ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ብትዘጋ በቀሪው ዓለም ላይ ምን ሊከሰት ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / Getty Images
እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈቱትን መካከል ጥቃት ተከትሎ ኢራን የዓለም ወሳኙ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነውን የሆሙዝ የባሕር ሰርጥን ትዘጋለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የምድራችን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በዚህ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ስፋት ባለው፣ በጣም ጠባብ በሆነው ሰርጥ በኩል ነው የሚያልፈው።
ጠቅላይ መሪዋን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣኖቿ የተገደሉባት ኢራን ጠላት በምትላቸው አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ ተጽእኖዋን ለማስፋት የባሕር ሰርጡን ልትዘጋ ትችላለች።
የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ድርጅት ኤምአይ6 ኃላፊ ሰር አሌክስ ያውንገር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የከፋው ሁኔታ ሰርጡ ሊዘጋ ይችላል።
"ሰርጡን መዝጋት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተግዳሮት እንደሚሆን ግልጽ ነው" ይላሉ።
በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ምን ያህል ነዳጅ ያልፋል?
የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር (ኢአይኤ) በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳለፈ ይገምታል።
ይህም በዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይተላለፋል ማለት ነው።
በባሕር ሰርጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየትን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም ወዲያውኑ በዓለም ዙሪያ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል።
ነገር ግን ተንታኞች ግጭቱ እየተባባሰ የሚሄድ እና የሚራዘም ከሆነ የበለጠ ከባድ መዘዝ ይኖረዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ ከባሕረ ሰላጤው አገራት በሚገባ የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ በሆኑት ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ሊኖረው ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Stocktrek / Getty Images
የሆርሙዝ ሰርጥ ምን ያህል ጠባብ ነው?
የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኝ መተላለፊያ ወሽመጥ ነው። መግቢያው እና መውጫው 50 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በመሃል ላይ ደግሞ በጣም ጠባብ የሆነው ቦታ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።
ሰርጡ በማዕከላዊው ክፍል ብቻ ትላልቅ መርከቦች ለማሳለፍ የሚሆን ጥልቀት አለው።
የባሕር አሳሾች መግቢያ እና መውጫው ለትልልቅ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በመካከልም ክብደት ያለውን ነዳጅ ጭነው ለሚጓዙ ምቹ መሆኑን ይገልጻሉ።
እነዚህ ግዙፍ መርከቦች ወደ 10 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው የሰርጡ ክፍል ላይ መቅዘፍ ይኖርባቸዋል።
ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሲያልፉ በኢራን እና በአረብ አገራት መካከል አወዛጋቢ በሆኑት የቱንብ ደሴቶች አቅራቢያ ያልፋሉ።
በሰርጡ ላይ የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን የሚያስተጓጉሉ ካሉ ወታደራዊ እርምጃ ከግምት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ድረስ በተካሄደው የኢራን እና የኢራቅ ጦርነት ወቅት ተከስቷል።

ወታደራዊ እርምጃ?
ተንታኞች እንደሚሉት ለኢራን የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥን መዝጋት እንደ "መከላከያ ኃይል" በመጠቀም፣ ልክ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከመያዝ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢራንን ወታደራዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር ለረጅም ጊዜ ሲቃወም እንደነበረው ሁሉ፤ ታላላቅ አገራት ቴህራን ያላትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ተጠቅማ የዓለምን የኃይል አቅርቦት እንድታንቅ እንደማይፈቅዱ ደጋግመው ሲገልጹ ተሰምተዋል።
ብዙውን ጊዜ ኢራን የባሕር ሰርጡን ለጊዜው ልትዘጋው እንደምትችል ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
ነገር ግን ብዙዎች ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ወታደራዊ መንገዶችን በመጠቀም የባሕር መስመር ፍሰቱን በፍጥነት ወደ ነበረበት ሊመልሱት እንደሚችሉ እርግጠኞች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን እንዴት ልትዘጋው ትችላለች?
በአውሮፓውያኑ 2012 የአሜሪካ ኮንግረስ የምርምር አገልግሎት ባደረገው ጥናት መሠረት ኢራን ሰርጡን ለመዝጋት አዝጋሚ አካሄድን ልትከተል ትችላለች።
ይሆናሉ ተብለው የተዘረዘሩት እርምጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ።
- ጥሰት የሚያስከትለውን መዘዝ በግልፅ ሳይገልጽ በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ መንቀሳቀስን ማገድ
- በሰርጡ የሚያቋርጡ መርከቦች ሊፈተሹ ወይም ሊያዙ እንደሚችሉ ማወጅ
- በመርከቦች ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መክፈት
- የተወሰኑ መርከቦችን በወታደራዊ ኃይል ዒላማ ማድረግ
- በባሕር ሰርጡ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የባሕር ውስጥ ፈንጂዎችን ማጥመድ
- የንግድ እና ወታደራዊ መርከቦችን ዒላማ ለማድረግ ሰርጓጅ መርከቦችን እና ሚሳዔሎችን መጠቀም
በኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ወቅት ኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ሚሳዔሎችን የተጠቀመች ሲሆን፣ በባሕረ ሰላጤው ላይ የባሕር ውስጥ ፈንጂዎችንም አጥምዳለች።
ከእነዚህ ፈንጂዎች መካከል አንዱ ዩኤስኤስ ሳሙኤል ቢ ሮበርትስን የተባለውን መርከብ በመምታቱ አሜሪካ በምላሹ ወታደራዊ እርምጃ ወስዳለች።
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ሳትችል የቀረች ቢሆንም፤ የመርከብ ኢንሹራንስ ክፍያን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
ከዚህም በተጨማሪ በባሕረ ሰላጤው መውጫ ላይ መጨናነቅ በመፈጠሩ መርከቦች ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገውም ነበር።
የኢራን ወታደራዊ አቅም
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኢራን በኩል ስጋት ብለው ከሚጠቅሷቸው ወታደራዊ ተቋማት መካከል አንዱ የኢራን ባሕር ኃይል ነው።
ባሕር ኃይሉ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ያለው የጎላ ሚና ከበላይ መሪዎችን መመሪያ ተከትሎ በሰርጡ ላይ አስፈላዊውን እርምጃ የመውሰድ አቅም አለው።
የኢራን መሪዎችም ባሕር ኃይሉ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በአካባቢው የእስላማዊ ሪፐብሊኩ በጣም ወሳኝ እና አስተማማኝ የመከላከያ ኃይል እንደሆነ በኩራት ይናገራሉ።
የባሕር ኃይሉ 10 ኪሎ ሜትርን ከሦስት ደቂቃ በታች መጓዝ የሚችሉ ባለከፍተኛ ፍጥነት ሚሳዔል ማስወንጨፊያ መርከቦች ባለቤት መሆኑ ደግሞ በሆርሙዝ ሰርጥ ያለውን ሁኔታ አስጊ ያደርገዋል።
ባሕር ኃይሉ ያሉት ፈጣን ጀልባዎች፣ ከባድ የውጊያ መርከቦች እና ሚሳዔሎች በመከላከል እና በማጥቃት ወቅት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
በተጨማሪም ከባሕሩ ስር የሚጠመቀዱ ፀረ መርከብ ፈንጂዎች በባሕር ኃይል ጦርነት ወቅት በጣም ወሳኝ የሆኑ እና ኢራን ሰርጡን ለመዝጋት ከቆረጠች እና ጥቅም ላይ ካዋለቻችው ከፍተኛውን አደጋ የሚደቅኑ አውዳሚ መሳሪያዎች ናቸው።
እንዲሁም የኢራን ባሕር ኃይል ሰው አልባ አውሮፕላኖች በባሕር ላይ በሚሸፍኑት ክልል፣ በአቅም እና ተልዕኮን በተሳካ ሁኔታ በመፈጸም በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ሚና አላቻው።

የፎቶው ባለመብት, Norbert Schiller via Getty Images
ተንታኞች ምን ይላሉ?
በየቀኑ ከአንድ መቶ በላይ ከባድ መርከቦች በሚመላለሱበት የሆርሙዝ ሰርጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ኢራን ልትወስድ የምትችለው ውጤታማ እርምጃ ከባድ ጉዳትን ሊያስከትል የሚችል ነው።
ይህም ፈጣን ጥቃት የሚያደርሱ ጀልባዎችን እና የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን በመጠቀም ፈንጂዎችን ማጥመድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
የኢራን መደበኛ የባሕር ኃይል እና የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል በሌላ አገራት የጦር እና የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ።
ሆኖም ኢራን ትላልቅ ወታደራዊ መርከቦች የምታሰማራ ከሆነ በቀላሉ የእስራኤል ወይም የአሜሪካ የአየር ጥቃቶች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ።
የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ብዙውን ጊዜ ፀረ መርከብ ሚሳዔሎች የታጠቁ ሲሆኑ፣ አገሪቱ ከፊል ሰርጓጅ መርከቦችን እና ሰርጓጅ መርከቦችንም ትጠቀማለች።
የሳተላይት ምሥሎችን የኢራን ወታደራዊ መርከቦች በአገሪቱ ደቡባዊ የባሕር ጠረፍ አካባቢ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ያሳያሉ።
የበለጠ የሚጎዱት አገራት የትኞቹ ናቸው?
ቮርቴክሳ የተሰኘው ድርጅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ሳዑዲ አረቢያ በቀን 6 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ በኩል ወደ ውጭ ትልካለች።
ይህም ከየትኛውም የአካባቢው አገር ይበልጣል።
ቻይና፣ ሕንድ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚያልፍ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከሚያስገቡት መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር በ2022 ወደ 82 በመቶ የሚጠጋ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች በባሕር ሰርጡ አልፈው ወደ እስያ አገራት ተጓጉዘዋል ብሏል።
የዜና ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የደቡብ ኮሪያን 60 በመቶ ያህል የነዳጅ ዘይት አቅርቦት በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ በኩል የሚያልፍ ነው።
አሜሪካም በየቀኑ ወደ 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና ሌሎች ማዕድናትን በባሕር ሰርጡ በኩል ታጓጉዛለች።
ይህም በግምት በጠቅላላው ከምታስገባው ነዳጅ ዘይት 11 በመቶው ሲሆን፣ የፍጆታዋ ደግሞ 3 በመቶው ይሆናል።
በባሕር ሰርጡ በኩል የሚጓጓዘው የአውሮፓ አገራት ነዳጅ ዘይት ድርሻ በቀን ከ1 ሚሊዮን በርሜል ያነሰ ነው።
ከዚህ አንፃር ሲታይ ሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ቢዘጋ በዋናነት የሚጎዱት ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ይልቅ የአረብ እና የእስያ አገራት ናቸው።
በርካታ የእስያ አገራት ከኢራን ጋር ጥሩ ወይም የቅርብ ሊባል የሚችል ግንኙነት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, CFOTO / Future Publishing via Getty Images
የቻይና ተጽእኖ
ቻይና በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ ከሚያልፍ የነዳጅ ዘይት ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች። ከፍተኛ መጠን ያለውን የነዳጅ ዘይት ኢራን ለቻይና ከዓለም የገበያ ዋጋ በታች ትሸጥላታለች።
ይህም በአሜሪካ ማዕቀቦች የተሽመደመደውን ምጣኔ ሀብቷን ለማገዝ ረድቷታል።
ቤይጂንግ ዋነኛ የኢራን ነዳጅ ዘይት ተጠቃሚ እንደመሆኗ መጠን የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ወይም የመርከብ መስመሮችን መቋረጥን አትቀበልም።
ቻይና የዚህን ወሳኝ መስመር መዘጋትን ለመከላከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን እንደምትጠቀም ይጠበቃል።
የኢነርጂ አማካሪ የሆኑት አናስ አልሃጂ ለሲኤንቢሲ እንደተናገሩት የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ መዝጋት ከጠላቶቿ የበለጠ የኢራን አጋሮችን ይጎዳል።
"መጀመሪያ ራሳቸውን [ኢራናውያንን] የሚጎዳ ነገር ማድረግ አይፈልጉም" በማለት ኢራን መተላለፊያውን አትዘጋም የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አማራጭ የጉዞ መስመሮችን መጠቀም ይቻላል?
ለዓመታት የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ ይዘጋል የሚለው ስጋት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የነዳጅ ላኪ የሆኑ አገራት አማራጭ የጉዞ መንገዶችን እንዲያስቡ አነሳስቷቸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ በቀን እስከ 5 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ማጓጓዝ የሚያስችል 1,200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቧንቧ መስመር ዘርግታለች።
በ2019 ሳዑዲ አረቢያ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይትን ለማስተላለፍ እንድትችል የተፈጥሮ ጋዝ መስመሯን ለጊዜው መልሳ ጥቅም ላይ አውላለች።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በቀን 1.5 ሚሊዮን በርሜል የሚይዝ የነዳጅ ማከማቻን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ከምትገኘው ፉጃይራህ ወደብ ጋር አገናኝታለች።
በሐምሌ ወር 2021 ኢራን ድፍድፍ ዘይትን ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ ለማሸጋገር የሚያስችለውን የጎሬህ ጃስክ የነዳጅ መስመርን መርቃለች።
ይህ የነዳጅ ማመላለሻ ቱቦ በቀን ወደ 350 ሺህ በርሜል ማመላለስ ይችላል።
የሚወጡ መረጃዎች ግን ኢራን እስካሁን ጥቅም ላይ አለማዋሏን ያሳያሉ።
እነዚህ አማራጭ መንገዶች በቀን ወደ 3.5 ሚሊዮን በርሜል ዘይት በአንድነት ማስተናገድ የሚችሉ ሲሆን፣ ይህም በአሁኑ ጊዜ በባሕር ሰርጡ ከሚጓጓዘው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት 15 በመቶው ይሆናል።















