ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፖላንድ ለአፍሪካውያን በክፍያ ቪዛ መሰጠቱ መንግሥት ላይ ጥያቄ አስነሳ
የፖላንድ የላይኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቶማዝ ግሮዲዚ በአገሪቱ ገንዘብ እየተቀበሉ ቪዛ የመስጠት አካሄድ መባባሱን ገለጹ።
መንግሥት ስለ ጉዳዩ ምን መረጃ እንዳለው ይፋ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ነገሩ የአገሪቱን ስም እያጠለሸ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግሥት የተወሰነ መረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ግን ስደተኞች እስከ 5,000 ዶላር እየከፈሉ የሥራ ቪዛ የማግኘት ሂደቱን ያፋጥናሉ።
እስካሁን ሰባት ሰዎች ላይ ክስ ቢመሠረትም አንዳቸውም የመንግሥት ባለሥልጣን አይደሉም።
የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒዮር ዋውዚክ ባለፈው ሳምንት ክሶችን ተከትሎ ከሥራ ተነስተዋል።
የፖላንድ ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሥሪያ ቤቱ ላይ ምርመራ ካደረገ በኋላ ነው የተባረሩት።
የሕግ ክፍሉ ዳይሬክተርም ተባረዋል።
እአአ ከ2011 ጀምሮ ለቪዛ ያመለከቱ ሰዎች ዝርዝር ላይ ኦዲት እንደሚደረግ ተገልጿል።
ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል እንዳሉት እስከ 250,000 ቪዛዎች ሕግ ሳይከተሉ ለእስያ እና አፍሪካ አመልካቾች ተሰጥተዋል።
መንግሥት ግን ቁጥሩ በጥቂት መቶዎች ብቻ የሚቆጠር ነው ብሏል።
የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ዶናልድ ተስክ “ከአፍሪካ ፖላንድ መምጣት የፈለገ ሁላ ከኤምባሲያችን ቪዛ ገዝቶ አገራችን በቀላሉ ይገባል” ብለዋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ይህ ንግግር ቀውስ እንደሚያስከትል ገልጸው ችግሩ የተባለውን ያህል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
“አገራችን ኃላፊነት የሚሰማት ዴሞክራሲያዊ አገር ሆና ሳለ የነጻውን ዓለም ደኅንነት አደጋ ውስጥ የምትከት ሆና እንድትታይ የሚያደርግ አካሄድ ስለሆነ በጥልቀት ሊብራራ ይገባል። ይህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ቅሌት ነው። ሙስና በመንግሥታችን ተንሰራፍቷል” ሲሉ የላይኛው ምክር ቤት አባል አሳስበዋል።
የፍትሕ ሚኒስተሩ ዚግኒው ዚዎብሮ በበኩላቸው ይህ አባባል የተጋነነ ነው ሲሉ ለብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ይህ ጉዳይ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በተያያ በቀጣዩ የፓርላማ ምርጫ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተገልጿል።