ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት "ከእውነት የራቀ" እና "ወገንተኛ" በማለት አጣጣሉ
የፎቶው ባለመብት, Wolkayt Tegedie Setit Humera Zone
በአማራ ክልል ሥር የተመሰረተው 'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን' ምክትል አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በትግራይ ተወላጆች ላይ "አድሏዊ አሰራር" ተዘርግቷል መባሉን አስተባበሉ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች ረቡዕ ሚያዚያ 14፣ 2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች "መታወቂያ እንዳያገኙ" እና "ፈቃድ ሳይኖራቸው ጉዞ እንዳያደርጉ" የሚከለክሉ "አድሎአዊ አሰራሮች" ተዘርግተዋል በማለት ከስሷል።
'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን' ምክትል አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከቢቢሲ ጋር ባረጉት አጭር ቆይታ ሪፖርቱን "ከእውነት የራቀ" እና "ወገንተኛ" ሲሉ አጣጥለውታል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ በኮሎኔል ደመቀ ላይ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው መጠየቁንም በሚመለከት ሲመልሱ "እኔ ወንጀለኛ አይደለሁም" ብለዋል።
"እኛ እዚህ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አስተዳደር የትግራይ ሰዎችን በማንነታቸው የሚገፋ አስተዳደር የለንም" ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ከዚህ በፊትም "እኛን ለመወንጀል ሞክሮ እንደነበር" እናውቃለን ሲሉ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም፤ የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች ይፈጸማሉ ስላላቸው ጥሰቶች ሪፖርት ያዘጋጀው ስፍራው ላይ የሚገኙ እና ከወራት በፊት የተሰደዱ 40 ነዋሪዎችን አነጋግሮ መሆኑን ገልጿል።
የእርዳታ ሠራተኞችን፣ ዲፕሎማቶችን እና ሌሎች ባለሙያዎችን በማነጋገርም መረጃ ማሰባሰቡን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት "በመቶ ሺህዎች" የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከእነዚህ አካባቢዎች "በግዳጅ" መፈናቀላቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ የትግራይ ተወላጆች አሁንም ድረስ "በባለሥልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች" ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ከስሷል።
ኮሎኔል ደመቀ በበኩላቸው "እኛ እንደእርሱ አድርገን አይደለም የያዝናቸው። እንደማንኛውም ሰው መታወቂያም፣ ፋይዳም ያውጡ ብለን ፈቅደናል። ከዚህ ውጪ እኛ ፋይዳ አልተሰጠንም ብሎ ወደ እኛ የመጣ አቤቱታም የለም" ብለዋል።
ኮሎኔሉ ሪፖርቱ ላይ የቀረበውን መረጃ "ህወሓት የሰጣቸው ሪፖርት እና የአካባቢውን ስም ለማጥፋት፣ በዓለም አቀፍ ገጽታውን ለማበላሸት ፈልገው የሚሰሩት ካልሆነ ይህ እውነት ላይ የተመሰረተ ነው አልልም" ሲሉ በምላሹ ተችተዋል።
በሂውማን ራይትስ ዎች "የአንድ ወገን ደጋፊ" በሚመስል ሪፖርት "ማዘናቸውንም" ገልጸዋል።
ሪፖርቱ ላይ የትግራይ ተወላጆች በዘፈቀደ እየታሰሩ መሆኑን "እንቅስቃሴያቸውን፣ የሥራ ዕድላቸውን እንዲሁም አገልግሎቶችን የማግኘት መብታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚገድብ አድሎአዊ ሥርዓት" እየተዘረጋ መሆኑ ተጠቅሷል።
በአካባቢዎቹ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች "ከከተማቸው ለቅቀው ለመሄድ" ከዞን አስተዳደሩ "ጊዜያዊ ፈቃድ" ማግኘት እንዳለባቸው ባደረገው ክትትል እንደደረሰበትም ተቋሙ ገልጿል።
ቢቢሲ የትግራይ ክልል ተወላጆች ላይ ይደርሳል ስለተባለው አድሏዊ አሰራር የጠየቃቸው 'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን' ምክትል አስተዳዳሪ፣ "የትግራይ ሰዎች በመሆናቸው ያገለልናቸው ነገር የለም" ሲሉ አስተባብለዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች "እንደማንኛውም ሰው" አገልግሎቶችን እየተጠቀሙ መሆኑንም ዘርዝረዋል።
ሪፖርቱ በአካባቢው አሁን ያለውን ሁኔታ አያንጸባርቅም ያሉት አስተዳዳሪው፣ ሂውማን ራይትስ ዎች በጉዳዩ ላይ እርሳቸውንም ሆነ አስተዳደራቸውን አለማነጋገሩን ጠቅሰዋል። የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ በበኩሉ በክትትሉ የደረሰባቸውን ግኝቶች "ለኢትዮጵያ መንግሥት" አቅርቦ ምላሽ አለማግኘቱን በሪፖርቱ አስፍሯል።
ሂውማን ራይትስ ዎች አነጋገርኳቸው ያላቸው ነዋሪዎች "ትክክለኛ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት" ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ የትግራይ ተወላጆች በመንግሥት ተቋማት እንደ ማንኛውም ነዋሪ አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ፣ በአካባቢው በሚኖሩበት ወቅትም "እንደማንኛውም ነዋሪ በሰላም እንዲንቀሳቀሱ እያደረግን ነው" ብለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰኔ 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ "ማሰቃየቶች"፣ "እስራት"፣ እና "የመንቀሳቀስ ገደብ"ን ጨምሮ "ማንነትን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎች" እንዲፈጸሙ አዝዘዋል ወይም መርተዋል በማለት በስም ጠቅሷቸዋል።
ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአካባቢው የዘር ማጽዳት እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደተከናወነ በገለጸበት የሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ሪፖርት ላይም በስም ተጠቅሰዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ረቡዕ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ደግሞ የኢትዮጵያ አጋር የሆኑ አካላት "እንደ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ" ያሉ አመራሮችን "ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ" እንዲጥሉ ጠይቋል።
ኮሎኔሉ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ " (ስቀው). . .እኔ እነዚህን ከትግራይ ሰዎች ውጪ ናቸው አልልም፤ እነዚህ ህወሓት ትናንትና በየቦታው ያስቀመጣቸው በስመ ሂውማን ራይትስ ዎች ተቋሙን ተጠቅመው የሚያራምዱት የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስተግበር ካልሆነ እኔን የሚመለከት ነው ብዬ አላስብም" ብለዋል።
አስተዳደሩ "ገለልተኛ" የሆነ አካል በአካባቢው ተፈጽሟል የሚላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አጣራለሁ የሚል ከሆነ ፈቃደኛ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ገለልተኛ" የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች "የትግራይ ሰዎች ላይ የደረሰውን ብቻ ሳይሆን የወልቃይት ሰዎች ላይም የደረሰውን የሚያጣራ ከሆነ" አስተዳደራቸው በሩ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከአካባቢው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች አስተዳደሩ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ስር ከሆነ በኋላ ምን ያህል ተመልሰዋል ተብለው የተጠየቁት ኮሎኔል ደመቀ "ከአስር ሺህ በላይ እዚህ አለ። በራሱም አልሄድም ብሎም የቀረ አለ። ተደናግጦም ወጥቶ የተመለሰም አለ። ኢትዮጵያዊ ነኝ እስካለ ድረስ የመኖር መብቱ የተጠበቀ ነው" ብለዋል።
ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለሁለት ዓመት ከተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት በትግራይ ክልል ይተዳደር የነበረ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ በአማራ ክልል ስር በተመሰረተ የዞን መዋቅር በመተዳደር ላይ ይገኛል፡፡
የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተፈናቀሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ላለፉት አምስት ዓመታት ወደ መኖሪያቸው አልተመለሱም።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም