አሜሪካ ስምንት "የአፍሪካ የዘር ሐረግ ያላቸውን" ስደተኞች ወደ ኡጋንዳ አባረረች

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ስምንት ሰዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኡጋንዳ ተባረሩ።
ይህ ባለፈው ዓመት አገራቱ ከተፈራረሙት ስደተኞች የማዘዋወር ስምምነት በኋላ የተወሰደ የመጀመርያው እርምጃ ነው።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የአሜሪካ ዳኛ የስደተኞቹን ከአገር መባረር ካጸደቀ በኋላ ረቡዕ ዕለት ወደ አገሪቱ መጥተዋል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ ከአሜሪካ ጋር የተፈራረመው ስምምነት ኡጋንዳ ወደ አገራቸው መመለስ ለማይችሉ ደኅንነቷ የተጠበቀ ሦስተኛ አገር ተደርጋ ትቆጠራለች።
የኡጋንዳ የሕግ ማኅበር የአሜሪካን እርምጃ አውግዞ ግለሰቦቹ "ክብርን በሚነካ፣ በሚያሰቃይ እና ሰብዓዊነትን በሚያዋርድ ሂደት" ወደ አገሪቱ መጥተው እንደተጣሉ ገልጿል።
ድርጅቱ ሂደቱን ሕገ ወጥ ሲል ጠርቶት በፍርድ ቤት እንደሚከራከርም አስታውቋል።
ቢቢሲ የአሜሪካን የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ ጠይቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገራት አባርረዋል።
ይህም አስተዳደሩ ሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ የሚከተለው ጠንካራ አካሄድ አካል ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፖሊሲውን ያወገዙ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ፖሊሲው ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለተባረሩት ስደተኞች ግላዊ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በሚል ብዙ ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችል ቢገልጽም "ኡጋንዳ ለተቸገሩ ሰዎች መጠለያ ለማቅረብ እና በክብር መያዛቸውን ለማረጋገጥ የገባችውን ቁርጠኝነት መከተሏን ቀጥላለች" ብሏል።
እነዚህ ሰዎች የኡጋንዳም ሆነ የአሜሪካ ዜጎች እንዳልሆኑ ቢገልጽም "አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸው እና በአሜሪካ ጥገኝነት ላይሰጣቸው የሚችል እንዲሁም ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ወይም ስጋት ሊኖራቸው የሚችል" እንደሆኑ ገልጿል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ኡጋንዳ የወንጀል ታሪክ ከሌላቸው በስተቀር ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምታለች።
እንደ አሜሪካ ዘገባ ከሆነ ወደ ሌሎች ሦስተኛ አገራት ከሚባረሩት ውስጥ አብዘኞቹ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠባቸው ወንጀለኞች ናቸው።
ትራምፕ ከሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ጀምሮ ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት ሰፊ ጥረት አድርገዋል።
ይህም በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙበት ቁልፍ ተግባር ነው።
ኡጋንዳ ከአሜሪካ የተባረሩ ሰዎችን ለመቀበል ስምምነት ከፈረሙ በርካታ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን ኤስዋቲኒ፣ ጋና እና ደቡብ ሱዳንም ይገኙበታል።















