ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ጀርመናውያን ወንዶች ከአገር ውጭ ለመቆየት ወታደራዊ ፈቃድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ወታደራዊ አገልግሎትን በሚያስተዋውቀው የጀርመን አዲስ ሕግ መሠረት ከ17 እስከ 45 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአገሪቱ ዜጋ ወንዶች፤ ከአገር ውጭ ለረዥም ጊዜ ለመቆየት ፈቃድ መጠየቅ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ተገለጸ።

በታህሳስ መጨረሻ ወደ ሥራ የገባው የወታደራዊ አገልግሎት ማዘመኛ ሕግ፤ ዩክሬንን የወረረችው ሩሲያ ስጋት መደቀኗን ተከትሎ የጀርመንን ጦር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተነግሯል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ፤ ዕድሜያቸው 17 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ከሦስት ወር በላይ በውጭ አገር ሲቆዩ ቅድመ ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው አረጋግጧል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የጉዞ ፈቃድ ሊኖር እንደሚገባ ቢገልጽም ሕጉ ቢጣስ ስለሚተገበርበት መንገድ ግን ግልጽ አይደለም።

ጉዳዩ አርብ ዕለት በፍራንክፈርተር ሩንድስቹ ጋዜጣ ላይ እስኪዘገብ ድረስ ፈቃድ የማግኘት ሕጉ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደንቡ "አስተማማኝ እና ትርጉም ያለው የወታደራዊ ምዝገባ ስርዓት ለማረጋገጥ" የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል። "ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ማን ለረዥም ጊዜ ከአገር ውጭ እንደሚቆይ ማወቅ አለብን" ብለዋል።

ይህ ሕግ በወጣቶች የሚያስከትለው ተጸዕኖ "እጅግ ሰፊ" ሊሆን እንደሚችል ያልሸሸገው መግለጫው፤ "አላስፈላጊ ቢሮክራሲን ለማስወገድ" ደንቦች እየተዘጋጁ መሆኑን አክሏል።

ለሕጉ መሠረት የሆነው በ1956 የወጣው የወታደራዊ ምዝገባ ሕግ ነው። ይህ ሕግ የታህሳሱን ጨምሮ በተደጋጋሚ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ከቅርብ ጊዜው ማሻሻያ በፊት በነበረው አሠራር መሠረት የተራዘመ የውጭ ቆይታ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ የሚተገበረው ጀርመን በብሔራዊ መከላከያ ወይም ጦሯን በማዝመት ሂደት ውስጥ ከሆነች ብቻ ነው።

የመከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣን ተመሳሳይ ድንጋጌ "በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም እና ምንም ተግባራዊ ጠቀሜታ ያልነበረው" መሆኑን ተናግረዋል።

የወታደራዊ አገልግሎት ማዘመኛ ሕጉ በ2035 የአገሪቱን ጦር ቁጥር ከ180 ሺህ አካባቢ ወደ 260 ሺህ ለማሳደግ ዕቅድ ይዟል።

በታህሳስ ወር የጀርመን ፓርላማ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የወታደራዊ አገልግሎት ማዘመኛ ሕግ ወደ ሥራ እንዲገባ ድምጽ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ከጥር ወር ጀምሮ ከ18 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ወደ ጦሩ ለመቀላቀል ስላላቸው ፍላጎት መጠይቅ ይላክላቸዋል።

ከሐምሌ 2027 ጀምሮ ደግሞ ጦርነት ቢቀሰቀስ ለአገልግሎት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን የአካል ብቃት ግምገማ ማድረግ አለባቸው።

ሴቶች ለወታደራዊ አገልግሎት በፈቃደኝነት ሊሳተፉ ቢችሉም በጀርመን ሕገ መንግሥቱ መሰረት እንዲያገለግሉ ሊገደዱ አይችሉም።

ዕቅዱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰጡ የሚተገበር ቢሆንም የፀጥታ ሁኔታው ​​ከተባባሰ ወይም በጣም ጥቂት በጎ ፈቃደኞች ብቻ ከመጡ የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ሊታሰብበት ይችላል።

ሕጉ በፓርላማ ሲፀድቅ ብዙ ወጣቶች ሕጉን በመቃወም ተቃውመዋል።