በዓለም ላይ ዋነኛው የነዳጅ እጥረት መቼ ነበር የተከሰተው? አሁን ያጋጠመው ከቀደመው ምን ያህል የከፋ ነው?

የፎቶው ባለመብት, James Pozarik/Liaison via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለዓለም የነዳጅ እና ኃይል አቅርቦት መሠረት የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የአገራትን ምጣኔ ሃብት ወዳልተጠበቀ ቀውስ እየወሰደ ይገኛል።

አንድ ወር ባለፈው የኢራን ጦርነት ምክንያት የተከሰተው ምስቅልቅል ዓለም በአውሮፓውያኑ በ1970 ከገጠማት ቀውስ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች መታየት ጀምረዋል።

በአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ መላው ዓለምን ያናወጠው የነዳጅ ቀውስ በምን ምክንያት ነበር የተከሰተው? አሁን ከተከሰተው የነዳጅ እጥረት ጋርስ እንዴት ይነጻጸራል?

የነዳጅ ዝውውር ባለሙያ ላርስ ጃንሰን እንደሚናገሩት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በ1970 ከተስተዋለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ "የረዘመ ጊዜ" ሊወስድ የሚችል ነው።

የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ፌዝ ቢሮል "ዓለም በታሪክ ያልታየ የኢነርጂ አቅርቦት ችግር እየገጠማት ነው" ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

"በ1970 ካየነው የአሁኑ የበለጠ ሰፊ ነው። የነዳጅ ዋጋ እጅጉን ጨምሯል። ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከታየው በባሰ ሁኔታ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋም ንሯል" በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ዓለም አቀፍ የሸቀጥ ዝውውር እና ንግድን የሚያውክ ቢሆንም እንኳ፤ አሁን ያለው ዓለም ከዚህ ቀደም በተሻለ ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ነው ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎችም አሉ።

በ1970ው የነዳጅ ቀውስ ምን ተከተሰ?

የአውሮፓውያኑ 1970 የነዳጅ ቀውስ ከአሁኑ "በእጅጉ የተለየ ነው" ሲሉ የክሪስቶል ኢነርጂ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ካሮል ናኪል ይናገራሉ።

"የዚያን ጊዜው የነዳጅ ቀውስ ሆነ ተብሎ በተወሰደ የፖሊሲ ለውጥ የተከሰተ ነበር" ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 1973 ላይ የአረብ ነዳጅ አምራቾች በአሜሪካ ወገን ባሉ አገራት ላይ ማዕቀብ ጥለው ነበር።

በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤል እና በአረብ አገራት መካከል በተከሰተው የዮም ኪፑር ጦርነት ወቅት እስራኤልን የደገፉ አገራት ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው።

የአረብ አገራት የፖሊሲ ለውጥ በእስራኤል ደጋፊ አገራት ላይ የነዳጅ ምርት ማዕቀብ መጣልን ያካተተ ነበር።

"በወራት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በአራት እጥፍ ጨምሮ ነበር" ሲሉ ባለሙያዋ ያስታውሳሉ።

በከፍተኛ መጠን ነዳጅ ይጠቀሙ የነበሩ አገራት የነዳጅ ክምችት ቆጥበው እና ከፋፍለው ለመጠቀም ተገድደዋል።

የተፈጠረው ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት እና የፋይናንስ ቀውስ ዘላቂ ጫና ያሳደረ እንደሆነም ይናገራሉ።

በኩዊንስ ዩኒቨርስቲ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ቲራናን ሄኒ እንደሚናገሩት፤ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በመላው ዓለም የዋጋ ንረትን አስከትሏል።

"ስለዚህ ንግድ እየተቀዛቀዘ እና የሥራ አጥነት መጠን እየጨመረ ነው" ይላሉ።

በተለያዩ አገራት የሥራ ማቆም አድማዎች እንዲካሄዱ መነሻ እንደሆነ ጠቅሰው "ማኅበራዊ መስተጋብርን ያወከ፣ አለመረጋጋትን የፈጠረ እና ኑሮን ለመግፋት እየታገሉ ያሉ ሰዎችን ሕይወት የበለጠ ያመሰቃቀለ ነው" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ ከ1973 እስከ 1975 ድረስ ባሉት ዓመታት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የምጣኔ ሃብት ቀውስ ገጥሟቸዋል።

የቴድ ሂል ወግ አጥባቂ መንግሥት በ1974 የወደቀውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ አይዘነጋም።

አሁን የተፈጠረው የነዳጅ ቀውስ ምን ይመስላል?

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን እያሳለፈ አይደለም።

ይህም ከባሕረ ሰላጤው አገራት የሚነሱ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የሌሎችም ሸቀጦችን ዝውውር አስተጓጉሏል።

ከዓለም አንድ አምስተኛው የነዳጅ አቅርቦት የሚተላለፈው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነዳጅ በወሽመጡ በኩል እንዲተላለፍ የተለያዩ ጥረቶች አድርገዋል።

የአሜሪካ አጋር አገራት የጦር መርከቦች ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲልኩ ትራምፕ ጥሪ አቅርበዋል። ኢራን መርከቦችን የማታሳልፍ ከሆነ የከፋ ጥቃት እንደሚሰነዘርም ዝተዋል።

የነዳጅ ዝውውር ባለሙያው ጃንሰን እንደሚሉት ከአንድ ወር በፊት ከባሕረ ሰላጤው አገራት የተነሳ ነዳጅ በተለያዩ አገራት የነዳጅ ማጣሪያ የደረሰው በቅርቡ ሲሆን፣ ይህ ዝውውርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚገታ ይሆናል።

"የሆርሙዝ ወሽመጥ ነገ ቢከፈት እንኳን አሁን የምናየው የነዳጅ እጥረት ይባባሳል። የኃይል አቅርቦት ዋጋ ይጨምራል። ቢያንስ ከስድስት እስከ 12 ወራት የዋጋ ንረቱ ይቀጥላል" ይላሉ።

የአሁኑ የነዳጅ ቀውስ ከ1970ው የከፋ ሊሆን ይችላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክሪስቶል ኢነርጂ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ካሮል እንደሚሉት አሁን ያለው የዓለም የነዳጅ ገበያ ከ1970ው በተለየ የተሰባጠረ ነው።

ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የነዳጅ መጠን መቀነሱን ያስረዳሉ። የነዳጅ ዋጋ ቢጨምርም ቀውሱ ከዚህ ቀደሙ ጋር ሲነጻጸር የከፋ እንደማይሆን ያምናሉ።

"ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እጥረት እያስተወልን ነው። በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው ሊባል የሚችል ነው። ሆኖም የዓለም ገበያ በ1970 ከነበረው አሁን ጠንካራ ነው" ይላሉ።

"አሁን ያለው የነዳጅ ገበያ የተሰባጠረ ነው። ነዳጅን ብቻ አማራጭ ከማድረግ የተሻለ አካሄድም አለ። ድንገተኛ ነገር ሲከሰት ለመቋቋም ዝግጅትም ተደርጓል" ሲሉም ያክላሉ።

በናቲክስ ሲአይቢ የጥናት ኃላፊ የሆኑት ጆኤል ሀንኮክ እንደሚናገሩት፤ በ1970 የነበረው የነዳጅ ማዕቀብ ያደጉ አገራት ላይ ያነጣጠረ ነበር። እነዚህ አገራትም የነዳጅ ቀውስን ለመቋቋም "ፖለቲካዊ አቅም" ነበራቸው።

አሁን የተፈጠረው የነዳጅ ቀውስ በአንጻሩ ታዳጊ አገራትን የሚጎዳ ነው።

"እነዚህ ታዳጊ አገራት ቀውሱን ለመቋቋም የገንዘብ እንዲሁም ተቋማዊ አቅም የላቸውም" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

በ1970 ከነበረው በተለየ አሁን ላይ የነዳጅ ቀውስ ከኢነርጂ ቀውስ ጋር የሚዛመድ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

አሁን ከተፈጠረው ምስቅልቅል መውጣት የሚቻለው ጦርነቱ ሲቆም መሆኑን ያስረዳሉ።

በኩዊንስ ዩኒቨርስቲ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ቲራናን ሄኒ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ዓለም ምጣኔ ሃብትን በተሻለ መንገድ መገንዘቡን እና በርካታ አገራት የነዳጅ ክምችት ያላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

"ችግሩ የጎላ የሚሆነው ሲራዘም ነው። ይህም የወደፊቱን ጊዜ ያጨልመዋል። የተሻለው መፍትሔ የሚሆነው ግጭቱ በአፋጣኝ ቆሞ ወደ መረጋጋት መመለስ ነው" ይላሉ።