በሕንድ በኮቪድ ወቅት እስር ቤት ውስጥ ከሞቱ ሰዎች ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ፖሊሶች ሞት ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሕንድ እአአ በ2020 አባትና ልጅ በእስር ቤት ውስጥ በመሞታቸው የተነሳ ዘጠኝ የፖሊስ መኮንኖች የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው።
የ58 ዓመቱ ፒ ጄያራጅ እና የ38 ዓመቱ ልጁ ቤኒክስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የእንቅስቃሴ ገደብን በመጣስ የሞባይል ስልክ ሱቃቸውን ክፍት አድርገው በመገኘታቸው ከታሰሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።
በደቡባዊ የታሚል ናዱ ግዛት እስር ቤት ሕይወታቸው ያለፈው አባት እና ልጅ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እጃቸው ታስሮ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል ሲሉ ጉዳያቸውን የተመለከቱት ዳኛ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
ዳኛው አክለውም የፖሊስ ተግባር በግልጽ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም እንደሆነ ገልጸዋል።
"ይህንን ያደረጉት ሆን ብለው ለመግደል በማሰብ ነው" ብለዋል።
ባለፈው ወር በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ፖሊሶች ይግባኝ መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል።
ዳኛው የፍርድ ውሳኔውን በሰጡበት ወቅት "ያልታጠቁ ሰዎችን አጥቅተዋል። ይቅርታ ሊደረግላቸው አይገባም። በእድሜያቸው ወይም በቤተሰባቸው ምክንያት ቅጣታቸው እንዲቀልላቸው ሊደረግ አይገባም። ሁሉም የተማሩ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
አባት እና ልጅን በጭካኔ በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት በአጠቃላይ አስር የፖሊስ መኮንኖች ቢሆኑም ከተከሰሱት መካከል አንዱ እአአ በ2020 በኮቪድ ምክንያት ሞቷል።
ጉዳዩ በታሚል ናዱ ተቃውሞ ያስነሱ ሲሆን የግዛቲቱ የተቃዋሚ ፓርቲ የሕግ አውጪዎችም ወደ ጎዳና ከወጡት መካከል ይገኙበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራሁል ጋንዲ እና የሕንድ የክሪኬት ኮከብ ሺካር ዳዋን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለሁለቱ ሰዎች ፍትህ እንዲሰጣቸው ከጠየቁት መካከል ይገኙበታል።
የሟቾቹ ግለሰቦች ታሪክ በሕንድ ስላለው የፖሊስ ጭካኔ ዳግም መወያያ እንዲሆን አድርጓል።
የመብት ተሟጋቾች በሕንድ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ ይሞታሉ ይላሉ። የተጠርጣሪዎቹን ቃል ለመቀበል የሚደረግ ማሰቃየት እና ድብደባ የፖሊስ የተለመደ አሰራር ሆኗል ሲሉ ኮንነዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በርካታ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ሕንድ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች ጋር በሚስማማ መልኩ የፖሊስ አገልግሎትን ዘመናዊ ለማድረግ ዋና ዋና ማሻሻያዎችን እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።















