በወልቃይት እና ሁመራ የትግራይ ተወላጆችን "እንቅስቃሴ የሚገድቡ አድሏዊ አሰራሮች" መዘርጋታቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, hrw/getty images
በአወዛጋቢዎቹ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች "መታወቂያ እንዳያገኙ" እና "ፈቃድ ሳይኖራቸው ጉዞ እንዳያደርጉ" የሚከለክሉ "አድሎአዊ አሰራሮች" ተዘርግተዋል በማለት ሂውማን ራይትስ ዎች ከሰሰ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም የኢትዮጵያ አጋር የሆኑ አካላት "እንደ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ" ያሉ አመራሮችን "ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ" እንዲጥሉም ጠይቋል።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና አጋሮቻቸው በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን "እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚያደርገውን አያያዝ ችላ ለማለት የወሰኑ ይመስላል" ሲል ወቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሂውመን ራይት ሰዎች ሪፖርት ላይ እስካሁን ድረስ ምንም ያለው ነገር የለም።
ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከትግራይ ጦርነት መነሳት ወዲህ በአማራ ክልል በተዋቀረው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሥር በሚተዳደሩት አካባቢዎች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ይፈጸማል ያለውን ግፍ የዘረዘረው ረቡዕ ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
ተቋሙ ሪፖርቱን የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚነሱባቸው አካባቢዎች ይፈጸማሉ ስላላቸው ጥሰቶች ሪፖርት ያዘጋጀው ስፍራው ላይ የሚገኙ እና ከወራት በፊት የተሰደዱ ነዋሪዎችን "በርቀት" አነጋግሮ መሆኑን ገልጿል።
ከእርዳታ ሠራተኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ባለሙያዎችን መረጃ እንዳሰባሰበም ጠቅሷል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት "በመቶ ሺህዎች" የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከእነዚህ አካባቢዎች "በግዳጅ" መፈናቀላቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ የትግራይ ተወላጆች አሁንም ድረስ "በባለሥልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች" ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ከስሷል።
ባለሥልጣናቱ "የትግራይ ተወላጆች በዘፈቀደ እያሰሩ እና እንቅስቃሴያቸውን፣ የሥራ ዕድላቸውን እንዲሁም አገልግሎቶችን የማግኘት መብታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚገድብ አድሎአዊ ሥርዓት እየዘረጉ ነው" ብሏል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር "በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በሁሉም የሕይወት ዘርፎቻቸው ላይ ከፍተኛ እና ከሰብአዊነት የሚያጎድል እገዳዎች እየተጣሉባቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ገለጻ፤ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች "ከከተማቸው ለቅቀው ለመሄድ" ከዞን አስተዳደሩ "ጊዜያዊ ፈቃድ" ማግኘት አለባቸው።
ይህንን ፈቃድ ማግኘትም አስቸጋሪ እንደሆነ ከነዋሪዎቹ መስማቱን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ "የአካባቢው ባለሥልጣናት ፈቃድ የሚሰጡት ከሕክምና ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ወይም ዕድሜያቸው የገፋ የቤተሰብ አባላትን ለመርዳት ሲሆን ብቻ" መሆኑን ያስረዳል።
ይህ ፈቃድ የሌላቸው ነዋሪዎች መዘዋወር የሚችሉት "በሚኖሩበት ወረዳ እና ሑመራ ከተማ ውስጥ ብቻ" እንደሆነ የሚገልጽ የጉዞ ሰነድ መመልከቱንም ተቋሙ አስታውቋል።
በተጨማሪም ሂውማን ራይትስ ዎች የአካባቢው ባለሥልጣናት የትግራይ ተወላጆች "እንደ መታወቂያ ያሉ ወሳኝ ሰነዶችን" እንዳያገኙ እየተከለከሉ ነው ሲል ከስሷል።
ተቋሙ ያነጋገረው አንድ የትግራይ ተወላጅ "መታወቂያ ተከልክለናል። ስለዚህ የባንክ አካውንታችንን መጠቀም አንችልም፣ መሬታችንን ማግኘት አንችልም ማለት ነው። የትግራይ ተወላጆች የሚፈቀድላቸው በቀን ሠራተኝነት እንዲሰሩ ብቻ ነው። እዛም እንኳ እንሰደባለን፣ እንደበደባለን" እንዳለ መግለጫው ላይ ሰፍሯል።
የትግራይ ተወላጆች በሙያቸው እንዳይቀጠሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ መታወቂያ አለመኖር እንደሆነም መግለጫው ያስረዳል። ተቋሙ ያነጋገራቸው የትግራይ ተወላጆች ሥራ የሚያገኙት በእርሻ ስፍራዎች የቀን ሰራተኛ ሆኖ ለመስራት ብቻ እንደሆነ መግለጻቸውን በሪፖርቱ አካትቷል።
በእነዚህ ምክንያቶች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት "በትግራይ ተወላጆች ላይ በሚፈጽሟቸው የዘፈቀደ እስሮች" ምክንያት ተጨማሪ ነዋሪዎች ከአካባቢው በመሸሽ በጦርነቱ ወቅት የተፈናቀሉትን "740,000" ዜጎች እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጿል።
የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ አጋሮቻቸው የምዕራብ ትግራይ ቀውስን ችላ ማለት እንዲያቆሙ" ጠይቀዋል። በጦርነቱ ወቅት የታየውን "የጅምላ መፈናቀል ያቀነባበሩ ሰዎች" በመጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ሰዎች "የሚመለሱበትን ሁኔታ ሊወስኑ አይገባም" ብለዋል።
"ይልቁንም ሥልጣናቸው መነሳት እና በመጨረሻም ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ማለታቸው በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
የተቋሙ አክሎም፤ ኢትዮጵያ አጋሮች በዞኑ "በቀጠለው በደል" ምክንያት በአሁኑ ወቅት ወደ ምዕራብ ትግራይ በሰላም ለመመለስ የሚያስችል እንደሌለ ግልጽ ማድረግ አለባቸው" ሲል አሳስቧል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ " ኮሎኔል ደመቀ [ዘውዱ]ን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ወቅት እና የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተፈጸመ በኋላ ለተፈጸሙ ከባድ በደሎች ተጠያቂ የሆኑ ባለስልጣናትን ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ መጣል አለባቸው" ብሏል።















