ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት እስከ 2.3 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ማስያዣ ሊጠየቁ ነው

የአሜሪካ ቪዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለንግድ እና ጉብኝት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የሚያስችል ቪዛ ለማግኘት የሚያመለክቱ ኢትዮጵያውያን ከአምስት እስከ 15 ሺህ ዶላር ወይም 2.3 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ማስያዣ ገንዘብ ሊጠየቁ ነው።

ኢትዮጵያውያኑ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ አሜሪካ ውስጥ ከቆዩ ገንዘቡ ተመላሽ እንዳይሆን የሚያደርገው ይህ አሠራር፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አሜሪካ የሚጓዙበትን እንዲሁም በዚያ የሚቆዩበትን መንገድ እያጠበቀ ያለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፤ ቪዛ ለማግኘት የዋስትና ገንዘብ እንዲያዝ የሚያደርገውን አሠራር ያስተዋወቀው ሐምሌ 2017 ዓ.ም. ነበር።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለፈው ታኅሣሥ ላይ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ ግዴታ ከተጣለባቸው 38 አገራት ውስጥ 24 ያህሉ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

እንደ ጂቡቲ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ ያሉ የአፍሪካ አገራት በዚህ አሠራር ውስጥ በተካተቱበት ወቅት ኢትዮጵያ ሳትጠቀስ ቀርታ ነበር።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አሁን ተጨማሪ 12 አገራት ይህ ግዴታ እንዲጣልባቸው መወሰኑን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ አንድ ኃላፊን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከመጋቢት 24/2018 ዓ.ም. ጀምሮ አሠራሩ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው 12 አገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ሞዛምቢክ፣ ቱኒዚያ ሌሴቶ፣ ሞሪሺየስ እና ሲሺየልስ በአዲሱ ዝርዝር ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር የተካተቱ ሌሎቹ አፍሪካ አገራት ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመሥሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያሳየው ይህ አሠራር ተግባራዊ የሚሆነው ለንግድ እና ለቱሪዝም የሚሰጡትን "B1/B2" የቪዛ ዓይነቶችን በሚጠይቁ ዜጎች ላይ ነው።

ቪዛው ለማግኘት የሚፈልጉ አመልካቾች የሚያስይዙት ገንዘብ 5,000፣ 10,000 ወይም 15,000 ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል። አመልካቾች ምን ያህል ገንዘብ ማስያዝ እንዳለባቸው የሚወሰነው በቪዛ ቃለ መጠይቅ ወቅት ነው።

በዚህ መልኩ ቪዛ የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ግዴታዎች ይጣሉባቸዋል። እንደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ገለጻ፤ ገንዘቡን ያስያዙ ዜጎች ወደ አሜሪካ መግባት እና መውጣት ሚችሉት በንግድ አየር ማረፊያዎች ብቻ ነው።

በምድር፣ በባሕር፣ በቻርተርድ አውሮፕላን ወይም እንደ የግል አውሮፕላን ባሉ የጠቅላላ አቪዬሽን ጉዞዎች ወደ አሜሪካ መግባትም ሆነ ከአገሪቱ መውጣት አይችሉም።

ኢትዮጵያውያኑ በተፈቀደው የመግቢያ እና መውጫ መንገድ ከተንቀሳቀሱ እንዲሁም ቪዛው በሚያበቃበት ቀን ወይም አስቀድመው ከአሜሪካ ከወጡ በማስያዣነት ያስገቡት ገንዘብ "ወዲያውኑ" ይመለሳል።

ቪዛው ካገኙ በኋላ ወደ አሜሪካ ካልተጓዙ ወይም አሜሪካ ሲደርሱ እንዲመለሱ ከተደረጉም ገንዘባቸውን መልሰው ያገኛሉ።

የተቀመጡት ግዴታዎች የሚጣሱ ከሆነ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጉዳዩን ወደ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት እንደሚወስደው ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያኑ ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ ጥገኝነትን መጠየቅን ጨምሮ ካሉበት ስደተኛ ያልሆነ ሰው ደረጃ የሚያወጧቸው ሌሎች ሂደቶችን የሚጀምሩ ከሆነ ገንዘቡ እንደማይመለስ የመሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

ተጓዦቹ ያገኙት ቪዛ ማብቂያው ቀን ካለፈ በኋላ ከአሜሪካ መውጣት እና ቀኑ ተጠናቆ አገሪቱ ውስጥ መቆየትም እንዲሁ ግዴታን እንደመጣስ ይቆጠራሉ።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በወሰዳቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያጠቡ እርምጃዎች ውስጥ ኢትዮጵያን ሲያካትት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ለጉብኝት እና ለንግድ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የሚሰጣቸው ቪዛ የቆይታ ጊዜ ከሁለት ዓመት ወደ ሦስት ወር መቀነሱ ይታወሳል።

አንዴ ቪዛ ካገኙ በኋላ የቆይታ ጊዜው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ይፈቅድ የነበረው አሠራርም ተቀይሯል።

በአዲሱ አሠራር የቪዛው የቆይታ ጊዜ ባይጠናቀቅም አንዴ ከአሜሪካ ከወጡ በኋላ በዚያው ቪዛ ተመልሰው መግባት አይችሉም።

ባለፈው ታኅሣሥ ላይ ደግሞ ከአምስት ሺህ በላይ የጥገኝነት መብት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ እንዳይባረሩ የአገሪቱ መንግሥት ቀደም ሲል ሕጋዊ ከለላ የተሰጠበት የአሠራር እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በዚህ አሠራር አማካኝነት አሜሪካ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በ60 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት ይህንን ውሳኔ በጊዜያዊነት አግዶታል።