ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ያለፈችው ኤርትራ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ቀሩ

የፎቶው ባለመብት, ENFF

የምስሉ መግለጫ, ለውድድሩ ከኤርትራ ከሄዱት 10 የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ሰባቱ ሳይመለሱ ቀርተዋል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ኢስዋቲኒን 4 ለ1 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ከ18 ዓመታት በኋላ ኤርትራን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ውድድር ካበቁት ተጫዋቾች መካከል ሰባቱ ወደ አገራቸው አለመመሳቸውን ምንጮች ለቢቢሲ አረጋገጡ።

በቅድመ ማጣሪያው ሁለት ዙር ጨዋታ ከተሳተፉት የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አባላት መካከል አስሩ ከአገር ውስጥ የተመረጡ ተጫዋቾች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 14ቱ ደግሞ በባሕር ማዶ የሚኖሩ ኤርትራውያን ናቸው።

ከአገር ውስጥ ከተመረጡት ከተመረጡት አስር ተጫዋቾች መካከል ከውድድሩ በኋላ ሰባቱ ወደ አገራቸው አለመመለሳቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከ18 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ድልድል የተመለሰው የኤርትራ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሁለት ዙር ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ኢስዋቲኒን (የቀድሞዋ ስዋዚላንድ) በመግጠም ነው በሁለቱም ጨዋታ ለማሸነፍ የቻለው።

የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ በደጋፊዎቹ ፊት በአገር ውስጥ በዋና ከተማዋ አሥመራ መጫወት የነበረበት ቢሆንም ጨዋታው የተካሄደው ግን በሦስተኛ አገር ወስጥ ነበር።

ቡድኑ በአሥመራ ስላልተጫወተበት ምክንያት ይፋዊ ምክንያት ባይገለጽም በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ስታዲየሞች ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ደረጃ በታች በመሆናቸው እንደሆነ ግን ሲነገር ቆይቷል።

የቀይ ባሕር ግመሎች በመባል ከሚታወቁት የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አባላት መካከል አብዛኞቹ ወደ አገራቸው አልተመለሱም።

ከአስሩ ተጫዋቾች መካከልም ሦስቱ እነሱም የቡድኑ አምበል አብለሎም ተክለዝጊ፣ የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ሄኖክ ታደሰ እና ሮሜል አብዱ ብቻ መመለሳቸውን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በደቡብ አፍሪካ እንደቀሩ ከሚነገርላቸው ተጫዋቾች መካከል አንጋፋው የክንፍ ተጫዋች ሮቤል ረዲ፣ ወደብ ፍሰኻዬ እና የደንደን እግር ኳስ ቡድን የግብ ጠባቂ ክብሮም ሰለሞን ይገኙበታል።

ሮቤል ረዲ ከኢስተዋቲኒ ጋር ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ በተለይ በሁለተኛው ጨዋታ ወቅት የአሊ ሱሌማንን ሁለት ጎሎች አግዟል።

ስለቀሩት ሰባት ተጫዋቾች ከኤርትራ ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ወይም ከኤርትራ መገናኛ ብዙኃን ምንም ዓይነት መረጃ አልተሰጠም።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ለኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ ቢያርብም ምላሽ አላገኘም።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የተጓዙት የኤርትራ ስፖርት እና ባህል ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ድራር ፍሰሃዬ ከሦስት ቀናት በፊት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ቡድኑ በካይሮ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ አባላት እና በግብፅ ካለው የኤርትራ ማኅበረሰባቸው ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለታል ብለው ነበር።

ነገር ግን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ባጋሯቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ውስጥ የሚታዩት ሁለት ተጫዋቾች ሔኖክ እና ሮሜል ብቻ ናቸው።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በይፋዊ ድረ ገጹ ወደ አገራቸው ስላልተመለሱት የእግር ኳስ ቡድኑ ተጫዋችች ምንም ያለው ነገር የለም።

በኤርትራ አትሌቶች እና ተጫዋቾች አሸንፈው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሕዝቡ በተገኘበት አቀባበል ማድረግ የተለመደ ነው።

ቢቢሲ በአሥመራ የሚገኙ ምንጮቹን አነጋግሮ እንዳረጋገጠው አብዛኞቹ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አባላት ወደ አገራቸው ባለመመለሳቸው የተነሳ ይህ አቀባበል አልተደረገላቸውም።

የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች መካከል የአንዱ እህት ወንድሟ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ እንደሚገኝ ለቢቢሲ አረጋግጣለች።

የኤርትራ እግር ኳስ ተጫዋቾች ለውድድር በሄዱበት አለመመለስ ያልተለመደ ክስተት አይደለም ከዚህ በፊትም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ለውድድር የሄዱ ተጫዋቾች በዚያው ቀርተዋል።

ኤርትራ ለስምንት ዓመታት ከፊፋ እና ለ18 ዓመታት ደግሞ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ውጪ ሆና ቆይታለች።

በፊፋ አገራት ደረጃ ሰንጠረዥ 184ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኤርትራ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጥቂት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያከናወነችው።

ኤርትራ ብሔራዊ ቡድኗን ለማጠናከር ግብፃዊ አሠልጣኝን ወደ ቡድኗ ያካተተችው በቅርቡ ነበር።

በምሥራቅ አፍሪካ አገራት በጥምረት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ያለፈው ያለፈው የኤርትራ ብሔራዊ አብዛኞቹን ተጫዋቾች በማጣቱ በውድድሩ ውስጥ ስለመቀጠሉ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።