የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መራጮች እንዲመዘገቡ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ገለጸ
የፎቶው ባለመብት, NBE
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በመራጮች የምዝገባ ሂደት ወቅት "ቤት ለቤት በመሄድ" ካርድ ውሰዱ ከሚል አንስቶ "ማኅበራዊ አገልግሎት ማግኘት" እንዲሁም "ከደሞዝ መቁረጥ ጋር በማያያዝ" በዜጎች ላይ ተጽዕኖ እስከማድረስ ያሉ ተግባራትን ማስተዋሉን ገለጸ።
ምርጫ ቦርድ ሐሙስ መጋቢት 24/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ቦርዱ በመራጮች ምዝገባ ሂደት "የሕግ ጥሰት" ማስተዋሉን በመግለጽ ባወጣው መግለጫ "የእርምት እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ችግሩ በተስተዋለባቸው የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች "ምርጫ እንዳይካሄድ" እስከማድረግ የሚደርስ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስጠንቅቋል።
ቦርዱ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ለክልል መንግሥታት እና ለሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማድረግ እንዲቆጠቡ እና በመራጭነት መመዝገብን እንደ ግዴታ የሚያደርግ ያልተገባ ተጽዕኖ አንዲታቀቡ በጽሑፍ ማስታወቁን አመልክቷል።
በማንኛውም አካል ሕግን በመጣስ በየቤቱ በመሄድ ተመዝገቡ ማለት እና በየመሥሪያ ቤቱ ለመራጭነት እንዲመዘገቡ ማስገደድ እንደማይቻል ምርጫ ቦርድ በመገለጫው ላይ ጠቅሷል።
ቦርዱ የመራጭነት ካርድ ካልወሰዳችሀ ደሞዛችሁ ይቆረጣል ማለት እና ማስፈራራት "ሕገወጥ ድርጊት" በመሆኑ አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጿል።
ቦርዱ በዚህ መግለጫው የእርምት እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ "የተጠቀሰው ያልተገባ ቅስቀሳ" በሚደረግባቸው የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት "ምርጫ እንዳይካሄድ የሚያደርግ እርምጃ እስከመውሰድ" ለመወሰን የሚገደድ መሆኑን አስታውቋል።
ዜጎች መምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጭነት መመዝገብ በምንም መልኩ በግዴታ መሆን የለበትም ብሏል።
"በመራጭነት መመዝገብ ግዴታ አይደለም" ካርድ አለመውሰድም "ደሞዝ እንደማያስቆርጥ እና ከሥራም ሆነ ከማንኛውም ማኅበራዊ አገልግሎት እንደማያስከልክል" በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን የዕጩዎች ምዝገባ ተጠናቅቋል።
ቦርዱ የመራጮችን ትምህርት ለማስተማር ራሱ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እንደሚያካሂድ ወይም ፈቃድ የሚሰጣቸው አካላት ሊያስተምሩ እንደሚችሉ ገልጿል።
በምርጫው ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚችሉ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም