ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ የአሜሪካ ዜግነት ላይ የጣሉት ገደብ ዳኞችን እንዳላሳመናቸው ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገደብ የጣሉበት አሜሪካ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በተመለከተ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ጥርጣሬ እንዳለው ተገለጸ።
አብዛኞቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች የትራምፕን ዕግድ አሳማኝ ሆኖ እንዳላገኙት እና ውሳኔውም ሊቀለበስ እንደሚችል ተመልክቷል።
ከሰነድ አልባ ስደተኞች እንዲሁም ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ከሄዱ ጥንዶች ለሚወለዱ ልጆች አገሪቱ ዜግነት ስትሰጥ ቆይታለች።
የትራምፕ አስተዳደር ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ሲይዝ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ አሜሪካ ውስጥ በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ላይ ገደብ መጣል ነው።
ትራምፕ ገደቡ ሕገ ወጥ ስደትን ይቀንሳል ብለዋል። ተቀናቃኞቻቸው ደግሞ ገደቡ የአሜሪካን የስደተኞች ሕግ ይጥሳል ብለው ተከራክረዋል።
ሥልጣን ላይ ባሉ ፕሬዝዳንቶች ባልተለመደ ሁኔታ፤ ትራምፕ ትናንት በፍርድ ቤት ተገኝተው ቃላቸውን ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር የትራምን ታሪፍ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። በዜግነት ላይ የጣሉት ገደብ ውድቅ ከተደረገ የፕሬዝዳንቱ ሁለተኛ ሽንፈት ይሆናል።
ጠበቃ ጀነራል ጆን ሳውር በፍርድ ቤቱ ክርክር ወቅት እንደተናገሩት፤ አሜሪካ በመወለድ የሚገኝ ዜግነት በባርነት ለተያዙ ሰዎች የወጣ ቢሆንም በዓመታት ሒደት ትግበራው "በስህተት" የሰፋ ሆኗል።
ወሳኙን ድምጽ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ዳኛ ጆን ሮበርትስ በበኩላቸው የትራምፕ ገደብ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
በትራምፕ ውሳኔ ምክንያት የሰነድ አልባ ስደተኞች ልጆች ከዜግነት መታገድ እንደሌለባቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ ያወጣችው ሕግ መተግበር ያለበት ለውጭ አገራት ዲፕሎማቶች እና ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነው ብለው ጠበቃው ተከራክረዋል።
ልጆቻቸውን በአሜሪካ ሲወልዱ የሌላ አገር ዜጋ የሆኑ ወላጆች "ታማኝነታቸው" ለአገራቸው ነው ሲሉ ሕጉ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ሆኖም ግን ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች አብዛኞቹ የጠበቃውን ሐሳብ ተቃርነዋል። ገደብ የሚጣል ከሆነ የአሜሪካ የዜግነት መብት ሒደት ላይ እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ዳኛዋ ኤሌና ካግን እንዳሉት፤ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ዕድሜ ጠገብ የዜግነት ሕግጋትን ለመቀልበስ እየሞከረ ነው።
በአውሮፓውያኑ በ1898 በአሜሪካ መንግሥት እና ዎንግ ኪም አርክ በተባሉ ግለሰብ መካከል የተደረገውን ክርክር፤ አሜሪካ የሚወለዱ ልጆች ዜግነት የማግኘት መብትን በማስከበር ረገድ በጉልህ ይጠቀሳል።
ይህም ከቻይናውያን ስደተኞች ለተወለደ ልጅ የአሜሪካ ዜግነት መስጠት ላይ የተደረገ ክርክር ነበር።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞቹ በአውሮፓውያኑ 1952 ኮንግረስ ያጸደቀውን የዜግነት ሕግን በማጣቀስ "ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ መብትን መጣስ አይፈልግም" ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ የፊታችን ሰኔ ውሳኔውን በይፋ ያስታውቃል።
ትራምፕ አሜሪካ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ላይ የጣሉትን ገደብ ጨምሮ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ጥብቅ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የጀመሩት ሥልጣን በያዙ ማግስት ነበር።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገውት የነበረው የስደተኞች ጉዳይን ነው።
ትራምፕ "በመወለድ ዜግነት የምንሰጥ ብቸኛው ቀሽም አገር ነን። ይህ ሕግ የወጣው ከእርስ በርስ ጦርነቱ በኋላ ለባሪያ ልጆች ሲባል ነው" ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።
"ሕጉ የወጣው 57 ልጆች ወልደው አሜሪካዊ ለሚያደርጉ ቻይናዊ ቢልየነሮች አይደለም" ሲሉም አክለዋል።