ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ አውዳሚ ጥቃት ይፈጸማልበማለት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በአንድ በኩል ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘው ጥቃታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ ኢራንም በእስራኤል እና በዙሪያዋ
ባሉ አገራት ላይ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ
ካልተከበረ ኢራንን “ወደ ድንጋይ ዘመን” ይመልሳታል ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ሰዓት እየተቆጠሩ ናቸው።
ይህ የኢራንን የሲቪል የኃይል ማመንጫ ተቋማትን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደርጋል የተባው የትራምፕ ዛቻ ተግባራዊ
የሚሆን ከሆነ “የጦር ወንጀል ነው” በማለት ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።
ይህ ሁሉ የጥቃት እና የውድመት ዜና እየተሰማ ባለበት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው።
በፓኪስታን መሪነት የሚደረገው ጥረት ወደ ወሳኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ፓኪስታን ጦርነቱን ለማብቃት በአሸማጋይነት “አዎንታዊ እና ውጤታማ ጥረት” እያደረገች መሆኑን በኢስላማባድ የኢራን አምባሳደር
ጠቅሰው በሂደቱም “ወሳኝ እና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ደረጃ ላይ እየተደረሰ” መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል አሜሪካ በአስቸኳይ ከተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣላችው ዕቀባ ካነሳች በኋላ
ቀጣይ የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ ሃሳብ ብታቀርብም፤ ኢራን ግን የራሷን የድርድር ሃሳብ በመቅረብ ውድቅ አድርጋዋለች።
ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት የተከፈተባት ጦርነት በዘላቂነት እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና በጥቃቱ ለደረሰባት
ውድመት የመልሶ ግንባታ ሃሳብን አቅርባለች።
እየተካሄዱ ያሉት ንግግሮች በፍጥነት ተቋጭተው በቀጣይ ሰዓታት ውስጥ ከስምምነት ካልደረሰ አሜሪካ ባላት ኃይል ሁሉ ኢራንን
ለማንበርከክ እርምጃ እንደምትወስድ፣ ኢራንም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ አጸፋ እንደምትመልስ እየዛቱ ነው።
ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ያሉት መጪዎቹ ሰዓታት ለኢራን ብቻ ሳይሆን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት
ብሎም ለመላው ዓለም መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች የሚተላለፉበት ሊሆኑ ይችላሉ።
መላው ዓለምም ምን ሊከሰት እንደሚችል በስጋት እና በጉጉት እየጠበቀ ነው።