ዜሌንስኪ የአሜሪካ መልዕክተኞች ኪዬቭን አለመጎብኘታቸው 'አክብሮት የጎደለው' ነው አሉ
የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካ መልዕክተኞች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር ኪዬቭን ሳይረግጡ ወደ ሞስኮ ያደረጉትን ጉብኝት "አክብሮት የጎደለው" አድርገው እንደሚቆጥሩት ተናገሩ።
ሁለቱ መልዕክተኞች ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የታለሙ የተኩስ አቁም ውይይቶች እየተጠናከሩ በሄዱበት ወቅት ሁለት ጊዜ ሩሲያን ጎብኝተዋል።
ወደ ሞስኮ ስምንት ጊዜ ያህል ያቀኑት ዊትኮፍ ቭላድሚር ፑቲንን በብዙ አጋጣሚዎች አግኝተዋቸዋል።
እሳቸውም ሆኑ ኩሽነር ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኪዬቭን አቅንተው አያውቁም።
"ኪዬቭ ሳይመጡ ወደ ሞስኮ ብቻ ማቅናታቸው አክብሮት የጎደለው ነው" ሲል ዜለንስኪ ከዩክሬን የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
"ውስብስብ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዳለን እረዳለሁ… [መምጣት] ካልፈለጉ በሌሎች አገሮች መገናኘት እንችላለን" ሲሉ አክለዋል።
የቀድሞ የሪል እስቴት ከበርቴ የነበሩት ዊትኮፍ የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ሲሆኑ ኩሽነር ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አማች ናቸው።
ዜሌንስኪ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ዩክሬንን ለመጎብኘት እያሰቡ እንደነበር ቢገልጹም ከኢራን ጋር በተደረገው የአሜሪካ እና የእስራኤል ጦርነት ምክንያት ጉዞው እውን ሳይሆን ቀርቷል።
በሩሲያ፣ በአሜሪካ እና በዩክሬን መካከል የተደረገው የሦስትዮሽ ውይይት ለመጨረሻ ጊዜ የተከናወነው በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ነበር።
ሁለት ሳምንት ሳይሞላ አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን ማጥቃት በመጀመራቸው ምክንያት ከአራት ዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየውን የዩክሬን ጦርነት የማስቆም ትኩረታቸውን ቀይረዋል።
ዊትኮፍ እና ኩሽነር ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ ወደ ፓኪስታን የሚጓዙ የአሜሪካ የድርድር ቡድን አባል ናቸው። ዜለንስኪ የአሜሪካ ትኩረት በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ መሆኑን አምነዋል።
"ያም ቢሆን ግን ለእኛ ከአሜሪካውያን ጋር መተባበር መቀጠል አስፈላጊ ነው" ሲሉ አክለዋል።
የሩሲያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት በዩክሬን ውስጥ የነበረውን ጦርነት የሚያስቆም ዕቅድ ላይ እየሰሩ በነበረበት በ2025 የተኩስ አቁም ንግግሩ ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ወደ መሆን እየተቀየረ ቢመጣም ለኪዬቭ የማይመቹ በርካታ ውሎችን ያካተተ ነበር።
ዩክሬን በውይይቱ ውስጥ ለመሳተፍ ጥረት አድርጋለች።
በየካቲት ወር ሞስኮም ሆነች ኪዬቭ እንደ ጦር ግንባር መስመርን እና ተኩስ አቁም ክትትልን ጨምሮ በአንዳንድ "ወታደራዊ ጉዳዮች" ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ዩክሬን ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሩሲያ በግዳጅ የወሰደቻቸውን የዩክሬን ልጆች እንድትመልስ የጠየቀችው ጥያቄ እና ሞስኮ በኪየቭ "የአገዛዝ ለውጥ" ላይ ያላት ጽኑ አቋምን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች አሁንም ድረስ አልተፈቱም።
ዋናው ጉዳይ ደግሞ የዩክሬን ምሥራቃዊ ዶንባስ ክልል ሁኔታ ነው። ሞስኮ ጦርነቱን ለማስቆም በምትኩ የዩክሬን ግዛት ለመውሰድ ያቀረበችው ጥያቄ በኪዬቭ ተቀባይነት አላገኘም። ሁለቱም ወገኖች ከአቋማቸው ዝንፍ ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ውይይቱን ባለበት እንዲቆም አድርጓል።
"በሁለት ተቃራኒ ዋልታ ባላቸው ቦታዎች መካከል ስምምነት እንፈልጋለን። እስካሁን ግን አላገኘነውም" ሲሉ የዜሌንስኪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ በየካቲት ወር ተናግረዋል።
በመጨረሻም ኪየቭም ሆነች ሞስኮ "ወይ መፍትሄ አግኝተን ይህንን ጦርነት እናስቆም፣ ካልሆነም ሁላችንም መፍትሄ እንዳላገኘን አምነን እርስ በእርሳችን መገዳደላችንን እንቀጥላለን። ከሁለቱ ነገሮች አንዱን መቀበል አለብን። ይህ በብቃት እና በሙያዊ መንገድ የምናደርገው ነገር ነው" ሲሉ አክለዋል።
ሩሲያ በ2022 ዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ስትጀምር የተጀመረው ጦርነት ለአራት ዓመታት ለዩክሬናውያን የዕለት ተዕለት እውነታቸው ሆኖ ቆይቷል።
ሰፊው የምሥራቅ ዩክሬን አካባቢ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ የኪዬቭ እና የሞስኮ ወታደሮች ከሰሜን ምሥራቅ ሉሃንስክ እስከ ደቡብ ኸርሰን ድረስ ባለው ረዥም ግንባር ውጊያ ቀጥለዋል።
በዩክሬን ውስጥ ያሉ ከተሞች መደበኛ የአየር ጥቃቶች የሚሰነዘርባቸው ሲሆን ሩሲያ ሲቪሎችን የሚገድሉ እና መሠረተ ልማቶችን ዒላማ የሚያደርጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን ትጠቀማለች።
ባለፈው ሳምንት በአንድ ምሽት ብቻ ሩሲያ ከ700 በላይ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎች አስወንጭፋ ቢያንስ 18 ሰዎችን ገድላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን በሩሲያ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ በረጅም ርቀት ድሮኖች ወደቦች፣ ፋብሪካዎች፣ ዴፖዎች እና የነዳጅ ተርሚናሎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም