ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የአስተዳደራቸው ዋነኛ ተሟጋች የነበሩትን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሥልጣን አነሱ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የረዥም ጊዜ አጋር እና የአስተዳደራቸው ዋነኛ ተሟጋች የነበሩትን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲን ከሥልጣናቸው አነሱ።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓን አሞግሰው በግሉ ዘርፍ ውስጥ ወደሚኖራቸው አዲስ ኃላፊነት "ትሸጋገራለች" ብለዋል።
ቦንዲ በፍትህ ቢሮ ውስጥ የነበራቸው ኃላፊነት ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ዶሴዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ እና በእርሱ ላይ በተደረገው ምርመራ ምክንያት ጥላ አጥልቶበት ነበር።
አቃቤ ሕጓ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ከሥልጣን የተነሱ ሁለተኛዋ የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣን ናቸው።
በመጋቢት ወር ክሪስቲ ኖኤም ከአገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ቦንዲ በቀድሞ ምክትላቸው ቶድ ብላንቼ ይተካሉ ተብሏል።
ቦንዲ ያላቸውን ኃላፊነት ወደ ብላንቼ ለማስተላለፍ "ያለመታከት እሰራለሁ" ያሉ ሲሆን የነበራቸው ሥልጣንም "የሕይወት ዘመን ክብር" እንደነበር ገልጸዋል።
ወደ የትኛውም የግል ዘርፍ እንደሚያመሩ ባይገልጹም በዚያም ሆነው "ለፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ለዚህ አስተዳደር ትግሌን እቀጥላለሁ" ብለዋል።
የቦንዲ ከኃላፊነት መልቀቅ የተሰማው ከሕግ አውጪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት በጥያቄዎች ከተፋጠጡ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።
ከኮንግረስ ጋር የነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ሂደት አንዳንድ ጊዜ መደማመጥ ያልነበረበት እና በጩኸት የታጀበ ሲሆን ቦንዲ በወቅቱ አንድ ዴሞክራትን "የከሰሩ ተሸናፊ" ሲሉ ዘልፈዋቸው ነበር።
ሐሙስ ዕለት ማለዳ ትራምፕ ቦንዲን "ድንቅ ሰው ነች፤ ጥሩ ስራ እየሰራች ነው" ሲሉ አሞካሽተዋቸው ነበር።
ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን አረጋግጠው የሚሰማሩበት አዲሱ የግሉ ዘርፍ "በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚሆን" ተናግረዋል።
ትራምፕ ቦንዲ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሳሉ ያሳዩትን ብቃት በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ "በአገራችን የነበረውን ወንጀል በመቆጣጠር ረገድ እጅግ በጣም ጥሩ ስራ ሰርታለች" ብለዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ በቦንዲ በተለይም የኤፕስቲን ሰነዶችን አያያዝ በተመለከተ የበለጠ ተሰላችተው እንደነበር ተዘግቧል።
እአአ በየካቲት ወር 2025 ወደ ሥልጣን ሲመጡ በኤፕስቲን ጉዳይ ግልጽ ለመሆን ቃል ገብተው የነበረ ሲሆን እአአ በ2019 ከሞተው ባለሀብት ጋር የተያያዘውን የግለሰቦች ዝርዝር ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።
ቢሮው በኋላ ላይ እንዲህ ዓይነት ዝርዝር እንደሌለ ተናግሯል።
በመጨረሻም ከኤፕስቲን ጋር የተያያዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰነዶች የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎችን ጫና በማድረጋቸው እንዲሁም ኮንግረሱ ዶሴዎቹን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ የሚያዝ ሕግ በማጽደቁ ይፋ ተደርገዋል።
ቦንዲ እና ቢሯቸው ሰነዶቹን ይፋ ሲያደረጉ የጥቃቱ ሰለባዎችን ማንነት በመደበቅ ረገድ ክፍተቶች በማሳየታቸው ከፍተኛ ትችትን አስተናግደዋል።
ሐሙስ ዕለት ከእርሳቸው ጋር በቅርበት የሰሩ ጥቂት የሪፐብሊካን አባላት ብቻ አወድሰዋቸዋል።
ብላንቼ "ፓም ቦንዲ ይህንን ቢሮ በብርታትና ያለመታከት መርታዋለች፤ ለአመራሯና ለጓደኝነቷም አመስጋኝ ነኝ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
አክለውም "ሕግ አስከባሪዎችን መደገፍ፣ ሕግን ማስከበር እና የአሜሪካን ደህንነት ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ሌሎች ደግሞ የቦንዲን ከኃላፊነት መነሳት በደስታ ተቀብለውታል።
ከእነዚህም መካከል ቦንዲ የኤፕስታይን ሰነዶችን በአግባቡ ስለመያዝ ዘወትር ትችት ያቀርቡ የነበሩት የኬንታኪ ሪፐብሊካን ኮንግረስማን ቶማስ ማሳሲ ይገኙበታል።
"ቀጣዩ አቃቤ ሕግ ሁሉንም የኤፕስታይን ዶሴዎች በሕጉ መሠረት እንደሚለቅ እና ምርመራዎችን፣ ክሶችን እና እስሮችን እንደሚከታተል ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የካሊፎርኒያ ዲሞክራት ሮ ካና በበኩላቸው ለቢቢሲ የኒውስ ናይት ፕሮግራም "ይህ ኮንግረስ ማንም እንደፈለገው የሚረማመድበት ደካማ እንዳልሆነ ያሳያል" ብለዋል።
ካና የሕግ አውጪዎች ብላንቼን ቀጣዩ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አድርገው ለማፅደቅ ፈቃደኛ መሆን የለባቸውም ብለዋል።