ጋና ውስጥ ማርፈድ ባህል ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው

ሰአት የሚሰራ ጋናዊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የጃፓኑ የኦሎምፒክ ጉዳዮች ሚኒስትር ዮሺታካ ሳኩሩንዳ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ሶስት ደቂቃ በማርፈዳቸው በህዝብ ፊት ወጥተው ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርገው ነበር። እንደ ጋናውያን ሚኒስትሮች የማርፈድ ልማድ ቢሆን ግን ከስራቸው እስከመባረር ሊያደርሳቸው ይችል ነበር ማለት ነው።

ደግነቱ ጋና ውስጥ ማርፈድ ምንም ማለት አይደለም። እንዳውም ማንኛውም ሰው ሆነ የመንግሥት ሃላፊዎች እስከ 40 ደቂቃ ድረስ እንዲያረፍዱ ይጠበቅባቸዋል ትላለች የቀድሞዋ ሚኒስትር ኤሊዛቤት ኦሄኔ።

''እኔ ሚኒስትር በነበርኩበት ወቅት በስብሰባዎች ላይ በሰአቱ ብገኝም አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት አርፍደው ነው የሚመጡት። እንደውም እኔ ሰአቴን አክብሬ በመምጣቴ ይገረሙ ነበር።''

''ሁሌም ቢሆን ፕሬዝዳንቱ በአሰታቸው ቢገኙ ምናልባት የባለስልጣኖቻቸውን አስተሳሰብ መቀየር ይችሉ ነበር ብዬ አስባለሁ።'' ትላለች።

የአሁኑ የጋና ፕሬዝዳንት ናና አዶ ዳንክዋ አኩፎ አዶ የሃገሬውንና የባለስልጣኖቻቸውን የሰአት አጠቃቀም ለመቀየር ቃል ገብተው ነበር።

እንደውም እራሳቸው ምሳሌ በመሆን ነገሮችን ለመቀየር ቢሞክሩም ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ ሆኖ አላገኙትም።

ፕሬዝዳንቱ በተባለው ሰአት በስብሰባዎች ላይ ቢገኙም ሚኒስትሮቻቸው ማርፈዳቸውን ማቆም አልቻሉም።

የጋና ባንዲራ ያለበት ሰአት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገሮችን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ትላለች የቀድሞ ሚኒስትሯ፤ ''በቀጠሮ ሰአት ካለመገኘት አልፎ የተያዙ ቀጠሮዎች በተባለላቸው ሰአት መጠናቀቅ አለመቻላቸው ነው።''

'' ከጠዋቱ 3 ሰአት መጀመር ያለበት የቤተክርስቲያን ዝግጅት ለመታደም አብዛኛው ሰው ከ30 እስከ 1 ሰአት አርፍዶ ነው የሚመጣው። በዚህ ምክንያት ዝግጅቶቹ በስንት ሰአት እንደሚጠናቀቁ ማወቅ እጅግ ከባድ ነው። '' ትላለች።

በአንድ ወቅትም ከጠዋቱ አራት ሰአት የጀመረው አምልኮ ዝግጅት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ መጠናቀቁን ታስታቀውሳለች።