የህወሓትን ውሳኔ ተከትሎ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, SM

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጦርነቱ በፊት በትግራይ በተካሄደው ምርጫ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ መወሰኑን ተከትሎ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ አማርኛ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች "ድብልቅልቅ ያለ ስሜት" እንደተሰማቸው ተናገሩ።

የህወሓትን ውሳኔ የሚደግፉ ነዋሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት አንድ ስሜ አይገለጽ ያሉ ግለሰብ "በርካታ ሰዎች ደግሞ ይህ ውሳኔ ምንም ይዞ ይመጣል" በሚል "ግራ መጋባት እና ስጋት ውስጥ" መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዋሪዎች ይህንን ውሳኔ ተከትሎ "ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን" ወይስ "የአገልግሎት መቋረጥ ይፈጠራል" በሚል ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

"ዳግም ችግር ውስጥ" እንገባለን የሚል ፍርሃት እንዳደረባቸው የተናገሩት እኚህ ነዋሪ የፓርቲው ውሳኔ በጎ ነገር ያመጣል የሚል አስተሳሰብ አለመኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

አንዳንድ ሰዎች ውሳኔው "ግብታዊ" ነው የሚል አስተያየት አላቸው የሚሉት ነዋሪው ይህንን የህወሓት መግለጫ ተከትሎ "ጦርነት ነው የሚቀጥለው ወይስ ድርድር" የሚለው ስጋት እንደተፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በትግራይ የሚኖሩ ሰዎች የሚያስቡት "የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ነው" ያሉት ነዋሪው የፓርቲው ውሳኔው "መልካም ነገር ይዞ ይመጣል" የሚል ሃሳብ በአብዛኛው ሰው ላይ አለመኖሩን ይናገራሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እኚህ የመቀለ ከተማ ነዋሪ "በርካታ ሰው ከተማዋን ለቅቆ እየወጣ ነው" በማለት እስከ ቅዳሜ ድረስ ያለው የአውሮፕላን በረራ ሙሉ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ከመጋቢት 30/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሥልጣን ዘመናቸው ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተራዝሞላቸዋል።

ይህንን ተከትሎ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት የጄነራል ታደሰ የሥልጣን መራዘምን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ". . . የሁለትዮሽ የፖለቲካ ውይይት ሳይደረግ እና የህወሓት እውቅና እና ተሳትፎ ሳይኖር የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የሰጠው ውሳኔ" መሆኑን በመግለፅ ተቃውሟል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው በክልሉ መሪነት እንዳይቀጥሉ ከህወሓት በኩል ጫና ተደርጎባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ለፌደራል መንግሥቱ የአፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ እና የሥልጣን ጊዜያቸው ከተራዘመ በኋላ ህወሓት "ሥልጣን እንዳትቀበል" ብሏቸው እንደነበር ገልጸዋል።

የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም. ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ የክልሉ አስፈጻሚ አካል "አቃፊ" ሆኖ እንዲቋቋም መወሠኑን ገልጿል።

የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜን ያለ ህወሓት ተሳትፎ ማራዘሙን የተቃወመው ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ድርጊቱ የግጭት ማቆም ስምምነቱን "የጣሰ" እና "የተናጠል ውሳኔ" መሆኑን ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ህወሓት ያወጣውን መግለጫ "ጊዜውን የጠበቀ ነው" ያሉት ሌላ ነዋሪ ደግሞ፣ ይህ የፓርቲው እርምጃ "ማኅበረሰቡን ይጠቅማል" ሲሉ ውሳኔውን ደግፈዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደር "በጊዜያዊነት" ዓመታትን እየፈጀ ከሚቆይ የፓርቲው ውሳኔ ለሕዝቡ "ፍትህ እና ነጻነት" የሚያስገኝበት መንገድ እንደሚፈጥርም ጨምረው አስረድተዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተወሰነ ነው የሚሉት እኚህ ነዋሪ ለክልሉ መፍትሄ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ይናገራሉ።

ወደ ትግራይ ክልል መላክ የነበረበት የድጎማ በጀት መቋረጡን የጠቀሰው ህወሓት፤ "ባጠቃላይ በትግራይ ላይ ዳግም እገዳ እና ከበባ በማድረግ፣ የጦር መሳሪያ እና ሜካናይዝድ አቅሙን ወደ ትግራይ በማስጠጋት ዳግም ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ ነው" ሲል የፌደራል መንግሥቱን ወንጅሏል።

በእነዚህ እርምጃዎች የተነሳም የፌደራል መንግሥቱ "ለትግራይ ህዝብ ህልውና እና ደኅንነት አደገኛ የሆነ ሁኔታ" እንደተፈጠረ ገልጿል።

የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት በዚህ ውሳኔው "የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚያፈርስ ተግባራዊ እርምጃ ወስዷል" ብለዋል።

ጌታቸው፤ "የፕሪቶሪያ ስምምነትን እና ከጦርነት በኋላ የተረዘጋውን ደካማ ስርዓት የሚያፈርስ ማንኛውም የተናጠል ውሳኔ በክልላዊ ተዋናዮች መካከል ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከፌደራል መንግሥት ጋር እንደ አዲስ ግጭት እንዲቀሰቀስ የማድረግ ዕድል አለው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ለዓመታት ከሚኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩ ነዋሪ ደግሞ የሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት ሲራዘም "ድንጋጤ" ፈጥሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ።

ግለሰቡ በውሳኔው የተደናገጡት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን የተራዘመው "በሕጉ መሠረት አይደለም" በሚል መሆኑን ገልጸው፣ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አሁን ይህንን ውሳኔ ሲወስን ደግሞ በክልሉ የተፈጠሩ ውጥረቶች "በሰላም በመደራደር ቢፈቱ ጥሩ ይሆናል" የሚል ስሜት አንደተሰማቸው ገልጸዋል።

አክለውም "ኅብረተሰቡ በአአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስላለ በማለት "ውሳኔውን እቀበለዋለሁ" ብለዋል።

"በውሳኔው ላይ በሰላማዊ መንገድ እና በድርድር" የሚሰራ ከሆነ ሕዝቡን ካለበት ችግር ያስወጣዋል ብለው እንደሚያምኑ ጨምረው ተናግረዋል።

ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት ላላቸው አካላት "አዲስ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይዞ ይመጣል" የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ውሳኔው ከሕዝብ ጋር በመመካከር የተደረገ አይደለም የሚሉት ሌላ ነዋሪ ደግሞ የፓርቲውን አቋም "አልተቀበልኩትም" ብለዋል።

"የሰላም ሁኔታው የሚረጋገጠው ሕዝብን ማዕከል አድርገው ሲነጋገሩ ነው" የሚሉት እኚህ ነዋሪ ስለ ክልሉ አጠቃላይ ሁኔታ ከጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከመነጋገር ይልቅ በግላቸው የወሰኑትን ውሳኔ" በመሆኑ እንደማይቀበሉት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ" ያሉት እኚህ ነዋሪ ይህ ደግሞ "ጦሱ ለኅብረተሰቡ ሊተርፍ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የህወሓት ውሳኔ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ምን ይሆናል የሚለውን መጠየቅ አለበት የሚሉት እኚህ ነዋሪ "በጦርነት ምክንያት ደቅቀናል፤ ኢኮኖሚያችን ወደ ኋላ ቀርቷል። የተራበ፣ ወደ መኖሪያ ቀዬው ያልተመለሰ ተፈናቃይ አለ" በማለት ለእነዚህ ወገኖች እንዴት መፍትሄ ይመጣል የሚለው ዋና ጥያቄ መሆኑን ያስረዳሉ።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቀጥል የተሻለ ነው የሚሆነው የሚሉት ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ "ይህ ተመልሶ መከራ የሚያስገባ እና መከራ የሚጠራ ነው የሚመስለው" ይላሉ።

በዚህ መግለጫ "ግለሰቦችን ማዳን እንጂ ሕዝቡን እያዩት ያለ አይመስለኝም" የሚለት ነዋሪው በዋናነት ከተጠያቂነት ለማምለጥ የተወሰነ ይመስለኛል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ከክልሉ ወጣቶች እየወጡ፣ ለሌላ ችግር እና እንግልት እየተጋለጡ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ የሚታያቸው "መልካም ነገር አለመሆኑን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴው "ወደ ሥራ እንዲመለስ" ውሳኔ ያስተላለፈለት ምክር ቤት የተቋቋመው የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ መራዘሙን የተቃወመው ትግራይ ክልል በ2012 ዓ.ም. በተናጠል ባካሄደው ምርጫ ነው።

በዚህ ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 190 ወንበሮች ውስጥ ውስጥ 152 ያህሉን ህወሓት ማሸነፉ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥት ከብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ውጪ የተካሄደውን ይህንን ምርጫ ውድቅ አድርጎታል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጷግሜን 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸና እና ተፈጻሚነት የሌለው" እንደሆነ ወስኗል።

ምርጫው ከሁለት ወራት በኋላ ለተነሳው የትግራይ ጦርነት ምክንያት ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ ተደርጎ የሚቆጠር ነው።