ በሰጡት መግለጫ አገራቸው ግጭቱ እንዲቆም እንደምትፈልግ ተናግረው ነገር ግን ወደፊት በቀጣናው ውስጥ ቀጣይነት ያለው አለመረጋጋትን የሚፈጥር እንዳይሆን ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በጥነምረት ጥቃት ከከፈቱባት ወዲህ ኢራን የዓለም ዋና የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዘግታለች።

    በየቀኑ በጣት የሚቆጠሩ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ብቻ በወሽመጡ የሚያልፉ ሲሆን ይህ ግን ከተለመደው ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።

    የኢራን ስትራቴጂ የባህረ ሰላጤውን አገራት ከዋሽንግተን ጋር ያላቸውን የደህንነት ትስስር ሊያጠናክር እና የእስራኤልን ተፅዕኖ በቀጣናው ላይ የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት "በእጥፍ" እንደምታሳድግም አክለው ተናግረዋል።

    “የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በማንኛውም አገር ታግቶ መያዝ አይችልም” ያሉት አማካሪው፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደ የባህር ኃይል ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ባትሆንም፣ “በወሽመጡ ውስጥ የሚደረግ የባህር ጉዞን ለማረጋገጥ በአሜሪካ የሚመራ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ጥረት” ትቀላቀላለች ብለዋል።

  16. የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሰላማዊ ሰዎች መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት "ተቀባይነት የለውም" አሉ

    የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ ማድረግ ሕገወጥ ነው አሉ። ፕሬዚዳንቱ አክለውም በኢራን ያለውን ጦርነት የሚያስቆመው “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ብቻ ነው” ብለዋል።

    አንቶኒዮ ኮስታ በኤክስ ገጻቸው ላይ “የሲቪሊያን መሠረተ ልማቶችን በስም ለመዘርዘር የኤነርጂ ተቋማትን፣ ዒላማ ማድረግ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

    የፕሬዚዳንቱ መግለጫ የተሰማው ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም የማይከፈት ከሆነ የኢራናውያንን መሠረተ ልማቶች እንደሚያወድሙ ከዛቱ በኋላ ነው።

    የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መስራች ዋና አቃቤ ሕግ ሉዊስ ሞሪኖ ኦካምፖ ቀደም ሲል ለቢቢሲ በኢራን የሚደረገው ጦርነት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ በሆነ መልኩ አንድ አገር ላይ ጥቃት የመክፈት ወንጀል ጋር ይስተካከላል ብለዋል።

    ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥሱ ነገሮችን ሲያደርጉ መመልከታቸውን በመግለጽ ያ "በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው" የሚገልጽ ግልጽ ደብዳቤ ፈርመዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ማርቭዳሽት የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ “በጠላት ጥቃት” ዒላማ ተደርጓል ሲሉ ዘግበዋል።

    የፋርስ ዜና ወኪል ጥቃቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን ዘግቧል።

    የታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ የማርቭዳሽት ካውንቲ አስተዳዳሪ ቢሮን ጠቅሶ በኢንዱስትሪው ላይ “ይህ ነው የሚባል ጉዳት አልደረሰም” ብሏል።

    ቀደም ሲል እስራኤል በደቡብ ኢራን በአሳሉያህ በሳውዝ ፓርስ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተናግራ ነበር።

  17. ዛሬ ሰኞ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ነገሮች

    • እስራኤል በአሳሉዬህ የሚገኘውን የኢራን ቁልፍ የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ መደብደቧን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ገለፁ።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን በርካታ የምርት ክፍሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ዘግበዋል፤ ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም።
    • እስራኤል ጥቃቱን የፈጸመችው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በኢራን መሠረተ ልማት ላይ ትልቅ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።
    • ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚያልፍበትን ሆርሙዝ እንደገና ካልከፈተች ማክሰኞ ዕለት "የኃይል ማመንጫ እና የድልድይ ቀን" ይሆናል ብለዋል።
    • ይህ በእንዲህ እንዳለ በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን፣ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የኢራን አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት ኃላፊን መግደሉን ተናግሯል።
    • በሰሜን እስራኤል አራት ሰዎች የኢራን ጥቃትን ተከትሎ ሲገደሉ በሊባኖስ የማያቋርጥ የውጊያ ጄቶች ድምፅ እየተሰማ መሆኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።
  18. እስራኤል የሄዝቦላህ አመራርን ለመግደል በፈጸመችው ጥቃት በስህተት ቡድኑን የሚቃወም ፖለቲከኛ ተገደለ

    እስራኤል እሁድ ዕለት በሊባኖስ የሄዝቦላህ አባልን ለመግደል ባደረገችው ሙከራ በስህተት ቡድኑን አጥብቆ የሚቃወም ከፍተኛ የፖለቲካ ቡድን መሪ ተገደለ።

    በጉዳይ ላይ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ጥቃቱ የታሰበውን ዒላማ መግደል እንዳልቻለ ገልጾ፣ በሲቪሎች ላይ “ለደረሰው ጉዳት መጸጸቱን" ገልጿል።

    በአብዛኛው ክርስቲያኖች በሆኑ ግለሰቦች የተዋቀረው የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ፣ በአንድ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር ፒየር ሞኡዋድን እና ባለቤቱን ፍላቪያን እንደገደለ አስታውቋል።

    የመኖሪያ ሕንጻው የሚገኘው ከቤይሩት በስተምሥራቅ በምትገኘው አይን ሳዴህ በምትባል በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች መኖሪያ በሆነችው ከተማ ውስጥ ነው።

    የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ጥቃቱ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶችን እንደገደለ አስታውቋል።

    የአካባቢው ከንቲባ ሟቾቹ ይኖሩ የነበረው ከዒላማው በታች ባለ አንድ ፎቅ ውስጥ ነበር ብለዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "በርካታ የማይመለከታቸው ግለሰቦች በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው መመልከት ችለናል" ብሏል።

    የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ ፒየር ሞአዋድ "ተዋጊም ሆነ ወታደራዊ ዒላማ አልነበረም" ካለ በኋላ ከአሰቃቂው ጥቃት በፊት ከቤተሰቡ ጋር የትንሳዔ በዓልን እያከበረ እንደነበር ተናግሯል።

    ፓርቲው ሄዝቦላህን አውግዞ ጥቃቱ የተከሰተው ወታደራዊ ግጭቶች ወደ መኖሪያ መንደሮች ዘልቀው እየመጡ በመሆናቸው ነው ብሏል።

  19. እስራኤል የኢራን ቁልፍ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካን መደብደቧን አስታወቀች

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በኢራን የፔትሮኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ላይ ድብደባ መፈጸሙን ገለጹ።

    ሚኒስቴሩ አክለውም ጦሩ “በሙሉ ኃይሉ” የኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንዲቀጥል ታዝዟል ብለዋል።

    “የእስራኤል መከላከያ በኢራን ግዙፉ የሆነውን እና [በአሳሉያህ] የሚገኘውን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽሟል ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በሌላ ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጨምረው ገልጸዋል።

    “ለኢራን የፔትሮኬሚካል የውጭ ንግድ በጥምረት 85 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል ስለዚህ አገልግሎት አይሰጡም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

    ካትዝ አክለውም በአሳሉያህ የሚገኘው ፋብሪካ የአገሪቱን ግማሽ የፔትሮኬሚካል ምርቶች የሚያመርት ነበር ብለዋል።

    ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ሁለት የፔትሮኬሚካል ኩባንያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዘግቧል።

    ካትዝ የኢራን ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሟን የገለጹት የፋርስ የዜና ወኪል በአሳሉያህ ከሚገኘው በሳውዝ ፓርስ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ብዙ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

  20. ኢራን በእስራአል ሃይፋ አካባቢ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

    የኢራን ሚሳዔል በሃይፋ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ አራት ሰዎች መግደሉ ተገለጸ።

    የጸጥታ አካላት ቦምቡ ከወደቀ በኋላ ባለመፈንዳቱ የሕይወት አድን ሠራተኞችን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ገልጸዋል።

    እንደ የእስራኤል ባለሥልጣናት ገለጻ በጥቃቱ የተመታው ቤት ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎችን ለማውጣት የጎረቤት ግድግዳን መሰርሰር አስፈልጎ ነበር።

    ጥቃቱ ከደረሰበት ሕንጻ ማዶ የምትኖረው ሞር ባረል፣ የእስራኤል በርካታ የአየር መቃወሚያዎች እያሉ እንኳን የኢራንን የሚሳዔል ጥቃት እያሰጉ መኖር በአደጋ የታጀበ ነው፤ ምናልባት ደህንነትህ የተጠበቀ ወይንም በማንኛውም ሰኮንዶች ለአደጋ እንደመጋለጥ ያለ የሕይወት ቁማር ነው ብላለች።

    እስራኤል የቴህራንን ባሌስቲክ ሚሳዔል መምታት በመቻሏ ውጤታማ አንደሆነች ብትገልጽም ኢራን ግን ዒላማ የምታደርገው የእስራኤልን የደህንነት ስሜት ነው ሲሉ ነዋሪዎቿ በምሬት ይናገራሉ።

    ያንን ደግሞ አንድ ሕንጻ ላይ በሚፈጸም ጥቃት መምታት ይቻላል ሲሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።