ያለበት ሳይታወቅ የቆየው የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኛ "ኢመደበኛ ማቆያ" ውስጥ እንደሚገኝ አሳታሚው ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, addis standard
ከአንድ ሳምንት በፊት "ሲቪል ልብስ በለበሱ" ሰዎች ከመስሪያ ቤቱ የተወሰደው የአዲስ ስታንዳርድ ዲጂታል መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ሚሊዮን በየነ የተያዘው "በደኅንነት ኃይሎች" መሆኑን እና አዲስ አበባ በሚገኝ "ስውር የማቆያ ቦታ" ውስጥ እንደሚገኝ አሳታሚው አስታወቀ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ከተወሰደበት ጊዜ አንስቶ በማን እንደተያዘ እና ያለበት ሳይታወቅ የቆየው ጋዜጠኛ ሚሊዮን በመንግሥት በእስር ላይ መሆኑ እንደተረጋገጠ የአዲስ ስታንዳርድ አሳታሚ የሆነው 'ጃኬን የኅትመት ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ገልጿል።
አሳታሚው ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም. ምሽት ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው አሁንም ቢሆን ጋዜጠኛው ቤተሰቡ፣ የሥራ ባልደረቦቹ፣ እና የሕግ አማካሪዎች ሊያነጋግሩት አልቻሉም።
ባለፈው ሳምንት "ለጥያቄ ትፈለጋለህ" ጋዜጠኛ ሚሊዮንን የወሰዱት "ማክስ" ያደረጉ ሰዎች እንደሆነ እና በደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ላይ "ግለሰቦቹ ድርጊቱን በታቀደና በተደራጀ መልኩ ሲፈጽሙ" መታየቱን አሳታሚው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ ነበር።
ስለ ጋዜጠኛው መወሰድ ጥያቄ የቀረበላቸው አዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በቁጥጥራቸው ስር እንዳልሆነ መግለጻቸውን የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር። ሁኔታው ቤተሰብ ላይ ጭንቀት መፍጠሩንም ገልጿል።
አሳታሚው ትናንት ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው ያለበትን ለማወቅ "ላለፈው አንድ ሳምንት ካደረግነው ያላሰለሰ ፍለጋ" መደረጉን አስታውቋል። በተደረገው ክትትልም ጋዜጠኛ ሚሊዮን የተወሰደው "በደኅንነት ኃይሎች" እንደሆነ እንዲሁም "በአዲስ አበባ በግልጽ ባልታወቀ፣ ስውር የማቆያ ቦታ እንደሚገኝ" መረጋገጡን ገልጿል።
መግለጫው፤ "ቤተሰቡ፣ የሥራ ባልደረቦቹ፣ እንዲሁም የሕግ አማካሪዎች ሊጠይቁትም ሆነ ሊያነጋግሩት አልቻሉም። ጤናውም በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ለማወቅ አልተቻለም" ብሏል። በሕጉ መሠረት በተያዘ በ48 ሰዓታት ውስጥ "ፍርድ ቤት የመቅረብ መብቱ" አለመጠበቁንም አስረድቷል።
"እንዲህ ዓይነቱን በሕግ የተከለከሉ መሠረታዊ መብቶችን የሚጥሱ ድርጊቶችን አጥብቆ" እንደሚኮንን የገለጸው አሳታሚው፤ ጋዜጠኛ ሚሊዮን "የሚገኝበት ቦታ በአስቸኳይ እንዲገለጽ" ጠይቋል። "ከቤተሰቦቹና ከሕግ ተወካዮቹ ጋር እንዲገናኝ እንዲሁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታም" ጥያቄ አቅርቧል።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄም ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሚሊዮን በየነን ማን እንደወሰደው በአፋጣኝ ማረጋገጥ፣ መለቀቁና ማረጋገጥ እና ተጠያቂዎቹንም ለፍርድ ማቅረብ" እንዳለባቸው አሳስቦ ነበር።
የማኔጂንግ ኤዲተሩ መጥፋት አዲስ ስታንዳርድ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች "አዲስ ምዕራፍ" መሆኑንም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ገልጾ ነበር።
አዲስ ስታንዳርድ ዲጂታል መጽሔት ካለፈው ዓመት አንስቶ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደውበታል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የካቲት ላይ "የአገርን እና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል" በሚል የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ ፈቃድ ሰርዟል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ደግሞ ቢሮው በፀጥታ አካላት እንደተበረበረ እና በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች መወሰዳቸውን ገልጾ ነበር። የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎቹ ሲመለሱ "በተደረገ ሙያዊ ፍተሻ የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware)" ተጭኖባቸው እንደተገኙ መገናኛ ብዙኃኑ በወቅቱ አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚህ ሳምንት ባወጣው የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ሪፖርት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ከጠቀሳቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሸርሸር ይገኝበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት "በጋዜጠኞች እና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች ላይ የዘፈቀደ እስር" እንደሚፈጽሙ ገልጿል። አምነስቲ፤ "ማንነታቸው ባልታወቀ ጭምብል በለበሱ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ፣ የት እንዳሉ ሳይታወቅ እስከ 12 ቀናት ድረስ የሚቆዩ" ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በሪፖርቱ አስፍሯል።















