ኤርትራ ከ19 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል አለፈች

የፎቶው ባለመብት, ENFF
ኤርትራ ከ19 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል መካተቷን አረጋገጠች።
በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ፤ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ኢስዋቲኒን 4 ለ 1 በሆነ ድምር ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በደርሶ መልስ ጨዋታው ለግብጹ ካራባ ኢስላሚያ የሚጫወተው የቀድሞው የሐዋሳ ከነማ አጥቂ አሊ ሱሌማን ሦስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ለውድድሩ የሚመጥን ሜዳ የሌላቸው የቀይ ባሕር ግመሎቹ፤ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሞሮኮ ላይ ማከናወናቸው ይታወሳል።
በጨዋታው አሊ ሱሌማን እና ለሼፊልድ ዩናይትድ የሚጫወተው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ወጣት ቡድን ተጫዋች ሴም ኢዮብ-አብርሃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሁለት ለምንም ማሸነፍ ችለዋል።
ኢስዋቲኒ ላይ በተደረገው የመልስ ጨዋታ ኤርትራ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ በቅታለች።
በፊፋ አገራት ደረጃ ሰንጠረዥ 184ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኤርትራ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጥቂት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያከናወነችው።
ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተችው እአአ በ2007 ከአሁኗ ተጋጣሚዋ ኢስዋትኒ ጋር ነበር።
ብሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ሌሴቶ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ማጣሪያውን አልፈው ለምድብ ድልድል የበቁ አገራት ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትላንት ባከናወነው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በድሬዳዋ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የዋልያዎቹን ብቸኛ የማሸነፊያ ግብ ቸርነት ጉግሳ በመጀመሪያው አጋማሽ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በድምር ውጤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን 4 ለ 0 አሸንፏል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ላይ መካተት ችላለች፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከዓመታት በኋላ በሜዳው ያደረገው ጨዋታ ሆኗል።
ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት የምድብ ጨዋታዎች ከመስከረም ጀምሮ የሚከናወን ይሆናል።
የ2007 የአፍሪካ ዋንጫን ኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ በጋራ ያዘጋጁታል። ውድድሩ በሦስት አገራት አዘጋጅነት ሲከናወን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።












