የኢራን ጦርነት መቼ ያበቃል? እየተቀያየረ ያለው የትራምፕ አስተዳደር የጊዜ ሰሌዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና ተሰናባቹ የአሜሪካ ሠራዊት ኤታማጆር ሹም ራንዲ ጆርጅ
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ዳፋ በርካታ አገራት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ጦርነቱ መቼ ያበቃል የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያካሄዱት ያለው ጦርነት ምን ያህል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል የቅርብ ጊዜ ግምገማቸውን አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ የካቲት ወር ላይ በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነቱን አስመልክቶ ረቡዕ ዕለት ምሽት በቴሌቪዥን የተላለፈው መግለጫቸው "በአጭር ጊዜ፣ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ" አሜሪካ በኢራን ወታደራዊ ዓላማዋን ለማሳካት መንገድ ላይ ነች ብለዋል።

ትራምፕ ጦርነቱ ዓመታት ከፈጀው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና የቬትናም ጦርነት በጣም አጭር እንደሆነ አሜሪካውያንን ያስታወሱ ሲሆን፣ አዲስ የጊዜ ሰሌዳቸውን አሳውቀዋል።

ኢራናውያንን "በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ሳምንታት ውስጥ ወደሚገባቸው የድንጋይ ዘመን እንመልሳቸዋለን" ብለዋል።

ይህ አስተያየታቸው ትራምፕ እንዲሁም የአስተዳደራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከሰጡት የጊዜ ሰሌዳ የራቀ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የካቲት ወር መገባደጃ ላይ ወታደራዊ ዘመቻቸውን ባሳወቁበት ወቅት "ግባችንን ለመምታት እስካስፈለገው ጊዜ ድረስ እንቀጥላለን" ነበር ያሉት።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ ፕሬዝዳንቱ አንድ ጊዜ አሜሪካ ጦርቱን አሸንፋለች፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ አሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻውን ለሳምንታት [ከሁለት እስከ ስድስት] ትቀጥላለች በሚሉ ሃሳቦች ውስጥ ሲዋልሉ ቆይተዋል።

የጦርነቱ ማብቂያ ተደርጎ የተገለፀው ስድስተኛ ሳምንት የሚያርፈው በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 11 ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች እንደሚሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግጭት የሚያበቃበትን የጊዜ መርሃ ግብር ማስቀመጣቸው የተለመደ ነው። ከዚያ ግን የጊዜ ሰሌዳቸውን ይለውጣሉ።

ሆኖም የትራምፕ አስተዳደር አካሄድ ልዩ እንደሆነ አንድ ባለሙያ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ቁርጥ ያለ ጊዜ አለማስቀመጡ ቴክኒካዊ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም "ለጠላቶቻችሁ ምን ልታደርጉ ወይም ላታደርጉ እንደምትችሉ አትንገሯቸው፤ መቼ ማቆም እንደምትፈልጉም ለጠላቶቻችሁ አትንገሯቸው" ብለዋል።

"ትራምፕ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት፤ ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንታት ብለዋል። የሆነ ውስን ጊዜ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በግልፅ ይህ ነው ብለን አንገልጽም ምክንያቱም ግባችን ዓላማዎቻችንን ማሳካት ነው። ለዚህም በጥሩ መንገድ ላይ ነን" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ግጭቱ በቀጠለበት ሌሎች በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጦርነቱ መቼ ሊያበቃ እንደሚችልም የራሳቸውን ትንበያ የሰጡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ከፕሬዝዳንቱ ሃሳብ ጋር የሚቃረኑ ይመስላሉ።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 8 የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት በሲቢኤስ ኒውስ የ60 ደቂቃ ፕሮግራም ላይ ሲናገሩ፣ እርምጃው ገና መጀመሩ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

24 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ "ውጊያውን ገና ጀመርን" ሲል ንግግራቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስተጋብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚያው ቀን በፍሎሪዳ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ወታደራዊ ግቦቿን ለማሳካት ወሳኝ ድሎችን እንደተቀዳጀች ገልጸው፤ "አንዳንድ ሰዎች ተጠናቋል ማለት ይችላሉ" ብለዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። አስተያየታቸው ብዙውን ጊዜ በትራምፕ እና በሄግሴት መካከል የሚያርፍ ነው።

ሩቢዮ፣ ትራምፕ ኢራንን በተመለከተ ከዋይት ሐውስ ከሰጡት መግለጫ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማክሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ"የመጨረሻውን መስመር ማየት እንችላለን። ዛሬ አይደለም። ነገም አይደለም። ግን እየመጣ ነው" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲገጥመው የመጀመሪያው የአሜሪካ አስተዳደር አይደለም።

አንዳንድ ጊዜ በፕሬዝዳንቱ የሚሰጡ የጊዜ መርሃ ሰሌዳዎች ግራ የሚያጋቡ፤ አንዳንዴ ደግሞ ውስን ናቸው። በእርግጥ የተወሰኑ ጦርነቶች የጦር አዛዦች ባስቀመጧቸው የጊዜ ገደብ ትንበያዎች ውስጥ ተጠናቅቀዋል።

በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የግጭት አፈታት እና ዲፕሎማሲ አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሪክ ሚን ግምቶች ብዙውን ጊዜ በእውነተኛ የጊዜ ሒደቶች ይቀያየራሉ ይላሉ።

"ጦርነቶች መቼ ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ማወቅ አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 1967 ፕሬዝዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን የቬትናም ጦርነትን ለማጠናቀቅ "ከጫፍ መድረሳቸውን" ተናግረው ነበር። ግልጽ ያልሆነው ንግግራቸው በአገሪቱ ያሉትን የግጭቱን ተቃዋሚዎች ለማስደሰት ያለመ ነበር።

ሆኖም ሃሳባቸው አልተሳካም፤ ጦርነቱ ለተጨማሪ ስምንት ዓመታት ዘልቋል። ይህም ጆንሰን በአገር ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ያሳጣ ሲሆን፣ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንዳይመረጡ ምክንያት ሆኗል።

ከአስርተ ዓመታት በኋላ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን በ1999 የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በዩጎዝላቪያ ላይ የወሰደው የቦምብ ድብደባ ዘመቻ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ተናግረው ነበር። ሆኖም የአየር ድብደባው ከሁለት ወር በላይ የዘለቀ ሲሆን፣ ይህም በርካቶች ከገመቱት በላይ የረዘመ ነበር።

ከዚያም ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የኢራቅ ጦርነት ከተጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ "ተልዕኳችን ተሳክቷል" ብለው ነበር። የአሜሪካ ጦር ግን እስከ አውሮፓውያኑ 2011 ድረስ ከኢራቅ ሳይወጣ ቆይቷል።

በሃርቫርድ ኬኒዲ ስኩል የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ቶማስ ፓተርሰን "ፕሬዝዳንቶች ብዙውን ጊዜ የሕዝብን ጊዜ ለመግዛት ሲሉ የጊዜ ሰሌዳ ያቀርባሉ። እናም ሁሉም ጊዜውን አሳንሰው ነው የሚያዩት" ብለዋል።

አሁንም ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አማካሪዎቻቸውን የጊዜ ሰሌዳቸውን እና የጦርነቱን ምክንያት በመለዋወጣቸው ኢራን ጎልታ ወጥታለች ብለዋል አንድ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ።

"በአስተዳደሩ ውስጥ ያለው አቋም የተለያየ እና ወጥነት የሌለው ነው። በዚህ ላይ ላስበው የምችለው ምንም ዓይነት ተመሳሳይ ታሪክ የለም" ብለዋል ሚን።

ዋይት ሐውስ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶችን ያስተባበለ ሲሆን፣ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ካሮላይን ሊቪት ባለፈው ወር "ትራምፕ እና ሙሉ ቡድናቸው ግልፅ ሆነ፣ ወጥነት ያለው ዓላማ አስቀምጠዋል" ብለዋል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ለአሜሪካ ሕዝብ ደያረጉት ንግግር በከፍተኛ ሁኔታ የተጠበቀ ነበር። ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ ጦርቱን በተመለከተ በሚሰጡት የመጀመሪያ መግለጫ ላይ ወሳኝ ዜናዎችን ይናገራሉ ተብሎ ነበር።

በዋሽንግተንም ትራምፕ የምድር ጦር ወደ ኢራን እየላኩ እንደሆነ ወይም ጦርነቱን ሊያቆሙ ይችላሉ የሚሉ ግምቶች ነበሩ።

ሆኖም ትራምፕ በምትኩ አዲስ የጊዜ ሰሌዳ ነበር ያቀረቡት።