ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመጋቢት ወር ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነጭ ናፍጣ 163 ብር ገባ
በኢራን ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ የታየውን ከፍተኛ ጭማሪ ተከትሎ በኢትዮጵያ የናፍጣ እና ቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ ላይ እስከ 27 ብር የሚደርስ ጭማሪ ተደረገ።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትናንት ረቡዕ መጋቢት 23/2018 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው አዲስ ተመን መሠረት፤ ነጭ ናፍጣ በሊትር 163 ብር ከ68 ሳንቲም ገብቷል። ቤንዚን ደግሞ በሊትር 142 ብር ከ41 ሳንቲም እንዲሸጥ ተተምኖለታል።
ከትናንት ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የዋጋ ጭማሪ የተያዘው መጋቢት ወር ውስጥ ብቻ የተደረገ ሁለተኛው ጭማሪ ነው። በወሩ መጀመሪያ ላይ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ እስከ 17 ብር የሚደርስ ጭማሪ ተደርጎበት ነበር።
በወቅቱ የቤንዚን ዋጋ የሦስት ብር ጭማሪ ተደርጎበት 123 ብር ገደማ ሲሸጥ ነበር። የ10 ብር ጭማሪ ያስተናገደው ነጭ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 139 ብር ከ84 ሳንቲም ተተምኖለት ለሦስት ሳምንት ገደማ ተሸጧል።
ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዲሱን የዋጋ ጭማሪ ያደረገው "የዓለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ" እንደሆነ ለነዳጅ ኩባንያዎች በላከው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል።
የአሁኑ ጭማሪ ይፋ የሆነው ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ከኢትዮጵያ ጋር ውል የገቡ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት "በግዢ ሂደት እና ተገዝቶ በመቅረብ ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ" ነዳጅን "ማቅረብ እንደማይችሉ" መግለጻቸውን ካስታወቁ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ዶ/ር ካሳሁን፤ መንግሥት የነዳጅ አቅርቦትን "ለማሳለጥ በተባባሪ ገበያ ወይም spot market አማካኝነት በከፍተኛ ውድ ዋገው በመግዛት እና በማቅረብ ላይ ይገኛል" ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ "በተባባሪ ገበያ" የሚገዛው ነዳጅ ዋጋ ከመደበኛው "በሦስት እጥፍ" ይጨምራል።
ከኢራን ጦርነት በፊት በበርሜል 80 ዶላር የነበረው የተጣራ ነጭ ናፍጣ አሁን 230 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። ቤንዚንም ከነበረበት 72 ዶላር ገደማ የቤርሜል ዋጋ ወደ 150 ዶላር ማሻቀቡን ገልጸዋል።
የቤንዚን አቅርቦት በፊት ከነበረው ጋር "የሚመጣጠን" እንደሆነ በማክሰኞ ዕለቱ መግለጫ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ነጭ ናፍጣ ግን "50 በመቶ ያህል" አቅርቦቱ መቀነሱን አስረድተዋል። "በአማካይ 9.1 ሚሊዮን ሊትር በቀን ሲቀርብ ከነበረበት ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ" ማለቱን ተናግረዋል።
ዶ/ር ካሳሁን እንደሚያስረዱት፤ መንግሥት ነዳጅ እየሸጠ ያለው ነጭ ናፍጣ ላይ በሊትር "95 ብር"፤ ቤንዚን ላይ ደግሞ በሊትር "42 ብር" በመደጎም ነው። በየወሩ መንግሥት ነዳጅ ላይ "ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር" የሚደርስ ድጎማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
አዲሱ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ተመንም ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው በናፍጣ ምርቶች ላይ ነው። ከፍተኛ የሆነውን የ27 ብር ጭማሪ ያስተናገደው ከባድ ጥቁር ናፍጣ ዋጋው 160 ብር ከ68 ሳንቲም ገብቷል።
ቀላል ጥቁር ናፍጣ ደግሞ ከነበረበት 137 ብር ገደማ ዋጋ ወደ 163 ብር ከ98 ሳንቲም ጨምሯል።
ነጭ ናፍጣ የ23 ብር፤ ቤንዚን ደግሞ የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎባቸዋል። ኬሮሲን የ5 ብር ገደማ ጭማሪ አሳይቶ 151 ብር ገብቷል። የአውሮፕላን ነዳጅ 150 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ከከፈቱት አንድ ወር የተሻገረው ጦርነት በዓለም ነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንዲሁም ዋጋ ጭማሪ አስከትሏል። ኢራን ከዓለም የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ መዝጋቷን ተከትሎ በርካታ መርከቦች ጉዟቸውን ለማቆም ተገድደዋል።
በወሽመጡ በኩል ከሚያልፈው ነዳጅ ተጠቃሚ የሆኑት የእስያ አገራት የሥራ ቀናትን ከመቀነስ እስከ ተቋማትን የመዝጋት እርምጃ ወስደዋል።
በኢትዮጵያ በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞቻቸው የዓመት እረፍት እንዲወጡ እያደረጉ ነው። መንግሥትም ነዳጅ ለየትኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት መመሪያዎችን አውጥቷል።