ኢራን ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰቡ ያሉት ትራምፕ የቆሙበት መንታ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት በመሆን ቴህራን ላይ ጦርነት ከጀመሩ ከሦስት ሳምንታት በኋላ፣ ግጭቱ የተደበላለቁ መልዕክቶች የሚተላለፉበት እና እርግጠኛ አለመሆን የሞላበት እየሆነ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በአደባባይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ከነባራዊ እውነታዎች ጋር የሚጋጩ ይመስላሉ።
ጦርነቱ "እየተጠናቀቀ ነው ማለት ይቻላል" ሲሉ ትራምፕ ቢናገሩም አዲስ የአሜሪካ የምድር ጦር እንዲሁም የባሕር ኃይል ወደ ቀጠናው እያንቀሳቀሰ ነው።
"እየተጠናቀቀ ነው" ባሉት ጦርነት አሁንም አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የሚፈጽሙትን ድብደባ አላቋረጡም፤ ኢራንም ሚሳዔል እና ድሮኖች ማስወንጨፏን አልገታችም።
የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት "ቀላል ወታደራዊ እርምጃ" ነው ቢሉም ለጊዜው በኢራን ይሁንታን ያገኙ ጥቂት መርከቦች ብቻ በባሕሩ ላይ መቅዘፍ ይችላሉ።
የኢራን ጦር "ጠፍቷል" ቢሉም ነገር ግን ድሮኖች እና ሚሳዔሎች አሁንም በቀጣናው ውስጥ ወደሚገኙ ዒላማዎች እያስወነጨፈ ሲሆን ከአካባቢው አልፎም የአሜሪካ እና ዩኬ የጋራ የጦር ሠፈር በሚገኝበት እስከ ዲያጎ ጋርሲያ ድረስ ጥቃት መፈጸም ችሏል።
ትራምፕ ቅዳሜ ምሽት ላይ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ ኢራን ሆርሙዝን በ48 ሰዓታት ውስጥ "ያለ ምንም ስጋት ሙሉ በሙሉ ካልከፈተች" የአሜሪካ ጦር "ትልልቅ" የአገሪቱን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ዒላማ ማድረግ እንደሚጀምር አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ከአንድ ቀን በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አሜሪካን ከኢራን ጋር በምታካሄደው ጦርነት ልታሳካቸው የምትፈልጋቸውን ወታደራዊ ዓላማዎች ዝርዝር ሲያቀርቡ ይህንንም አገራቸው "ለማሳካት በጣም እየተቃረበች ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መግለጫ የሰጡት ትራምፕ የኢራንን ወታደራዊ ኃይል፣ የመከላከያ መሠረተ ልማቷን እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፕሮግራሟን መቀነስ ወይም ማውደም እንዲሁም በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ አጋሮችን መጠበቅ ዓላማዎቻቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን መጠበቅ የሚል ግብ ግን አልተካተተም።
ትራምፕ ወሽመጡን መጠበቅ ከባሕረ ሰላጤው በሚወጣው የነዳጅ ምርት ላይ ጥገኛ የሆኑ ሌሎች አገሮች ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አገራቸው ከመካከለኛው ምሥራቅ በሚመጣው የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ እንዳልሆነች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት የኢራንን አገዛዝ ለውጥን በተመለከተ ምንም ዓይነት ጥሪ አላቀረቡም።
በጦርነቱ መጀመሪያ ቀናት ላይ አጥብቀው የጠየቁትን የአገሪቱን ቀጣይ መሪ ማፅደቅ ወይም "ያለ ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠት" የሚያመለክቱ ምንም መልዕክቶች የሉም።
ትራምፕ በቅርቡ ይፋ ባደረጓቸው ዓላማዎች ላይ በጦርነት ውስጥ ሆናም የነዳጅ ምርትዋን ወደ ውጭ እየላከች ባለችው ኢራን፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን የተወሰነ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻል ከሆነ በሥልጣን ላይ ያለውን ፀረ-አሜሪካን አገዛዝ እያለ የጀመረችውን ዘመቻ ልታቆም እንደምትችል ጠቁመዋል።
ይህ እስላማዊ ሪፐብሊክ ከሥልጣን ለማስወገድ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ለነበሩት እና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየተጓዙ ያሉትን የአሜሪካ የምድር ጦር ኃይሎችን የሚያካትት አማራጭ መንገድ ይኖራል ብለው ለሚያስቡት የሚዋጥ አይመስልም።
ከአንድ ሳምንት በፊት የአሜሪካ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ወደ 2,500 የሚጠጉ የባሕር ኃይል ወታደሮችን እና ድጋፍ ሰጪ መርከቦችን እና አውሮፕላኖችን የያዘ ቡድን ከጃፓን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተልኳል።
ተመሳሳይ መጠን ያለው ሌላ የባሕር ኃይል በቅርቡ በካሊፎርኒያ የሚገኘውን የጦር ሰፈሩን ለቅቆ ተንቀሳቅሷል።
ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት አሜሪካ ኢራንን ወደ ውጭ የምትልከውን የነዳጅ ምርት የምታስተላልፍበት እና 3 ካሬ ኪ.ሜ ስፋት ያላትን የኻርግ ደሴትን ለመያዝ አቅዳ ሊሆን ይችላል።
አሜሪካ ይህንን የምታደርግ ከሆነ በንድፈ ሀሳብ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከውን የነዳጅ ዘይት ሊያቋርጥ እና የምታገኛውን ወሳኝ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ሊያሳጣ ስለሚችል ጦርነቱ እንዲቆም ለማስገደድ ቀላል ይሆናል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ወደ ኢራን የምድር ጦራቸውን እንደማይልኩ ቢናገሩም፣ "የማደርገው ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት አልነግርህም ነበር" ሲሉ አክለዋል።
የኢራን የመንግሥት ሚዲያዎች ቅዳሜ ዕለት በኻርግ ደሴት ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት ቴህራን በቀይ ባሕር ውስጥ የሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ "መስተጓጎልን" እንድትፈጥር እና በቀጣና ውስጥ የሚገኙ የኢነርጂ ተቋማት "በእሳት እንዲቀጣጠሉ" እንደምታደርግ ዘግበዋል።
ኢራን የሰጠችው ማስጠንቀቂያ የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይሎች ለቴህራን የበቀል እርምጃ የበለጠ የሚያጋልጥ መሆኑን አጉልቶ ያሳያል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የትራምፕ አስተዳደር ለኢራን ወታደራዊ ዘመቻ 200 ቢሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ለኮንግረስ ለመጠየቅ እየተዘጋጀ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ዋይት ሐውስ ረዥም እና ውድ ለሆነ ውጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ያሳያል።
ኮንግረሱ እንዲሁም የሪፐብሊካን አባላት ለዚህ ጥያቄ የሰጡት የመጀመርያ ምላሽ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር።
"እየተነጋገርን ያለነው እግረኛ ጦር ስለማሰማራት ነው። ስለዚያ ዓይነት የተራዘመ እንቅስቃሴ ነው የምንነጋገረው" ሲሉ የቴክሳስ ሪፐብሊካን ኮንግረስ አባል ቺፕ ሮይ ተናግረዋል።
"እንዴት እንደምንከፍል እና ተልዕኳችን ምን እንደሆነ የሚያስረዱ ተጨማሪ ማብራሪያዎች መስጠት ይጠበቅባቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
"የጦርነት ደመና" የሚባለው ነገር የወታደራዊ ዕቅድ አውጪዎችን አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የፖለቲከኞችንና የሕዝቡን አመለካከትም ይነካል።
የኢራን ጦርነት ማዕከሉ ላይ ያለ ቢመስልም ነገር ግን አሁን ካለበት ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚሄድ ግን እንቆቅልሽ ነው።















