ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን "በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች" ላይ ተነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር "በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች" ላይ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የሩሲያ መንግሥት አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 7/2018 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ፤ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር "ውጤታማ" የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጻ የሁለቱ መሪዎች ንግግር "በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች" ያተኮረ ነው።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ክሬምሊን በበኩሉ ባወጣው መረጃ "በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች" ላይ መነጋገራቸውን ገልጿል።

የሁለቱ መሪዎች ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው መስከረም ወደ ሩሲያ በተጓዙበት ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነም በክሬምሊን መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዓመቱ መጀመሪያ በፕሬዝዳንት ፑቲን ግብዣ ወደ ሞስኮ ተጉዘው በዓለም አውቶሚክ ሳምንት ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው እና ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች በወቅቱ ውይይት ካደረጉባቸው ጉዳዮች አንዱ "ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ንፁህ ኃይል ምንጭ የሚውል የጋራ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የማልማት ስምምነቶች" እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

"የኃይል ማመንጫ፣ ግብርና፣ የጤና ጥበቃ ልማት እና የመከላከያ ትብብርን" የተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርገው ነበር።

በመስከረሙ ጉዞ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች የተከተለው ዛሬው የሁለቱ መሪዎች ውይይትም "ከፖለቲካ፣ ከንግድ እና ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከሰብአዊ ዘርፎች" ጋር የተያያዙ "የሁለትዮሽ ትብብር" መስኮች እንደተነሱበት ተገልጿል።

የክሬምሊን መግለጫ፤ "ሁለቱም ወገኖች የሩሲያ እና የኢትዮጵያን በወዳጅነት የተሞላ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም በሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል" ይላል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳን ፑቲን 81 ሰዎች እንደሞቱ በተረጋገጠበት እና በአጠቃላይ 125 ሰዎች በጠፉበት የጋሞ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጹላቸው ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ወደ 130 ዓመታት የሚጠጋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል። ይህም ሩሲያ በአፍሪካ ካላት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከቀዳሚዎቹ የሚመደብ ነው።

ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በምጣኔ ሃብት እና በባሕል ጠንካራ ትስስር አዳብረዋል።