መድኃኒት አምራቾች ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ካልተስማሙ 100% ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ተገለጸ

መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Thanasis via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

መድኃኒት አምራቾች ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ 100% ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

ትራምፕ ለረዥም ጊዜ ሲዝቱ እንደቆዩት መድኃኒት አምራቾች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ትናንት ይፋ አድርገዋል።

ዋይት ሐውስ እንዳለው ከውጭ አገራት የሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ታሪፉ ያስፈለገው የአሜሪካ ተቋማትን ለማበረታታት እና የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ነው።

ታዋቂ ድርጅቶች ከሚያመርቷቸው መድኃኒቶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ እና በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርቡ አማራጭ መድኃኒቶች ታሪፍ አልተጣለባቸውም። አብዛኞቹ አሜሪካውያን የሚጠቀሙት ደግሞ እነዚህን ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶች ነው።

እነዚህ መድኃኒቶች በታሪፍ ዝርዘር ውስጥ ባለመካተታቸው፤ የትራምፕ ታሪፍ "በአመዛኙ ምልክታዊ ነው" እንዲባል አድርጓል።

ግዙፍ መድኃኒት አምራቾች ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ስምምነት ፈጽመዋል። የተቀሩትም በቀጣይ ሳምንታት ከስምምነት እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሻን ሱሊቫን "ትራምፕ የተቀሩት መድኃኒት አምራቾችን ወደ ድርድር ለማምጣት ይፈልጋሉ" ብለዋል።

የትራምፕ የሥልጣን ዘመን በአውሮፓውያኑ 2029 ከመገባደዱ አስቀድሞ አዲስ መድኃኒት በአሜሪካ ለማስተዋወቅ የተስማሙ ተቋማት 20% ታሪፍ ብቻ ይጣልባቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተቋማቱ መካከል ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የተስማሙት ምንም ታሪፍ አይከፍሉም። ተቋማቱ መድኃኒታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት ዋጋ ላይ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር መስማማት ይጠበቅባቸዋል።

አንዳንዶቹ መድኃኒት አምራቾች ምርታቸውን ለአገሪቱ ብሔራዊ መድኅን ተቋም በመሸጥ ዋጋው እንዲቀንስ ተስማምተዋል።

አሜሪካ ባለፈው ዓመት ከአውሮፓ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ጋር ታሪፍ ለመቀነስ ተስማምታለች።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ስምምነቱን ለአገሪቱ መድኃኒት አምራቾች እና ምጣኔ ሃብት "ድል" ሲል ገልጾታል።

መድኃኒት አምራቾች ጠንካራ ማበረታቻ ማግኘታቸው የሕክምና ሙከራዎችን በዩኬ እንዲያከናውኑ ያግዛል ተብሏል። ካንሰርን የመሰሉ ሕመሞች ያሉባቸው ዜጎች አዳዲስ መድኃኒቶችን በቀላሉ እንደሚያገኙም ይጠበቃል።

የአሜሪካ መንግሥት ታሪፍ ከመጣሉ በፊት ለግዙፍ መድኃኒት አምራቾች 120 የሥራ ቀናት፣ ለመካከለኛ እና አነስተኛ መድኃኒት አምራቾች ደግሞ 180 የሥራ ቀናት ሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም በቂ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጠ ስምምነት ላይ የማይደርሱት እርምጃ እንደሚጠብቃቸው የትራምፕ አስተዳደር አስጠንቅቋል።

በብሩኪንግስ ኢንስቲትዩት የጤና ፖሊሲ ባለሙያ ሪቻርድ ፍራንክ እንደተናገሩት፤ ምን ያህል መድኃኒቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጣል ግልጽ ስላልሆነ የሚያሳድረውን ጫና ለማወቅ ይከብዳል።

ግዙፍ መድኃኒት አምራቾች ስምምነት ላይ ቢደርሱም አነስተኛ ተቋማት ታሪፍ ሊጣልባቸው ይችላል።

"ችግሮች የሚታዩት የታሪፍ ስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ሲደረግ ነው። ጥሩ የሚመስሉ ነገሮች እንደተባለው ላይሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የአሜሪካ መንግሥት አገር በቀል መድኃኒት አምራቾችን ማበረታታት ቢፈልግም ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቀው ይችላል። ስለዚህም ከሌሎች አምራቾች ጋር የዋጋ ስምምነት ማድረግን እንደ አማራጭ ወስዷል።

ዋይት ሀውስ እንዳለው ከሆነ ታሪፍ ይጣላል በመባሉ ብቻ መድኃኒት አምራቾች በአሜሪካ 400 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብተዋል።