በጋና ያላለቀ የቤተክርስትያን ሕንጻ ተደርምሶ አምልኮ ላይ የነበሩ ሦስት ሰዎች ሞቱ
በጋና አንድ ያላለቀ የቤተክርስትያን ሕንጻ ተደርምሶ አምልኮ ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ቢያንስ ሦስቱ መሞታቸው ተገለጸ።
አደጋው የደረሰው በመዲናዋ አክራ ሲሆን፣ አማኞች እንደ ቤተ ክርስቲያን የሚጠቀሙበት በግንባታ ላይ የነበረ ባለ ሦስት ወለል ሕንጻ ተደርምሶ የሁለት ሴቶችን እና የአንድ ወንድ ምዕመናን ሕይወት ቀጥፏል።
የጋና የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሙንታካ ሞሐመድ ሙባረክ እንደተናገሩት በአደጋው 20 ሰዎችን መታደግ የተቻለ ሲሆን፣ በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።
እስካሁን ሙሉ በሙሉ ባይረጋገጥም በሕንጻው ፍርስራሽ ውስጥ የተደበቀ ሰው አለመኖሩን ከ90 በመቶ በላይ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሊቱን ሙሉ ፍለጋ ሲያደርጉ አድረዋል።
በመዲናዋ አክራ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ አደጋው የተከሰተ ሲሆን፣ የአደጋው ዋና መንስዔ ምን እንደሆነ ምርመራ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሕንጻው ምንም እንኳን ግንባታው ያላለቀ ቢሆንም ለብዙ ዓመታት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ "ይህ ለሁላችንም በጣም አሳዛኝ ቀን ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሩ ሕንጻው ከመደርመሱ በፊት በውስጡ ምን ያክል ሰዎች እንደነበሩ ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሰጡትን ፈጣን ምላሽ አድንቀዋል።
አንድ ከሕንጻው ጀርባ ቢዝነስ የሚያንቀሳቅስ ሰው በሰጠው ምስክርነት፣ መጀመሪያ ከፍተኛ ድምጽ መስማቱን ያንን ተከትሎ ከቤቱ ሲወጣ ሕንጻው እየተደረመሰ መመልከቱን ተናግሯል።
አማዱ የተባለው የአካባቢው ነዋሪ "ከፍተኛ አቧራ ነበር። በዚህም ምክንያት ከጀርባ ምን እንደተከሰተ ማየት አልቻልኩም" ብሏል ለቢቢሲ።
በኋላ ላይ ወደ ስፍራው ሲያመራ ከውስጥ ሆነው ሰዎች ሲጮሁ እና ፖሊስ ሲጠሩ እንደነበርም ገልጿል።
ሌላኛው ነዋሪ አደጋ ያደረሰው ሕንጻ ደካማ የግንባታ ሥርዓት እንደነበረው ገልጿል።
"ሕንጻው ደካማ እንደሆነ ማንኛውም የአካባቢው ሰው ያውቃል።
እንዲያ ሆኖ ነው አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገው" በማለት ሌላ የዓይን ምስክር አክሏል። ሃፊዝ የተባለው ይህ የዓይን እማኝ እንደተናገረው "ሕንጻው አንድ ቀን እንደሚደረመስ ያስታውቅ ነበር" ብሏል።
የሕንጻው ፍርስራሽ እየተወገደ ሲሆን ምናልባትም በውስጡ የቀረ ሰው ካለ በሚል ፍለጋ እየተካሄደ ነው።
አደጋውን ተከትሎ በአገሪቱ የሚደረጉ አንዳንድ ግንባታዎች ላይ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋትን እና ጥርጣሬን ፈጥሯል።
ይህ አደጋ ሰዎች ከአሁን በፊት የደረሱ የሕንጻ መደርመስ አደጋዎችን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል።
የጋና የኢንጂነሪንግ ኢንስቲቲዩት ፕሬዝዳንት ሉድዊግ አናንግ ሄሴህ እንደተናገሩት "የሕግ ተፈጻሚነት እስካልተተገበረ ድረስ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ይቀጥላሉ" ብለዋል።
"ሕጉ አለን፤ መመሪያው አለን፤ እናም ነገሮችን በትክክል ከተገበርን ችግሮች አይገጥሙንም"
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም