ትራምፕ በኢራን ጦርነት ምክንያት ያራዘሙትን የቻይና ጉብኝት በግንቦት ወር ሊያደርጉ ነው

 ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቻይናን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘው በትራምፕ የመጀመርያ የሥልጣን ዘመን እአአ በኅዳር ወር 2017 ነበር
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በጀመሩት ጦርነት ምክንያት አራዝመውት የነበረውን የቻይና ጉብኝታቸውን በግንቦት ወር አጋማሽ ሊያደርጉ ነው።

ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር እአአ ከግንቦት 14-15 በቻይና እንደሚገናኙ ተናግረዋል።

ይህም ከአስር ዓመታት በኋላ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ቻይና ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል።

ትራምፕ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ዢን በዋሽንግተን ዲሲ ተቀብለው ለማስተናገድ ቀጠሮ ይዘዋል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የአገሪቱ ባለሥልጣናት "ለእነዚህ ታሪካዊ ጉብኝቶች ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው" ሲሉ ረቡዕ ዕለት ጽፈዋል።

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ኃላፊ ካሮላን ሌቪት ትራምፕ ጉብኝት የሚያደርጉባቸውን ቀናት አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ዢ ጉዞውን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ የቀረበውን ጥያቄ ተረድተው መቀበላቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ፕሬዝዳንት ዢ ፕሬዝዳንቱ በእነዚህ የጦርነት ዘመቻዎች ወቅት በሙሉ እዚህ መገኘታቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተረድተዋል" ሲሉ ሌቪት ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤጂንግ ትራምፕ በጠቀሱት ቀናት ላይ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠችም።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የትራምፕን ጉብኝት በተመለከተ ከዋሽንግተን ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታውቋል።

ጉዞው መጀመሪያ ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው እአአ መጋቢት 31 ሲሆን፣ ባለፈው ወር አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ ዘግይቷል።

በምላሹም ኢራን በባህረ ሰላጤው ውስጥ የእስራኤልንና የአሜሪካ አጋር አገሮችን በማጥቃት ለዓለም የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር ቁልፍ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን በመዝጋቷ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ተፈጥሯል።

ትራምፕ የአሜሪካ አጋሮች የባህር ወሽመጡን ለማስከፈት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። እንዲሁም ኢራን መተላለፊያውን ሙሉ በሙሉ ክፍት ካላደረገች በኢነርጂ ማምረጃቻ መሠረተ ልማቷ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ቻይናን በሚጎበኙበት ወቅት የኢራን ጦርነት ይጠናቀቅ እንደሆን የተጠየቁት ሌቪት "ሁል ጊዜም ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት አካባቢ ይገመታል፤ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ስሌቱን መስራት ትችላላችሁ" ብለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቻይናን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘው በትራምፕ የመጀመርያ የሥልጣን ዘመን እአአ በኅዳር ወር 2017 ነበር።

ትራምፕ እና ዢ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ባለፈው ኅዳር ወር በደቡብ ኮሪያ በተካሄደ ጉባዔ ወቅት ነበር።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከንግድ ግጭት እስከ የቴክኖሎጂ ፉክክር እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ባሉ ከባድ ፍትጊየዎች የተወጠረ ነው። የትራምፕ ጉብኝት ውጥረቱን ያቃልል መሆን አለመሆኑ የሚታይ ይሆናል።

ከትራምፕ ጉብኝት በፊት የቻይና የመንግሥት ሚዲያዎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ እና እንዲወያዩ ጥሪ ሲያደርጉ ተደምጠዋል።