ኤምሬትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከባድ ዋጋ እየከፈለች ያለችው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከሌሎቹ አገራት በበለጠ ኤምሬትስ የኢራን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ዒላማ ሆናለች
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ሁለተኛ ወሩን ሲይዝ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቴህራን ግልጽ ዒላማ እየሆነች መጥታለች።

በዚህ ጦርነት ኢራን የጥቃት አድማሷን እስራኤል ላይ ብቻ ከማድረግ ባሻገር በባሕረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት (GCC) አባል አገራትን ዒላማ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።

ይህ ቴህራን በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ለመምታት የሰጠችውን ዛቻ ወደ ተግባር መለወጧን ያሳያል።

እንዲሁም ትኩረቷ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ ማነጣጠሯ ከአቡ ዳቢ ጋር ያላቸው ግንኙነት አሁንም ጠንካራ ለሆነው ዋሽንግተንም ሆነ ለእስራኤል ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል።

ኢራን ግጭቱን በማስፋት ለሁሉም ወገኖች የጦርነቱን ወጪ ለመጨመር እና የባሕረ ሰላጤው አገራት አጋራቸው የሆነችውን ዩናይትድ ስቴትስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትቀበል ጫና እንዲያደርጉ ግፊት ለማድረግ ትጥራለች።

በምላሹም አቡ ዳቢ ለቴህራን ባልተለመደ መልኩ ከረር ያለ አነጋገር በመጠቀም የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ አሜሪካን እንደምትቀላቀል አስፈራርታለች።

ይህም ውይይትን እና መልካም ጉርብትናን ቅድሚያ ከሚሰጠው የቀደመ አቀራረቧ የተለየ መሆኑን ያሳያል።

ኢራን በባሕረ ሰላጤው ላይ የፈጸመችው ጥቃት ምን ያህል ነው?

ኢራን በተለይም በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እስራኤልን ሳይሆን የባሕረ ሰላጤ አገራትን ዒላማ አድርጋ ማጥቃቷን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መቀመጫውን በኳታር ያደረገው አል ጀዚራ እንደዘገበው፤ በመጀመሪያዎቹ 11 ቀናት ውስጥ የተፈጸሙት የጥቃት ቁጥሮች "እስራኤል የኢራን የመጀመሪያ ዒላማ አለመሆኗን ያሳያሉ።"

ይህንንም በማስረጃ ሲያስደግፍ ቴህራን ወደ አረብ አገራት 3,100 ጥቃቶች ስትሰነዝር ወደ እስራኤል ግን 433 ብቻ ፈጽማለች።

በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ ስለ ኢራን ጥቃቶች የዘገቡ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ያደረጉት መረጃ እንደሚያሳየው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ ዒላማ ሆና ቆይታለች።

የዱባይ የሕዝብ ፖሊሲ ምርምር ማዕከል ኃላፊ መሐመድ ባሃሩን ለአቡ ዳቢ ስካይ ኒውስ አረቢያ ቲቪ እንደተናገሩት፣ ቴህራን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ "በጣም ቀላሉ ታዳኝ" እና "በቀጣናው ተፅዕኖ ውስጥ የመጀመሪያው ዒላማ" እንደሆነች ያላትን እምነት የሚያሳይ ነው።

"ይህ ዒላማ ከተመታ ሌሎቹ እየተከታተሉ ይወድቃሉ የሚል የኢራን አመራር ግምት አለ" ሲሉ ባሃሩን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እአአ መጋቢት 14 በፉጃይራህ የነዳጅ ማምረቻ ዞን ላይ ኢራን በፈጸመችው የድሮን ጥቃት የተነሳ ጭስ ሲወጣ ታይቷል

ኤምሬትስ ለምን ዒላማ ሆነች?

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢራን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ በርካታ ቁልፍ ቦታዎችን አጥቅታለች።

ከእነዚህም መካከል የሃብሻን የጋዝ ማምረቻ፣ የአልዳፍራ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ፣ የፉጃይራህ ወደብ፣ የነዳጅ ማከማቻ ተቋማት እና የዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይገኙበታል።

በኢራቅ ሰሜናዊ ኩርዲስታን ክልል ኤርቢል የሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የቆንስላ ጽህፈት ቤትም በሁለት የድሮን ጥቃቶች ተመትቷል።

የኢራን ሠራዊት አካል የሆነው የከታም አል-አንቢያ ማዕከላዊ ዋና መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ኢብራሂም ዞልፋቃሪ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ "በኤሚሬት ከተሞች ውስጥ ካሉ ወደቦች፣ የጀልባች መቆሚያዎችን እና የአሜሪካውያን መጠለያ ስፍራዎች" እንዲርቁ አሳስበዋል።

ኢራን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ የሚገኙትን የአሜሪካ ሚሳዔል ማስወንጨፊያ ቦታዎች ላይ በማነጣጠር ራሷን የመከላከል "ሕጋዊ መብት" እንዳላት ተናግረዋል።

ኢራን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ግዛቷን በኻርግ ደሴት ላይ እና አቡ ሙሳ ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን ጨምሮ ጥቅም ላይ መዋሏን በመግለጽ ስትወነጅላት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ክሱን ውድቅ አድርጋዋለች።

ጥቃቶቹ በኤምሬትስ ኢኮኖሚ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደሩ?

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለረዥም ጊዜ የቀጣናው የኢኮኖሚ፣ የዲጂታል እና የሚዲያ ማዕከል መሆኗን ስትገልጽ የነበረው በጦርነቱ ከፍተኛ ተጽዕኖ ደርሶባታል።

ከኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱት ፈጣን የደኅንነት ስጋቶች በተጨማሪ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና የአክሲዮን ገበያ የሆነው ኤዲኤክስ ጄኔራል በባሕረ ሰላጤ ገበያዎች ከፍተኛውን ኪሳራ አስመዝግቧል።

ባለፈው አንድ ወር ውስጥ የአክሲዮቹ ገበያ በ11.42 በመቶ ቀንሷል ሲል የትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ መረጃ አመልክቷል።

ቱሪዝም እና አቪዬሽን በአየር ክልል መዘጋት እና በስፋት በሚደረጉ የበረራ ስረዛዎች ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 8 የታተመው የኢራቅ አል-ጋድ ፕሬስ በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንት ብቻ ስድስት የባሕረ ሰላጤው አውሮፕላን ማረፊያዎች 399 ሚሊዮን ዶላር እንዳጡ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኪሳራ 95 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት ዘግቧል።

የኢነርጂ ዘርፉም ቢሆን እንዲሁ ተጎድቷል።

የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በመዘጋቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዕለታዊ የነዳጅ ምርት ከግማሽ በላይ ቀንሷል ሲል ሮይተርስ ዘገቧል።

በአብዛኛው በምሥራቅ የመን ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው እና ፀረ ኤምሬትስ አቋም የሚያራምደው የአል-ማህሪያህ ቲቪ በመጋቢት 11 ቀን ዘገባው አቡ ዳቢ በግጭቱ ውስጥ "ትልቁ ተሸናፊ" እንደሆነች ጠቅሶ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላት ምሥል "እንደተበላሸ" አክሏል።

በተጨማሪም በሩዋይስ የነዳጅ ማጣሪያ እና በፉጃይራህ የነዳጅ ማዕከል ላይ በተሰነዘረው ጥቃት የነዳጅ ምርቷ መቀነሱን ጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቶች ምክንያት በረራዎች በመስተጓጎላቸው የቱሪስቶች እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተደናቅፈዋል

አቡ ዳቢ ምን ዓይነት እርምጃዎችን ወሰደች?

የኤሚሬትስ ባለሥልጣናት እና ሚዲያዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የቀጣናው "አስተማማኝ አገር" ተደርጋ እንድትታይ ለማድረግ ሞክረዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ለሕዝብ ባስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክት ዜጎችን እና ነዋሪዎችን "ሁሉም ነገር ደህና ነው" በማለት አገራቸው የመጡባትን ስጋቶች ለመጋፈጥ "ሙሉ በሙሉ ዝግጁ" መሆኗን አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሃማድ ሳይፍ አል ሻምሲ ሕዝቡ ኢራን በአገሪቱ ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች ፎቶግራፍ ከማንሳት፣ ከማተም ወይም ከማሠራጨት እንዲቆጠብ አስጠንቅቀዋል።

መመሪያው የኢራንን ጥቃቶች እና ውጤቶቻቸውን የሚያሳይ እውነተኛ ወይም የተፈበረከ ምሥል ያጋሩ በርካታ የውጭ ዜጎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።

የተያዙት ሰዎች ቢያንስ የአንድ ዓመት እስራት እና ከ27,200 ዶላር በላይ ቅጣት የሚያስቀጣ ክስ ይጠብቃቸዋል።

በኤምሬትስ እና ኢራን ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

አቡ ዳቢ እና ቴህራን መቀራረብ ማሳየት የጀመሩት በ2021 ነበር። በቴህራን እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ወደነበረበት ለመመለስ ቻይና ያደረገችውን ጥረት ተከትሎ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል።

የግንኙነቱ መሻከር ዋና ምክንያት በአብዛኛው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢኮኖሚ ጥቅሞች እና ከሪያድ ጋር ባለባት ፉክክር ውስጥ ራሷን እንደ ቀጣናው ኃይል አገር ለማስቀመጥ ካላት ፍላጎት የተነሳ ነው።

ይሁን እንጂ የአሁኑ ጦርነት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና የኢራን ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፣ ይህም ወደ መወነጃጀል እና ዛቻዎች እንዲያድግ አድርጓል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቴህራን የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘግታ ኢራን በግዛቷ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ምክንያት አምባሳደሯን እና ዲፕሎማቶቿን አስወጥታለች። በተጨማሪም በአቡ ዳቢ የኢራን አምባሳደር ሬዛ አሜሪን በመጥራት "ጠንካራ የተቃውሞ መልዕክት" አስተላልፋለች።

የባሕረ ሰላጤው አገራት ኅብረት ውይይትን የሚያጎላ መልዕክት ቢያስተላልፍም፣ አንዳንድ የሚዲያ ዘገባዎች ግን እንደሚጠቁሙት ከሆነ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኢራን ጋር በሚደረገው ውጊያ ውስጥ ለመሳተፍ "እየጣሩ" ነው።

ይህ ለውጥ በአቡ ዳቢ እና በቴህራን መካከል ግንኙነታቸውን ለማስተካከል ያለውን ማንኛውንም ዕድል ሊያደናቅፍ ይችላል።