የኢራን ጦርነት ኪም ጆንግ ኡን ስለ ሰሜን ኮሪያ ዕጣ ፈንታ እንዲሰጉ ያደርጋቸው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, BBC / Andro Saini
ኪም ጆንግ ኡን አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ አንዳንድ ጭንቅ ጥብብ የሚያደርጉ ሀሳቦች እንዲሰማቸው ሳያደርግ አይቀርም።
ሰሜን ኮሪያ ጥቃቶቹን "ተገቢ ያልሆነ ጠብ አጫሪ ጦርነት" በማለት ያወገዘችው በፍጥነት ነበር። ከሁሉም በላይ ሁለቱ አገራት ከአውሮፓውያኑ 1979 ጀምሮ "ፀረ አሜሪካ" አቋም በመያዝ "የደም ትስስር ያለበት ግንባር" ፈጥረው በሚሳኤል ልማት ላይ አጋርነት መሥርተዋል።
ሰሜን ኮሪያ ወደ ውጭ ለምትልካቸው የጦር መሣሪያዎች ኢራን ግንባር ቀደም መዳረሻ ነች ሲሉ ለቢቢሲ ስማቸው እንዳይገለጽ ያልፈለጉ የቀድሞ የአገሪቱ ዲፕሎማት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ሁለት ነገሮች ሰሜን ኮሪያን ከኢራን በተሻለ ስፍራ ላይ እንዳስቀመጧት ተንታኞች ይናገራሉ።
እነዚህም የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎቿ እና ቻይና ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2003 የኢራቅ ጦርነት ወቅት ሟቹ የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኢል ለ50 ቀናት ደብዛቸው ጠፋ።
እንደ ደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት መረጃ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ 600 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ሳምጂዮን ግቢ ውስጥ በተዘጋጀ ምሽግ ውስጥ ተደብቀው ነበር።
በአንጻሩ ግን የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቃት ከተገደሉ በኋላም ቢሆን ኪም ጆንግ ኡን ከሕዝብ ዕይታ አልተሰወሩም።
እንዲህ ዓይነቱ የተለየ ምላሽ በአንድ በኩል ሰሜን ኮሪያ በጥንካሬዋ ላይ ያላት እምነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ሲሉ በደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት ስር የሰሜን ኮሪያ ትንተና ቡድን የቀድሞ ዳይሬክተር ያንግ ዮንግ-ሴኦክ ተናግረዋል።
'የኒውክሌር ኃይል'

የፎቶው ባለመብት, AFP / KCNA VIA KNS
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃይልን የታጠቀች አገር ናት። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በ2025 አገሪቱን "ብዙ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ያሏት" በማለት "የኒውክሌር ኃያል" ሲሉ ገልጸዋታል።
የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም በ2025 ያወጣው ሪፖርት ሰሜን ኮሪያ ወደ 50 የሚጠጉ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አረሮች እና 40 ተጨማሪ ለማምረት የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች አሏት።
በሐምሌ 2024 ሰሜን ኮሪያ አጭር ርቀት የሚምዘገዘግ እና ጥቅም ላይ የሚውል ታክቲካዊ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት "በመጨረሻው ደረጃ" ላይ እንደምትገኝ ደቡብ ኮሪያ አስጠንቅቃለች።
ባለፈው ዓመት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ አሜሪካን ሊመታ የሚችል አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል ለመሥራት ተቃርባ ነበር።
ይህ የባለስቲክ ሚሳዔልን አቅጣጫ የሚመራው መሣሪያ ላይ እና በከባቢ አየር ውስጥ በሚምዘገዘግበት ወቅት አረሩን የመከላከል አቅሙ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማማን የለም ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) ኢራን "በጣም ትልቅ እና አሳሳቢ የኒውክሌር ፕሮግራም" እንዳላት ቢገልጽም፣ "የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለማምረት የተዋቀረ ፕሮግራም" እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ግን አለማግኘቱን አስታውቋል።
ኢራን በ2015 ከገባችው ታሪካዊ የኒውክሌር ስምምነት በኋላ፣ በዩራኒየም ማበልጸጊያ ፕሮግራሟ ላይ ተጨማሪ ገደቦችን ለማድረግ ተስማምታለች።
የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ፍተሻዎችም ሰፋ ብለው ተካሄደዋል፤ ይህም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለማዘግየት ረድቷል ሲሉ በአሳን የፖሊሲ ጥናቶች ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሙያ የሆኑት ጃንግ ጂ-ሂያንግ ተናግረዋል።
ነገር ግን ትራምፕ በ2018 ከኒውክሌር ስምምነቱ አገራቸውን ማስወጣታቸውን ተከትሎ ኢራን ኤጀንሲው የኒውክሌር ተቋሞቿን እንዳይፈትሽ መገደብ ጀምራለች።
የቁጥጥር ቡድኑ በሰጠው ምሥጢራዊ መረጃ ኢራን በሰኔ 2025 ከእስራኤል ጋር ባደረገችው ጦርነት ምክንያት ሁሉንም ትብብሯን አቋርጣለች።
ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ሙከራዋን በ2006 አድርጋ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሁሉንም የኤጀንሲውን ተቆጣጣሪዎችን አባራለች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምስት ተጨማሪ የኒውክሌር ሙከራዎችን አድርጋለች፤ የመጨረሻውን ደግሞ በአውሮፓውኑ 2017 አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በወቅቱ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነበረች። ይህም በ2018 እና 2019 በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ሁለት ታሪካዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ አድርጓል።
ኪም ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሳላቸው እና የዮንግቢዮን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫቸውን ለማፍረስ መደራደሪያ አቀረቡ። ነገር ግን ትራምፕ ተጨማሪ ነገር በመፈለጋቸው ንግግሮቹ ሳይሳኩ ቀርተዋል።
በአሜሪካ ስቲምሰን ማዕከል የኮሪያ ፕሮግራምን የሚመሩት ጄኒ ታውን፣ ሰሜን ኮሪያ አሁን በራስ የመተማመን ስሜት ያላት ይመስላል፤ ምክንያቱም በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ወደ ሩሲያ የበለጠ ቀርባለች ይላሉ።
ነገር ግን ትራምፕ እና ኪም ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ይመስላሉ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት የሰሜን ኮሪያ አቻቸውን ሲያሞግሱ ተደምጠዋል።
ኪም "ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ ልዩ ዕድል" መሆኑን ይገነዘባሉ፤ ነገር ግን "ግንኙነቱን ለማደስ መስዋዕትነት አይከፍሉም" ይላሉ ታውን።
ሰሜን ኮሪያ የኢራንን ጦርነት ባወገዘችበት ወቅት ትራምፕን በግልጽ አልኮነነችም።
ባለፈው ወር በፓርቲው ጉባዔ ላይ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት እንደምትጠብቅ ተናግራለች፤ ይህም ለውይይት በሯ ክፍት መሆኑን ያሳያል።
ቻይና፣ ሩሲያ እና የ"ኒውክሌር ተጋቾች'
መልከዓ ምድር ለሰሜን ኮሪያ አድልቷል፤ ቻይናን ትዋሰናለች ይህንንም ከአሜሪካ እና ከደመኛዋ ከደቡብ ኮሪያ ጋር እንደ ወሳኝ መሸሸጊያ አድርጋ ትመለከተዋለች።
የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ከወደቀ ቻይና ከፍተኛ የስደተኞች ፍልሰት ሊያጋጥማት ይችላል።
ለዚህም ነው በታሪክ በሁለቱ የኮሚኒስት አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት "እንደ ከንፈርና ጥርስ የቀረበ ነው" ተብሎ የሚገለጸው።
ከ1961 ጀምሮ ቻይና ከአገሪቱ ጋር በገባችው የጋራ የመከላከያ ስምምነት መሠረት ሰሜን ኮሪያ ከተወረረች ለመከላከል ቃል ገብታለች፤ ይህም ቤይጂንግ የፈረመችው ብቸኛው ስምምነት ነው።
ይህ ማለት ቻይና ሰሜን ኮሪያን ሁልጊዜ ፍጹም አጋር አድርጋ ትመለከታለች ማለት አይደለም። ምክንያቱም የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎቿ እየሰፉ መምጣታቸው ክልሉን እያናጋ ነው።
በሴዑል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ጃንግ ዮንግ-ሴኦክ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ በመምጣቱ ብዙም ደስተኛ ላትሆን ትችላለች ባይ ናቸው። በተለይም ሁለቱ አገራት በ2024 የመከላከያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ይህ ስሜት እያደገ መምጣቱን ተመራማሪው ያስረዳሉ።
ሆኖም ግን "ሰሜን ኮሪያ ለቻይና ስትራቴጂካዊ ጥቅም አላት… ቻይናም በስትራቴጂካዊ ፍላጎቶቿ በጣም ጽኑ አቋም አላት፤ ኪም ጆንግ ኡንም ይህንን በሚገባ ያውቁታል" ሲሉ አክለዋል።

ሰሜን ኮሪያ፣ ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ባላት የመልከዓ ምድር ቅርበት ምክንያት "የኒውክሌር ታጋቾች" አድርጋ ትይዛለች ሲሉ የአሳን ኢንስቲትዩቱ ጃንግ ተናግረዋል።
ሁለቱ ኮሪያዎች የሚለያዩት ከወታደራዊ እንቅስቃ ነጻ በሆነው ቀጣና አካባቢ ብቻ ሲሆን፣ ይህም 250 ኪሜ ርዝመት እና 4 ኪሜ ስፋት አለው፤ ከዋና ከተሞቻቸውም 200 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።
የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት አባል የሆኑት ጃንግ፣ የሴዑል ሜትሮፖሊታን አካባቢ በሰሜን ኮሪያ ቀጥተኛ የጥቃት ቀጣና ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ይናገራሉ።
"ደቡብ ኮሪያ እንደ እስራኤል፣ አሜሪካ ወይም ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሚሳዔሎችን ማክሸፍ ትችል እንደሆነ አጠያያቂ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ጃፓንም ብትሆን በሰሜን ኮሪያ ቀጥተኛ የጥቃት ቀጣና ውስጥ ትገኛለች፤ እና ሰሜን ኮሪያ የሚሳዔል ሙከራ በምታካሄድበት ወቅት በተደጋጋሚ ወደ ጃፓን ባሕር ታስወነጭፋለች።
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ወደ 80 ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮችን ያስተናግዳሉ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ጦር አባላት ይገኛሉ።
ተንታኞች ኪም በኢራን ጦርነት ወቅት የጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊኻሜኒ መገደል "የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ስላልነበረው አቅመ ቢስ" ሆኗል የሚል ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል ይላሉ።
ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ድርድርም ለአገዛዙ ኅልውና ዋስትና አይሰጥም ሲሉ በዲሲ የሚገኘው የኮሪያ-አሜሪካ የኢኮኖሚ ተቋም ባልደረባ ኤለን ኪም ተናግረዋል።
ታውን በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
"ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ዓመታት የኒውክሌር መከላከያ አቅሟን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ችግር ገጥሟት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት ኪም ጆንግ ኡን ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረጉ በእርግጠኝነት ያምናሉ። ምክንያቱም የኒውክሌር ታጣቂ አገርን ማጥቃት አደጋው በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚመረጥ መንገድ ሊሆን እንደማይችል ስለሚያውቁ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።















