በነዳጅ እጥረት ምክንያት አገር አቋራጭ የሕዝብ ጉዞዎች እየታጠፉ መሆኑን የተሽከርካሪ ማኅበራት ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Transport and Logistics

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በናፍጣ እጥረት ምክንያት አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አቅራቢዎች ራቅ ወዳሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚደረጉ ረጅም ጉዞዎችን እያጠፉ እንደሆነ ማኅበራት እና ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን በበኩሉ በነዳጅ እጥረት ምክንያት አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች የሚያደርጓቸው ጉዞዎች "ከ35 እስከ 40 በመቶ" መቀነሳቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።

38ተኛ ቀኑን የያዘው ኢራን ጦርነት በነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል እና በዋጋ ላይ በፈጠረው ጭማሪ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበት 180 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ሳይደርስ መቅረቱን መንግሥት አስታውቋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከኢትዮጵያ የነጭ ናፍጣ አቅርቦት ውስጥ 60 በመቶው ይገባ የነበረው ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ምክንያት የነዳጅ ምርቷን ማጓጓዝ ካልቻለችው ኩዌት ነው።

ይህንን ተከትሎም በቀን "በአማካይ 9.1 ሚሊዮን ሊትር" ሲቀርብ የነበረው ነጭ ናፍጣ አቅርቦቱ በ50 በመቶ ገደማ ቀንሶ "4.5 ሚሊዮን ሊትር" መድረሱን ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የሚያወጣው ዕለታዊ የማደያዎች ነዳጅ ሥርጭት መረጃ እንደሚያሳየው በከተማዋ ካሉ 120 ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም. ላይ ናፍጣ ያላቸው 26ቱ ብቻ ናቸው። በአንጻሩ 65 የአዲስ አበባ ነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን አላቸው።

ይህ ሁኔታ ነጭ ናፍጣ የሚጠቀሙትን አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አቅራቢዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ብርሃኔ ዘሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ የነዳጅ አቅርቦት "ትንሽ ትንሽ" እንደነበረ የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ "ከጦርነቱ በኋላ ተባብሶ ቀጥሏል" ብለዋል። ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት "ሦስት እና አራት ቀናት" እየተሰለፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በነዳጅ እጥረቱ ምክንያት አገር አቋራጭ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ሚያደርጓቸው ጉዞዎች "ከ35 እስከ 40 ፐርሰንት ቀንሷል" ብለዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ "ተሽከርካሪዎች ከዚህ ነዳጅ አግኝተው እንኳ ቢሄዱ ከዚያ ለመመለስ ነዳጅ ስለማያገኙ ባይሄዱ ይመርጣሉ።"

ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ማኅበር ኃላፊም "መመለሻ ነዳጅ ካላገኘ ተሽከርካሪው እዚያው ነው የሚቀረው፤ ይህ ብቻም ሳይሆን በአላስፈላጊ ተጨማሪ ዋጋ በኮንትሮባንድ ንጹህ ያልሆነ ነዳጅ ሊገዛ ይችላል" ሲሉ ለተጨማሪ ወጪም እንደሚዳረጉ አስረድተዋል።

ኃላፊ እንደሚናገሩት አብዛኛውን ጊዜ ተሽከርካሪዎች በሚጓዙበት ስፍራ መመለሻ ነዳጅ ስለማያገኙ መኪናቸው መያዝ በሚችለው ነዳጅ ልክ ያሉ ርቀቶችን እየተጓዙ ነው። ነዳጅ ባለመኖሩ ምክንያት "የማይኬድባቸው መስመሮች" እንዳሉም ገልጸዋል።

ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ ነዳጅ መቅዳት ቢችሉም እንኳ ለቀናት እንደሚሰለፉ አንስተዋል። "ያ ደግሞ ሕዝብ ጭኖ ደግሞ አይሆንም" ብለዋል።

"ለምሳሌ ወደ ሐዋሳ የሚደረግ ጉዞ ላይ ችግር የለም። የተሽከርካሪው ሰልቫቲዮ [የሚይዘው ነዳጅ] አድርሶ ይመልሰዋል። ጅማም አድርሶ ይመልሰዋል።

"ለምሳሌ ሞያሌ፣ ሚዛን፣ ጋምቤላ ያሉ ርቀቶች ላይ የግድ መንገድ ላይ ነዳጅ መቅዳት መቻል አለበት። እነዚህ ቦታዎች ላይ ግን በአግባቡ ነዳጅ ስለማይደርስ፤ ቢኖርም ዋና ከተሞች ስለሚሆን፣ እዚያም ደግሞ ሰልፍ ስለሚኖር […] ተሽከርካሪው ይቸገራል" ብለዋል።

ኃላፊው በምሳሌነት የጠቀሱት ከአዲስ አበባ ወደ ሞያሌ የሚደረግ ጉዞ መስተጓጎል እየገጠመው እንደሆነ ቢቢሲ ከተጓዦች ተረድቷል።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ተጓዥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከሞያሌ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለመኖሩ በሦስት ተሽከርካሪዎች አቆራርጦ አዲስ አበባ መድረሱን ገልጿል።

ተሳፋሪዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ ባስ ውስጥ ከተሳፈሩ በኋላ ሻሸመኔ ከተማ ላይ ለመውረድ እንደተገደዱ እና አሽከርከሪው ወደ መዲናዋ "መሄድ ብፈልግም ናፍጣ የለኝም፤ አዲስ አበባ ላደርሳችሁ አልችልም" የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው አስረድቷል።

"አዲስ አበባ መግባት የነበረብን ሰዎች አስር ሰዓት ተኩል በኋላ ሻሸመኔ ገባን፤ እዚያም ተመሳሳይ [የነዳጅ] ችግር አለ። በሚታወቅ ሰው ደውለን መኪና ሙሉ ሃይሩፍ ተከራይተን ሌሊት ስድስት ሰዓት ገባን" ሲል ያጋጠመውን አስረድቷል።

በነዳጅ እጥረቱ ምክንያት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በመቀነሱ የተነሳም የትኬት ዋጋ ከመደበኛው አሠራር ውጪ በሆነ መንገድ በጨመረ ዋጋ እየተሸጠ ስለመሆኑ እማኝነቱን ሰጥቷል።

የፌደራል መንግሥት በዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ ምክንያት የተፈጠረውን የአቅርቦት ችግር ለማስተዳደር ነዳጅ በቅድሚያ የሚያገኙ አካላት ዝርዝርን አውጥቷል።

"የከተማ እና አገር አቀፍ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች" በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ ሲሆን "በናፍጣ የሚሠሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ" አሠራር እንደሚተገበርም ተገልጾ ነበር።

የከተማ እና አገር አቀፍ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም አፈጻጸሙ ላይ እንቅፋት እያጋጠማቸው መሆኑን ሁለት የትራንስፖት ማኅበራት ተናግረዋል።

መንግሥት በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት መቅረብ ያልቻለውን የነዳጅ አቅርቦት ለማካካስ "ከተባራሪ ገበያ" ከፍ ባለ ዋጋ ነዳጅ እየገዛ መሆኑን አስታውቋል።