ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” - ፕሬዝዳንት ትራምፕ
ኢራን የቀረበላትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ "ሙሉ ስልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ይሞታል" ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቁ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሌሊት የሚጠናቀቀውን ለኢራን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ባለፉት ቀናት ሲሰጡ የነበረውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን አጠናክረው ደግመውታል።
ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባሰፈሩት መልዕክት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት ያበቃለታል” ሲሉ በኢራን ላይ ዝተዋል።
ትራምፕ ጨምረውም:
"ያ እንዲሆን አልፈልግም፣ ነገር ግን ሳይከሰት አይቀርም። ቢሆንም ግን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ እና አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ አለ፤ የተለዩ ብልህ እና ብዙም ጽንፈኛ ያልሆኑ የበላይነትን ይይዛሉ፤ ምናልባትም የሚያስደንቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ ማን ያውቃል?" በማለት ጽሁፋቸው ላይ የጠየቁት ትራምፕ ዛሬ ሌሊት ሊከሰት የሚችለውን አመልክተዋል።
"በዓለም ረጅም እና ውስብስብ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነውን ነገር ዛሬ ማታ የምናየው ይሆናል። የ47 ዓመታት ጭቆና፣ ሙስና እና ሞት በመጨረሻም ያበቃል። እግዚአብሔር ታላቁን የኢራን ሕዝብ ይባርክ!”
ትራም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ሃሳብን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ያበቃል።
ኢራን የተኩስ አቁም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት እና የሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላትን በመጠየቅ የራሷን ቅድመ ሁኔታዎች አቅርባለች።
በሌላ በኩል ደግሞ በፓኪስታን መሪነት ዲፕማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ በቀሩት ሰዓታት አንዳች ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ለስድስት ሳምንታት የተካሄደው ጦርነት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።