ሩቢዮ አሜሪካ በሚቀጥሉት "ሁለት ሳምንታት ውስጥ" የኢራንን ጦርነት እንደምታጠናቅቅ ገለጹ
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ በኢራን እያካሄደች ያለውን ዘመቻ "በሚቀጥሉት ሁለት ምንታት ውስጥ" እንደምታጠናቅቅ ተናገሩ።
የጦርነቱ ዓላማዎች እየተሳኩ መሆናቸውን እና ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ ፈጥነው መከናወናቸውን በፈረንሳይ በተካሄደው የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን አጥብቃ ትፈልገዋለች ሲሉ የሚናገሩትን የሰላም ድርድር በመጥቀስም ከአገሪቱ መልዕክቶች መምጣታቸውን ነገር ግን አገሪቱን የሚወክል ማን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኢራን ከአሜሪካ ጋር የተጀመረ ምንም ዓይነት ንግግር የለም ስትል አስተባብላለች።
አሜሪካ እና እስራኤል የዛሬ ወር የካቲት 212018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ በርካታ የቴህራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ አካባቢው እየላከች መሆኑን ሩቢዮ ጨምረው ተናግረዋል።
ትራምፕ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው በኢራን እያደረጉት ያለው ዘመቻ ከአራት እስከ ሰባት ሳምንታት እንደሚቆይ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
አራተኛው ሳምንቱን እየጨረሰ ያለው የኢራን ጦርነት ሲያልቅ የተደረገው የሩቢዮ ንግግር ቀደም ሲል ከተቀመጡት ጊዜ ገደቦች ጋር አብሮ የመሄድ ይመስላል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጦርነቱ የሚያበቃበትን ጊዜ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ተከታታይ ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት "የሳምንታት እንጂ የወራት አይደለም" ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ያስችላል የተባለ ባለ 15 ነጥብ ዕቅድ ለኢራናውያን በፓኪስታን በኩል እንዲደርስ ማድረጋቸው በስፋት ተዘግቧል።
ይሁን እንጂ ጋዜጠኞች ኢራን አርብ ዕለት ምላሿን ትሰጥ እንደሆነ ሲጠየቁ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "እስካሁን ድረስ አልደረሰንም። መልዕክቶች እየደረሱን ነው። ከኢራን አገዛዝ፣ የቀረው ማን ይሁን ማን፣ ስለ አንዳንድ ነገሮች ለመነጋገር ፈቃደኛ ስለመሆን መልዕክቶችን እና ምልክቶችን ተለዋውጠናል።" ብለዋል።
"ከማን ጋር እንደምንነጋገር፣ ስለምን እንደምንነጋገር እና መቼ እንደምንነጋገር ተጨማሪ ማብራሪያ እየጠበቅን ነው።"
የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በኋላ ላይ "በዚህ ሳምንት" ስብሰባዎች ይኖራሉ የሚል "ተስፋ እንዳላቸው" ተናግረዋል።
"ኢራናውያን ለተወሰነ ጊዜ የተመለከቱት ባለ 15 ነጥብ ስምምነት አለን። ከእነሱ መልስ እንጠብቃለን፤ ይህም ሁሉንም ነገር ይፈታል" ሲሉ ዊትኮፍ ተናግረዋል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በኢራን የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ለንግግሮች ዕድል ለመስጠት በሚል ማቆማቸውን ተናግረዋል።
"ኢራን እየወደመች ነው" ያሉት ትራምፕ አክለውም "አሁን እየተነጋገርን ነው። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ" ብለዋል።
አርብ ዕለት ኢራን፤ በኒውክሌር ተቋሟ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ባሉት ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎች ላይ በእስራኤል ጥቃት እንደፈጸመባት ተናግራለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ይህ ጥቃት እስራኤልን "ከፍተኛ ዋጋ" እንደሚያስከፍላት ዝተዋል።
የአገሪቱን ስርዓት የሚደግፈው ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፣ ከአሜሪካ ወይም ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ በማድረግ የአጻፋ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል።
የቡድን ሰባት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ ኢራን በበቀል እርምጃ ዘግታዋለች ያሉትን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ የነበረው የመርከቦች እንቅስቃሴ እንደ ቀድሞው ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያለምንም ክፍያ ሆኖ ወደ ነበረበት መመለስ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።
ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ለማስከፈል ሕግ እያረቀቀች መሆኑ ሲነገር ሰንብቷል።
አብዮታዊው ዘብ አንዳንድ መርከቦችን ያለ ምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ ክፍያ እየጠየቀ መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎች ተሰምተዋል።
የኢራን የፓርላማ አባላትም ወሽመጡን ለሚጠቀሙ መርከቦች ስለሚተመነው ክፍያ፣ ምንም እንኳ ገና ያልዳበረ ቢሆንም፣ ረቂቅ ሕግ እያዘጋጁ መሆኑ ተሰምቷል።
ሩቢዮ በፈረንሳይ ከተካሄደው ውይይት በኋላ ዩኬ የባህር ወሽመጡ ነፃ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥምረት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት እየመራች መሆኑን ተናግረዋል። ከጦርነቱ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ጥምረት እንደሚያስፈልግ ጨምረው ተናግረዋል።
የኢራን ዛቻ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ከአሜሪካ ይልቅ አጋሮቿ የበለጠ እንደሚጎዱ አብራርተዋል።
የቡደን ሰባት አባል አገራት በመግለጫቸው ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት "በሲቪሎችና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም" ጥሪ አቅርበዋል።
"በጦርነት ወቅት ሆን ተብሎ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ እንዲሁም በዲፕሎማሲ ተቋማት ላይ ጥቃቶችን መፈጸም ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብበት አይችልም" ብለዋል።
መግለጫው ተፋላሚ ወገኖቹን በስም ባይጠቅስም፣ መልዕክቱ ኢራን ላይ የበለጠ ትኩረት ያደረገ ይመስላል።
ቴህራን የባህር ወሽመጡን ከመዝጋት በተጨማሪ ከአሜሪካ ጋር በተባባሪነት በሚሰሩ የባህረ ሰላጤ አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች የሚገለገሉባቸውን መሠረተ ልማቶች ዒላማ በማድረግ አጥቅታለች።
ቴህራን ከእስራኤል በተጨማሪ በአረብ ባሕረ ሰላጤ ወደሚገኙ እና የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ወደሚገኙባቸው አገራትም ድሮኖችንና ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።
ኢራን ከጦር ሠፈሮች በተጨማሪ በአገራቱ በሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶች፣ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና የኃይል ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም