የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ የመንግሥት ሠራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ የአንዳንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሠራተኞች ተናገሩ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሠራተኞች በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት የተነሳ የመንግሥት ሠራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ መጋቢት 15/2018 ዓ.ም. የድርጅቱ ሠራተኞች ለሆኑ የሠራዊት አባላት እና ሲቪሎች በሙሉ "በሁለት ቀናት ውስጥ" እረፍት እንዲወጡ ማዘዙንም ቢቢሲ ከተመለከተው ማስታወቂያ መረዳት ችሏል።
የኢንጂነሪንግ አንዱስትሪው "ላልተወሰነ ጊዜ ቅዳሜ ቀን" ሥራ እንደማይኖርም በማስታወቂያው ላይ ለሠራተኞቹ አስታውቋል።
ቢቢሲ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱን ከድርጅቱ ሠራተኞች ያረጋገጠው ማስታወቂያ በኢንዱስትሪ ግሩፑ ስር የቢሾፍቱ ሞተር ቬሄክል ኢንጂነሪንግ "በነዳጅ ዋጋ ግሽበት ምክንያት" ሁሉም የሠራዊቱ አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ ያዝዛል።
ኢንዱስትሪው ሠራተኞቹ ማስታወቂያው በተለጠፈበት ዕለት እና በማግሥቱ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም. ያላቸውን "የ2016 እና የ2017 ዓ.ም. ፍቃድ" እንዲወጡ አሳስቧል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኢንዱስትሪው ሠራተኞች "ከጥቂት አስፈላጊ ሠራተኞች በስተቀር" ሁሉም እረፍት መውጣታቸውን አረጋግጠዋል።
የኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪው አክሎም "የሥራ ሁኔታው ታይቶ የ2018 ዓ.ም." የዓመት ፈቃድ ያላቸው ሠራተኞችም እረፍት እንዲወጡ "በጥብቅ" አሳስቧል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመት በመዘጋቱ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች የትራንስፖርት ዘርፍ ላይም ማነቆ ሆኗል።
በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መቸገራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እና ሐዋሳ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ለመኪኖቻቸው ናፍጣ ለመቅዳት እስከ ሦስት ቀናት ድረስ በነዳጅ ማደያዎች ዙሪያ በመሰለፍ ለመጠበቀቅ መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ ተማሪዎችን የሚያመላልሱ፣ ወደ አዲስ አበባ ለተለያዩ ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች መቸገራቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ይህ እጥረት ወደ ቤንዚን ይሸጋገራል የሚል ስጋት መኖሩንም የተሽከርካሪ ባለቤቶች ጨምረው ገልጸዋል።
መንግሥት የሕዝብ ተቋማት እና በመንግሥተ ስር የሚተዳደሩ ድርጅቶች ወሳኝ ያልሆኑ ሠራተኞችን የነዳጅ እጥረትን ለመቅረፍ በሚል እረፍት እምዲወጡ እያደረገ መሆኑን የተያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ አሽከርካሪዎች ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት የተነሳ ከፍተኛ መጉላላት እንደገጠማቸው እና የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች ለመቀነስ መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እና ሐዋሳ በነዳጅ መቅጃ ስፍራዎች ረዣዥም ሰልፎች እንደሚታይ ለቢቢሲ አስተየየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች "ሰልፉ አንዳንዴ ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል" ብለዋል።
ዛሬ ሰኞ ማለዳ ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰጠ አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ የሚኖር አሽከረካሪ "እኔ ዕድለኛ ነኝ፤ ትናንት [እሁድ] ከቀን 6 ሰዓት ላይ የያዝኩት ሰልፍ ዛሬ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ደርሶኛል" በማለት ነዳጅ ማግኘቱን ተናግሯል።
የነዳጅ እጥረቱን ለመቅረፍ ታስቦ እየተወሰደ ባለ እርምጃ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ መንግሥት "ወሳኝ ያልሆኑ ሠራተኞችን" የዓመት እረፍታቸውን እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦች ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ ወላጆችም የነዳጅ እጥረቱ የተማሪዎች መጓጓዣ ላይም ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።
"ልጆቻቸውን ራሳቸው እንዲወስዱ የተነገራቸው ወላጆች እንዳሉ ሰምቻለሁ" ያለ አንድ አሽከርካሪ ናፍጣ ማግኘት "ለሁላችንም እጅግ ከባድ ሆኗል" ብሏል።
ቢቢሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተመከለታቸው አሽከርካሪዎች የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ አትክልት እና ፍራፍሬ ጭነው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ አይሱዙዎች ናፍጣ ለመሙላት ለቀናት በነዳጅ ማደያዎች ለመቆም በመገደዳቸው የተነሳ ጭነቶች እየተበላሹ መሆኑን ከምሥል ጋር ሲናጋሩ ያሳያል።
በተለይ ቲማቲም፣ ፓፓያ እና ሙዝ ጭነው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች የሚጓዙ አይሱዙዎች በዚህ የተነሳ ሥራቸውን ለመሥራት መቸገራቸውን እና የገበሬውን ምርት ለሸማች ማድረስ አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
የአይሱዙዎች የነዳጅ ታንከራቸው 100 ሊትር አካባቢ እንደሚይዝ የሚናገሩት እነዚህ አሽከርካሪዎች ይህ ነዳጅ አትክልት ይዘው ከሚያደርሱበት ከተማ የማድረስ አቅም እንደሌለው በማኅበራዊ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ተጨማሪ የነዳጅ መያዣ (ሳልቫቲዮ) ያላቸው ተሽከርካሪዎች እንዲያነሱ እና በፋብሪካው የተገጠመውን ብቻ እንዲጠቀሙ ማዘዙ ይታወሳል።
ለቀናት ነዳጅ ለማግኘት በመንገድ ለመቆም ተገድደናል የሚሉት እነዚህ አሽከርካሪዎች በዚህም የጫኑት አትክልት ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን በምሥል አስደግፈው ተናግረዋል።
አሁን ላይ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ጭነትን የሚያመላልሱ የአይሱዙ ሹፌሮች አትክልት ለመጫን ፍላጎት እያጡ መሆኑን በመግለጽ ይህም ገበሬዎችንም ሆነ ነጋዴዎችን ለኪሳራ እንደሚዳርግ በማኅበራዊ ገጾቻቸው ላይ አጋርተዋል።
በኢራን ጦርነት የተነሳ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋትን ተከትሎ በዓለም ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
በተጨማሪም በጦርነቱ የኢራን እና የሌሎች የመካለኛው ምሥራቅ አገራት የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ጥቃት እየፈጸመችባቸው ነው።
በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት በበርሜል 120 ዶላር ገብቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የፋይናንስ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤቤ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም ሕብረተሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን "በከፍተኛ ቁጠባ" እንዲጠቀሙ አሳስበው ነበር።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከመጋቢት 8/2018 ዓ.ም. የነዳጅ አቅርቦት ለፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲሰጥ ያዘዘ ሲሆን፣ የነዳጅ ሥርጭቱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።
በዓለም ዙሪያ የነዳጅ እጥረት ባስከተለው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት የተለያዩ አገራት የነዳጅ እጥረትን ለመቋቋም የነዳጅ ፍጆታቸውን የሚቀንሱ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው።
በዚህም መሠረት አንዳንድ አገራት የሥራ ቀናት መቀነስ፣ ሕዝቡ የሕዝብ ትራንስፖርትን እንዲጠቀም፣ አምራች እና የንግድ ተቋማት የሥራ ጊዜያቸውን እንዲቀንሱ እያደረጉ ነው።















