በጋዛ የእስራኤል ጥቃት እና የታጣቂዎች ግጭትን ተከትሎ አስር ሰዎች ተገደሉ
የፎቶው ባለመብት, Reuters
በማዕከላዊ ጋዛ በእስራኤል የአየር ድብደባ እንዲሁም በሐማስ እና በእስራኤል በሚደገፈው የፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 10 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።
ጥቃቶቹ ከማጋዚ የስደተኞች ካምፕ በስተምስራቅ ከሚገኙት የሚሊሻ አባላት ጋር የተጋጩትን የሐማስ የደህንነት ሠራተኞችን ዒላማ እንዳደረጉ ተዘግቧል።
ከሠራተኞቹ መካከል ስንት ሰዎች በጥቃቶቹ ምክንያት ወይንም በውጊያው መካከል እንደሞቱ ግልጽ አይደለም።
በዴር አል-ባላህ የሚገኘው የአል አቅሳ ሆስፒታል ቃል አቀባይ እንዳሉት በጥቃቱ እና በግጭቱ የተገደሉ የ10 ሰዎች አስከሬን ወደ ሆስፒታላቸው መጥቷል።
በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና አንዳንዶቹ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል።
ከእስራኤል ጦርም ሆነ ከሐማስ ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም።
ሰኞ ዕለት ታጣቂዎቹን ወደ ግጭት ያስገባውም ሆነ ለአየር ድብደባው ምክንያት የሆነው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ይሁን እንጂ የዓይን እማኞች እንዳሉት በእስራኤል የሚደገፉት ታጣቂዎች ከማጋዚ በስተምስራቅ የሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ ሲያቋቁሙ ከሐማስ የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን ይህም ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል።
እማኞቹም አክለውም የእስራኤል ድሮኖች ታጣቂዎቹን በመደገፍ በሦስት የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የሐማስ ወታደሮች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል ብለዋል።
እስራኤል እና ሐማስ ከስድስት ወራት ገደማ በፊት የተስማሙበትን የተኩስ አቁም ስምምነት በተደጋጋሚ በመጣስ እርስ በርሳቸው ይካሰሳሉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ በእስራኤል በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 723 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን ሐማስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በተኩስ አቁሙ ወቅት በፍልስጤም ቡድኖች በተፈፀሙ ጥቃቶች አምስት ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሰላም እቅድ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ እንዳይደረስ ካደረጉት ቁልፍ እንቅፋቶች አንዱ ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት ነው።
ባለፈው ሳምንት የሐማስ ልዑካን ቡድን በካይሮ ከግብፅ፣ ከኳታር እና ከቱርክ አደራዳሪዎች ጋር ተገናኝቶ በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ቦርድ የፍልስጤም ቡድኖች የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንዲያስወግዱ ላቀረበው ሀሳብ የመጀመሪያውን ምላሽ ሰጥቷል።
እሁድ ዕለት የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ እስራኤል በትራምፕ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሰላም ዕቅድ መሠረት ቃል የገባችውን ሳትፈጽም የጦር መሳሪያ ትጥቅ ስለመፍታት ንግግር እንደማይኖር አስታውቀዋል።
"የጦር መሳሪያ ጉዳይን በዚህ መንገድ መነሳቱን አንቀበልም" ሲሉ ባለፈው ዓመት በእስራኤል በተፈፀመ ጥቃት ሞክሼያቸው የተገደሉት አቡ ኡባይዳ ተናግረዋል።
አክለውም "ጠላት በታንክ በማውደም ከእኛ ሊወስደው ያልቻለውን በፖለቲካም ሆነ በድርድር ጠረጴዛ አይወስድም" ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቀደም ሲል ሐማስን "በቀላሉም ሆነ በከባድ መንገድ" ትጥቅ እንደሚፈታ አስጠንቅቀው ነበር።
አቡ ኡባይዳ በተጨማሪም የሐማስን ጦርነት በጋዛ በእስራኤልና በአሜሪካ እንዲሁም በኢራንና በአጋሮቿ መካከል ካለው ሰፊ ግጭት ጋር አያይዘውታል።
በኢራን የሚደገፉት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና በየመን የሁቲ ወታደሮች በእስራኤል ላይ የፈጸሙትን የሚሳዔል፣ የድሮን እና የሮኬት ጥቃቶችን ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የጀመረውን "ቅጥያ" ነው በማለት አድንቀዋል።
የጋዛ ጦርነት የተቀሰቀሰው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎች ከገደለ እና 251 ደግሞ ካገተ በኋላ ነው።
እስራኤል በጋዛ በሐማስ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ከ72,300 በላይ ሰዎች መግደሏን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም