በኡጋንዳ መዋዕለ ሕጻናት ውስጥ አራት ሕጻናት በስለት ተወግተው ተገደሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሁለት ዓመት እና የሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው አራት ልጆች ሐሙስ ዕለት በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በሚገኝ የሕፃናት ትምህርት ቤት ውስጥ "በጭካኔ በስለት ተወግተው ተገድለዋል" ሲል የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

ሦስቱ ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጅ ወዲያውኑ መገደላቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ጥቃት የፈጸመው ከአንድ በላይ ስለት በመጠቀም መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የ39 ዓመቱ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ "ይህንን አሰቃቂ ወንጀል የፈጸመበትን ምክንያት እና ሌሎች ተዛማጅ ሁኔታዎችን መመርመር ቀጥሏል" ሲል የኡጋንዳ ፖሊስ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ክስ አስታውቋል።

በግለሰቡ ድርጊት የተቆጡ ወላጆች በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ሊገድሉት ሞክረው እንደነበር ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የፖሊስ ቃል አቀባይ ራቸል ካዋላን ጠቅሶ ዘግቧል።

ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋሩት ምስሎች የተቆጡ እና የተጨነቁ ወላጆችን ያሳያል፤ አንዳንዶቹ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ለማወቅ ሲጠይቁ ተስተውለዋል።

ካዋላ እንዳሉት ተጠርጣሪው በቅርቡ ወደ ጊጋባ መዋዕለ ሕጻናት በመምጣት ልጅ ለማስመዝገብ ጠይቆ እንደነበር እና ሐሙስ ዕለት እንዲመለስ እንደተነገረው ገልጸዋል።

"የመመዝገቢያ ክፍያ ከፍሏል፤ ቀጥሎም እነዚህን ልጆች አጥቅቶ አራቱን ወዲያውኑ ገድሏል" ብለዋል።

ወንጀሉ የተፈፀመው ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ፖሊስ ስለ ወንጀሉ መረጃ እንደደረሰው በቦታው በፍጥነት መገኘቱን አስታውቋል።

በወቅቱ በትምህርት ቤቱ የነበሩ ሌሎቹ 10 ልጆች ለወላጆቻቸው ተላልፈው መሰጠታቸውን ቃል አቀባይዋ ጨምረው ገልጸዋል።

መርማሪዎች በጊጋባ አካባቢ በመገኘት ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ካዋላም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች ወደፊት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የፖሊስ አዛዥ አባስ ባይካጋባ ትምህርት ቤቱን ጎብኝተው ፖሊስ ስራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ሕዝቡ እንዲረጋጋ አሳስበዋል።

ይህ አሳዛኝ ክስተት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ወላጆችን ያስደነገጠ ሲሆን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ የተማሪዎች ደህንነት ላይ መኖር ስለሚገባው ጥንቃቄ ጥያቄ አጭሯል።