ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ኤምሬትስ ሲደውሉ፤ የኢራን አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር ተነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያ ተገናኝተው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/fb

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያ ተገናኝተው ነበር
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ረቡዕ ዕለት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያ ደውለው፤ "ኢራን ዬኤኢ እና ሌሎች የቀጣናው አገራት" ላይ የምትፈጽመውን "ግልጽ ጥቃት" በድጋሚ ማውገዛቸውን የአገሪቱ የዜና ወኪል ዘገበ።

በተመሳሳይ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢራን እና የኢራቅ አምባሳደሮችን አግኝተው፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታ ተነጋግረዋል።

መካከለኛው ምሥራቅን እያመሰ ያለው የኢራን ጦርነት ያደረሰው የኢነርጂ ቀውስ ወደ ኢትዮጵያም እየተቃረበ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት የኢራን ጥቃት እየደረሰባቸው ላሉ የባሕረ ሰላጤው አገራት ያላትን አጋርነት ብትገልጽም፤ በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ከኢራን ዲፕሎማቶች ጋር ተገናኝተዋል።

ባለፉት ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ኳታር እና ኩዌት ደውለው በመካከለኛው ምሥራቅ ከተከሰተው ቀውስ አንጻር ለአገራቱ ያላቸውን አጋርነት የገለጹ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተጉዘዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደዋኖ ከድር የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደልን ተከትሎ በኢራን ኤምባሲ የተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው "ለኢራን መንግሥት እና ሕዝብ ሐዘናቸውን" ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ወደ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ትናንት ረቡዕ መጋቢት 9/2018 ዓ.ም. ወደ አቡ ዳቢ እንደደወሉ የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት የስልክ ውይይት "ወታደራዊ እንቅስቃሴ መባባሱን ተከትሎ በቀጣናው ስላለው ሁኔታ" እንዲሁም ጦርነቱ "በቀጣናውም እና ለዓለም አቀፍ ደኅንነት እና መረጋጋት ላይ ስለሚያስከትለው ከባድ መዘዝ" እንደተነጋገሩ ተገልጿል።

ዐቢይ "በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በሌሎች የቀጣናው አገራት ላይ የሚፈጸመውን የኢራን ግልጽ ጥቃት በድጋሚ" እንዳወገዙ የዜና ወኪሉ ዘገባ ያሳያል። የኢራን ድርጊት "የአገራቱን ሉዓላዊነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ህጎችን እና አሠራሮችን የሚጥስ" እንደሆነም ገልጸዋል ተብሏል።

የኤምሬቶች የዜና ወኪል "በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደኅንነቷን፣ ግዛቷን እና ሕዝቧን ለማስጠበቅ በምትወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ የኢትዮጵያን አጋርነት በድጋሚ አረጋግጠዋል" ሲል ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ቢን ዛይድ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታየው የጦርነት "መባባስ በአስቸኳይ መቆም" እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

"በቀጣናው መፍትሔ ያላገኙ ጉዳዮችን ተጨማሪ ውጥረቶች እና ቀውሶች በማያመጣ እንዲሁም ቀጣናዊ ደኅንነት እና መረጋጋትን በሚያስጠብቅ መልኩ በንግግር እና ዲፕሎማሲ" መፈታት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ

በሌላ በኩል በትናንናው ዕለት በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው ከሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር ሀደራ ጋር ተወያይተዋል። የኢራቅ አምባሳደር ሱለይማን ካሊድ አል-ዳይም በሚኒስትር ዲኤታው ጋር እንደተነጋገሩ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ሚኒስትር ዲኤታው የኢራን እና ኢራቅ አምባሳደሮች ያነጋገሩት በተናጠል ነው።

ሚኒስትር ዲኤታ ሀደራ ከሁለቱ አምባሳደሮች ጋር "ሀሳብ ከተለዋወጡባቸው" ጉዳዮች መካከል "ቀጣናዊ ሁኔታዎች" ይገኝበታል። "ንግግር በማድረግ በመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት እና የጋራ ደኅንነትን ለማስፈን አስፈላጊ መሆኑን" አፅንዖት እንደሰጡበት ተገልጿል።

በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም ተነጋግረዋል ተብሏል። "በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የስራ ስምሪት ዘርፎች" ያሉ ትብብሮችን ማስፋት ላይ ትኩረት እንደተሰጠም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።