ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጦርነት ውጥረት ውስጥ ወዳለችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገቡ

የፎቶው ባለመብት, wam
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢራን ጦርነት አለመረጋጋት ውስጥ ወደ ገባው መካከለኛው ምሥራቅ ተጉዘው የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 3/2018 ዓ.ም. ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተጓዙት ለሥራ ጉብኝት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቡዳቢ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፍትሕ ሚኒስትር አብዱላህ ሲልጣን ቢን አዋድ አል ኑኢሚ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ፕሮቶኮል እና ስትራቴጂክ ትርክት ባለሥልጣን ሊቀመንበር የሆኑት ሞሐመድ አብዱላህ አል ጀነቢም በስፍራው ተገኝተዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አቡ ዳቢ የተጓዙት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ከከፈቱት ጥቃት በኋላ በተነሳው ጦርነት ምክንያት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ በርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት እያስተናገዱ ባሉበት ወቅት ነው።
የኢራንን የአጸፋ ምላሽ ከደረሰባቸው አገራት አንዷ የሆነችው ኤምሬቶች፤ ጦርነቱ በተካሄደባቸው 13 ቀናት ውስጥ በርካታ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ተወንጭፈውባታል። ጦርነቱን ተከትሎ በመላው መካከለኛው ምሥራቅ የአየር በረራ ለቀናት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን አሁን በከፊል ተጀምሯል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ወደሚገኙ በርካታ መዳረሻዎች የሚያደርጓቸውን በረራዎች ካቋረጡ የአየር ትራንስፖርት አቅራቢዎች አንዱ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ አቡ ዳቢ የደረሱት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በርረው እንደሆነ ጽሕፈት ቤታቸው ያወጣው ፎቶ ያመለክታል።
ባለፉት ቀናት የተወሰኑ አገራት ባለሥልጣናት ወደ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተገኙ ቢሆንም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውጪ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወደ አገሪቱ የተጓዘ የአገር መሪ ስለመኖሩ አልተገለጸም።
ዐቢይ ዛሬ ረፋድ ላይ አቡ ዳቢ ከመድረሳቸው አስቀድሞ በትናንናው ዕለት ልዑካቸውን አስከትለው ወደ ጂቡቲ ተጉዘው ነበር።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተጓዙት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ይገኙበታል።
በጅቡቲ ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ እንዲሁም ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን መሐመድ ሼህ ጋር ተነጋግረዋል። የሦስቱ መሪዎች ንግግር "ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ" ያተኮረ እንደነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር በትናንትናው ዕለት ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። ንግግሩ ሁለቱ አገራት በቀጣናዊ መረጋጋት ዙሪያ ባላቸው የጋራ አቋም እንዲሁም የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ ላይ በሚያደርጉት ትብብር ላይ ያተኮረ እንደነበር የአሜሪካ ውጩ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተጓዙት ቀጥታ ከጂቡቲ ይሁን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እስካሁን አልታወቀም። የአቡ ዳቢ ጉብኝታቸው ለምን ያህል ቀናት እንዲቆይ፣ ምን ላይ እንደሚያተኩት እና ከማን ጋር እንደሚነጋገሩም እስካሁን አልተገለጸም።
አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የኢራን አጸፋ ጥቃት እየደረሰባቸው ካሉ ቀዳሚ አገራት መከካል የተበባሩት አረብ ኤምሬስ አንዷ ናት። ኢራን በየዕለቱ በሚባል ደረጃ በተለያዩ ኤምሬትስ ክፍሎች ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት እየፈጸመች ነው።
በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፍ በረራዎች ውስን ናቸው አንዳንድ ጊዜም ይቋረጣሉ። አገራት ዜጎቻቸው እና ዲፕሎማቶቻቸው ከአገሪቱ ለቅቀው እንዲወጡ እያስጠነቀቁ ነው።
ከኢራን በኩል በሚሰነዘርባት ጥቃት ሳቢያ በርካታ አገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኤምሬትስ ሕዝብ እና መንግሥት ጎን መቆማቸውን በስልክ እና በሌሎችም መንገዶች እየገለጹ ነው። አንዳንድ ባለሥልጣናትም በአካል ወደ አገሪቱ በማቅናት ድጋፋውን እያሳዩ ነው።
በአገር መሪ ደረጃ ግን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የተደረገ ይፋዊ ጉብኝት ስለመኖሩ የወጣ ሪፖርት የለም። ስለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት በአገር መሪ ደረጃ የተደረገ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሳይሆን አይቀረም።















