የቡርኪና ፋሶው መሪ ሕዝባቸው የዴሞክራሲን ጉዳይ "መርሳት" እንዳለበት ተናገሩ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ፤ ዴሞክራሲ "ይገድላል"፤ የአገሪቱ ሕዝብም "መርሳት" አለበት ሲሉ በቴሌሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ተናገሩ።

ከሦስት ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት ወታደራዊው መሪ፤ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት የዴሞክራሲ ሥርዓትን አይፈልፈጉም ብለዋል።

ወታደራዊ መሪው ቡርኪና ፋሶ የራሷ አማራጭ አካሄድ አላት ሲሉም ተደምጠዋል። አማራጭ ስላሉት ስርዓት ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ትራኦሬ ሥልጣን በያዙበት ወቅት ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገራቸውን በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ቃል ገብተው ነበር። ያስቀመጡን ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ሲቀሩት ግን የሚመሩት ወታደራዊ መንግሥት ዕቅዱን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት አራዝሞታል።

ባለፈው ጥር ላይ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት "አገሪቱን መልሶ ለመገንባት" በሚል ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አግዷል።

ትራኦሬ ሐሙስ ዕለት በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው "ሕዝቡ የዴሞክራሲን ጉዳይን መርሳት አለበት። ዴሞክራሲ ለእኛ አይሆንም" ብለዋል።

ራሳቸውን የምዕራቡን ዓለም ኢምፔሪያሊዝም እንደሚጋፈጥ አብዮታዊ መሪ አድርገው የሚያቀርቡት የ38 ዓመቱ ፕሬዝዳንት፤ "ሊቢያን ተመልከቱ፤ ለእኛ ቅርብ ሆነች ምሳሌ ናት" ሲሉም ተደምጠዋል።

ትራኦሬ በምሳሌነት የጠቀሷት ሊቢያ ለአራት አስርት ዓመታት በኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ አስከፊ አገዛዝ ሥር ነበረች። በዚሁ ጊዜ ግን የሊቢያ መንግሥት ድጎማ የተደረገበት ቤት፣ ነጻ ትምህርት እና ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለሕዝቡ ያቀርብ ነበር።

ጋዳፊ 40 ዓመታትን ከተሻገረ የሥልጣን ቆይታ በኋላ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በታገዘ አመጽ ተገድለዋል። አገሪቱ ከዚያ በኋላ ምርጫ ለማድረግ አልቻለችም። ሊቢያ በሁለት ባላንጣ አስተዳደሮች የተከፈለች ሲሆን፣ በርካታ ታጣቂ ቡድኖችም ይንቀሳቀሱባታል።

ትራኦሬ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "[ምዕራባውያን ኃይሎች] ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚሞክሩበት በየትኛውም የዓለም ክፍል ሲገኙ ደም መፋፈስ አብሮ ይኖራል" ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቂት የማይባሉ ወታደራዊ የመንግሥት ፍንቀላዎች ቢስተዋሉም አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት በመደበኛ ሁኔታ ምርጫዎችን ያካሂዳሉ። አንዳንዶቹ ምርጫዎች ግን የተጭበረበሩ ናቸው የሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። ጋቦን እና ጊኒ ውስጥ የሚገኙት ሁለት ወታደራዊ መሪዎች ባካሄዱት ምርጫ አሸናፊነታቸውን አውጀዋል።

ትራኦሬ ከወራት በፊት ስለተላለፈው ፖለቲካ ፓርቲዎችን የማፍረስ ውሳኔም በቃለ መጠይቁ አንስተዋል። ፖለቲካ ፓርቲዎቹን እንደ ከፋፋይ፣ አደገኛ እና ከአብዮታዊው ፕሮጀክት ጋር የማይጣጣሙ አድርገው እንደሚቆጥሯቸው ገልጸዋል።

"እውነታው፤ አፍሪካ ውስጥ ያለ ፖለቲካ ወይም ቢያንስ እኛ ቡርኪና ውስጥ እንዳየነው ከሆነ፤ እውነተኛ ፖለቲከኛ የሚባለው ሁሉንም መጥፎ ምግባሮች የተላበሰ ነው፤ ውሸታም፣ አድርባይ እና አፈ ጮሌ [ነው]" በማለት ተናግረዋል።

የወታደራዊ መሪው አማራጭ ሥርዓት ባያቀርቡም "የራሳችን የሆነ አካሄድ አለን። የማንንም ለማስመሰል እንኳ እየሞከርን አይደለም። እዚህ ያለነው ነገሮች የሚከወኑበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ነው" ብለዋል።

ባሕላዊ መሪዎች እና ከታች የሚነሳ መዋቅር ዋና ሚና የሚጫወትበት እንዲሁም ሉዓላዊነት፣ አገር ፍቅር እና አብዮታዊ ንቅናቄ ላይ የተመሠረተ አዲስ ሥርዓት የመገንባትን አስፈላጊነት በአጽንኦት አንስተዋል።

ትራኦሬ አገሪቱን እየመሩ ያሉት ተቃዋሚዎች፣ መገናኛ ብዙኃን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖችን በማፈን ነው። መንግሥታቸው ተቺዎችን ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ፊት ለፊት በማሰለፍ እየቀጣ ነው የሚል ክስ ጭምር ይቀርብበታል።

ይህም ቢሆን ግን ወታደራዊው መሪ ባላቸው ፓን አፍሪካዊ ራዕይ እና በምዕራባውያን ተጽዕኖ ላይ በሚያሰሙት ትችት የተነሳ በአህጉሪቱ በርካታ ደጋፊዎች አሏቸው።