ህወሓት ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ የተቋቋመው "የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት" እንዲመለስ ወሰነ

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በ2012 ዓ.ም. በትግራይ ክልል በተካሄደው እና የፌደራል መንግሥት ውድቅ ባደረገው ምርጫ "የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" እንዲመለስ መወሰኑን አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ከተመለሰ በኋላ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመራው የክልሉ አስፈጻሚ አካል "አቃፊ ሆኖ እንዲቋቋም መግባባት ላይ መደረሱንም" ገልጿል።

ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲያካሂድ የነበረው ህወሓት ውሳኔውን ያስታወቀው እሁድ ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ባለ ሦስት ገጹ መግለጫ፤ የፌደራል መንግሥት በመጋቢት መጨረሻ የተጠናቀቀውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜ "ያለ ህወሓት ተሳትፎ" ማራዘሙን ይቃወማል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የሥልጣን ቆይታ ከሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸው ይታወሳል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህ እርምጃ የፕሪቶሪያ ስምምነትን "የጣሰ"፣ "ከድርጅታችን እውቅና ውጪ" የተላለፈ እና "የተናጠል ውሳኔ" ሲል ተቃውሞታል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ የተራዘመው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት የወጣን ሕግ በመጥቀስ" እንደሆነ በመግለጽ ተችቷል።

የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያ ስምምነትን "ሙሉ በሙሉ በሚንድ መልኩ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር ለማድረግ" እየተንቀሳቀሰ ነው ሲልም ከስሷል።

ወደ ትግራይ ክልል መላክ የነበረበት የድጎማ በጀት መቋረጡን የጠቀሰው ህወሓት፤ "ባጠቃላይ በትግራይ ላይ ዳግም እገዳ እና ከበባ በማድረግ፣ የጦር መሳሪያ እና ሜካናይዝድ አቅሙን ወደ ትግራይ በማስጠጋት ዳግም ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ ነው" ሲል የፌደራል መንግሥቱን ወንጅሏል።

በእነዚህ እርምጃዎች የተነሳም "ለትግራይ ህዝብ ህልውና እና ደኅንነት አደገኛ የሆነ ሁኔታ" እንደተፈጠረ ገልጿል።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ "የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት" መገምገሙን የጠቀሰው መግለጫው፤ በዚህ መነሻነት የቀድሞው "የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት" እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቋል።

"2.8 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ የመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ ወስኗል" ብሏል። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ "የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት እና የሕዝብ ውሳኔ ሰጪነት መገለጫ" ሲል የጠራው ይህ ምክር ቤት "ለሰላም ሲባል ወደጎን ተደርጎ" እንደነበር በመግለጫው ጠቅሷል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው "ወደ ሥራ እንዲመለስ" ውሳኔ ያስተላለፈለት ምክር ቤት የተቋቋመው የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ መራዘሙን የተቃወመው ትግራይ ክልል በ2012 ዓ.ም. በተናጠል ባካሄደው ምርጫ ነው።

በዚህ ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 190 ወንበሮች ውስጥ ውስጥ 152 ያህሉን ህወሓት ማሸነፉ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥት ከብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ውጪ የተካሄደውን ይህንን ምርጫ ውድቅ አድርጎታል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጷግሜን 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸና እና ተፈጻሚነት የሌለው" እንደሆነ ወስኗል።

ምርጫው ከሁለት ወራት በኋላ ለተነሳው የትግራይ ጦርነት ምክንያት ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ ተደርጎ የሚቆጠር ነው።

ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከመቋቋሙ አስቀድሞ ምክር ቤቱ የሕግ አውጪነት ሥልጣኑን በወቅቱ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ሲመራ ለነበረው አስፈጻሚ አካል ማስረከቡ ተገልጾ ነበር።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ምክር ቤቱ ወደ ሥራ እንዲመለስ የወሰነው ምርጫው ከተካሄደ ስድስት ዓመት ገደማ በኋላ ነው። ምክር ቤቱ ወደ ሥራው ከተመለሰ በኋላ አስፈጻሚው አካል "የመከተ አቅሞችን በሚያሳትፍ መልኩ አቃፊ ሆኖ እንዲቋቋም መግባባት ላይ" መደረሱን አስታውቋል።

መግለጫው "የመከተ አቅሞች" ሲል የገለጸው የትግራይ ኃይሎች አመራሮችን በአባልነት እንደያዘ የሚነገርነት የአመራር ውሳኔ ሰጪ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ከማዕከላዊው ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ በህወሓት ውሳኔዎች ላይ ስብሰባ ማድረጉን መግለጫው ጠቅሷል።

ሚያዝያ 9 እና 10/2018 ዓ.ም. በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ 'የመከተ አቅሞች ምክር ቤት' የህወሓትን "አጀንዳዎች የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን በመጨመር ለህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎች ያለውን ድጋፍ" እንደገለጸም አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, tplf

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከምክር ቤቱ ጋር በተያያዘ ካሳለፈው ውሳኔ በተጨማሪ "በትግራይ ሕዝብ እና በሌሎች ሕዝቦች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት" እንደተወያየ መግለጫው ያስረዳል። "ከየትኛውም ጊዜ በላይ ሕዝባችን ከጎረቤት ሕዝቦች፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች እና ከጎረቤት አገራት ሕዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች እንዲሰሩ ወስኗል" ብሏል።

አሁንም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ እና ህወሓት "ቢሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያሉትን ልዩነቶች በውይይት እና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ" መሆናቸውን ገልጿል። አክሎም ግን የክልሉ ሕዝብ "የትግራይ ሕዝብን ህልውና እና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተካሄደ ያለው ወሳኝ የትግል ምዕራፍ" ከህወሓት ጎን እንዲቆሙ ጠይቋል።

ይህንን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥትም ሆነ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት የለም። ከህወሓት በተቃራኒ የተሰለፉ የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች ግን ውሳኔው ጦርነት የሚቀሰቅስ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟቸውን አምተዋል።

ከእነዚህ አንዱ የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት በዚህ ውሳኔው "የፕሪቶሪያ ስምምነትን ውድቅ የሚያፈርስ ተግባራዊ እርምጃ ወስዷል" ብለዋል።

ጌታቸው፤ "የፕሪቶሪያ ስምምነትን እና ከጦርነት በኋላ የተረዘጋውን ደካማ ስርዓት የሚያፈርስ ማንኛውም የተናጠል ውሳኔ በክልላዊ ተዋናዮች መካከል ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከፌደራል መንግሥት ጋር እንደ አዲስ ግጭት እንዲቀሰቀስ የማድረግ ዕድል አለው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።