ለሰዎች ባዮኒክ እጅ እና እግር እየቀጠሉ 'ኤዲት' ማድረግ ዓለምን እንዴት ይለውጣል?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአራት ዓመት በፊት አርብ ቀን ነበር። ሳራ ደ ላግሬድ ለንደን ከሚገኘው ቢሮዋ ወደ ቤቷ እየተጓዘች ሳለ አደጋ ገጠማት።
በባቡር እና በሐዲድ መካከል ወደቀች። ባቡሩ ጉዞ እየጀመረ ስለነበር ቀኝ እጇ ተጨፈለቀ። እዚያው በወደቀችበት ሌላ ባቡር መጥቶ እግሯ ላይ ወጣ።
ኮስሞቲክ እጅ ሊገጠምላት ታስቦ ነበር። ሆኖም ግን ልታንቀሳቅሰው አትችልም። ከዚያም ኤሌክትሮኒክ (ባዮኒክ) ክንድ ሊገጠምላት እንደሚችል ተነገራት።
ማድረግ የምትፈልገውን እንቅስቃሴ አእምሮዋ ውስጥ አሰላስላ ጡንቻዋን ስታንቀሳቅስ የተገጠመላት ክንድ ትዕዛዙን ይቀበላል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚዘወር ክንድ (AI-powered bionic arm) የተገጠመላት የመጀመሪያዋ ሰው ናት።
ሳራ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደተናገችው፤ እጇን በተጠቀመች ቁጥር መረጃ እየሰበሰበ በሰርቨር ላይ ያከማቻል።
"በተንቀሳቀስኩ ቁጥር ማሽኑ ይማራል። በዚህ መረጃ መሠረት ቀጣይ እንቅስቃሴዬ ምን ሊሆን እንደሚችል ይገምታል (Generative AI ይሆናል)" ስትል ታስረዳለች።
መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባት ነበር። ባዮኒክ እጇን ለረዥም ጊዜ ከተጠቀመችበት በኋላ ግን በቂ መረጃ ስላከማቸ በቀላሉ ይታዘዛት ጀመር።
"አሁን እያወራሁ ጎን ለጎን እጄ መሥራት ይችላል። ከዚህ በፊት አንድን እንቅስቃሴ ለመከወን አስቤ እስከሚፈጸምበት ወቅት ድረስ የሰከንዶች ጊዜ ክፍተት ነበር። አሁን ግን ያሰብኩትን ነገር ወዲያው መፈጸም እችላለሁ።"
ከተፈጥሯዊ እጇ በበለጠ ባዮኒክ እጇ ጠንካራ ነው። ተፈጥሯዊ እጇን እንደማይተካው ብትናገርም "የወደፊቱ ዓለም እንዴት አጓጊ እንደሆነ ማሳያ ነው" ትላለች።
ሳራ በባዮኒክ እጇ ከልጇ ጋር ትጫወታለች፣ ኪቦርድ ላይ ትጽፋለች፣ ድመቷን ትዳብሳለች። ሳራ የወደፊቱ ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያ ናት።
ከቀላል ምሳሌ እንጀምር። በሩቅ ማየት የማንችለውን በመነጽር እገዛ እንመለከታለን።
ቴክኖሎጂ እየተራቀቀ ሲሄድ ደግሞ እግራችን በተፈጥሮ ከሚችለው በላይ እንዲሮጥ ወይም እጃችን መሸከም ከሚችለው በላይ እንዲያነሳ ማድረግ የሚቻልበት ዘመን እየተቃረበ ይሆን?
በዘረ መል ምክንያት ሊገጥም የሚችል ሕመምን መርጦ ከሰውነት ማውጣት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ ነው።
እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ክሪስፐር ቴክኖሎጂ (CRISPR ወይም Clustered Regularly Interspaced Short Palindromic Repeats) ዘረ መል ላይ አርትኦት በማድረግ ይታወቃል።
እንደ ሳራ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ እጅ ወይም እግር መቀጠል፣ የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ አቅም በቴክኖሎጂ ማሻሻል እንዲሁም በተፈጥሮ ያሉ የዘረ መል ግድፈቶችን ማሻሻል ዓለምን እንዴት ሊለውጥ ይችላል?
ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጠን የማይንድ ፕሌክስ ሥራ አስኪያጅ እና የአይኮግ ላብስ መሥራች ኅሩይ ፀጋዬን ጠይቀናል።
የፎቶው ባለመብት, Leigh Day
ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልኅቀት የሚያስረዳው 20% የሚደርሱ የአሜሪካ ወላጆች የልጆቻቸውን የትውስታ አቅም ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ነው።
የላቀ አንጎል (Super Brain) ያላቸው ብቻ ሳይሆን ሰውነታቸው ከተፈጥሮ ገደቡ ማለፍ የሚችል ሰዎች የምናይበት ወቅት እየተቃረበ ይሆን?
ቀደም ባሉት ዓመታት የሳይንሱ ዓለም ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረው በዘረ መል የሚተላለፉ በሽታዎችን ለማከም በሕመም የተያዘን ሕዋስ ለይቶ በማውጣት በጤናማ መተካት (Gene Editing) እንደነበር ባለሙያው ያስታውሳል። በዘር የሚተላለፉ በሽታዎችን ለማቆም ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው።
በዘር የሚተላለፍ የደም መርጋት በሽታን የሚያመጣውን ዘረ መል በማውጣት ማዳን መቻሉ ትልቅ ማሳያ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ቁመት ለመጨመር የሚረዳ ሆርሞን (Growth Hormone) የመጠቀም ሳይንስን ኅሩይ ለንጽጽር ያቀርባል።
የሰው ልጅ ተጨንቆ እና ተጠቦ በራሱ ላይ አንድ ዘለላ ፀጉር ይጨምራል? ለሚለው ጥያቄ መልሱ 'አይጨምርም' ነበር። "አሁን ግን በሳይንስ መጨመር ተችሏል" ይላል ባለሙያው።
የዘረ መል ልወጣ የተደረገበት አትክልት እና ፍራፍሬ (Genetically Modified Organism) አወዛጋቢ ቢሆንም፤ ባለፉት ዓመታት ከመደበኛ አትክልት እና ፍራፍሬ በማይተናነስ መጠን መቅረቡን ቀጥሏል።
". . .ሰላጣ ከሦስት ቀን እስከ 10 ቀን ባለው ይደርሳል። ሰላጣን ለወራት አባብሎ፣ ተንከባክቦ ማሳደግ ቀረ ማለት ነው። አንድ ዶሮ በ20 ቀን ውስጥ፣ በሬም በ60 ቀን ለእርድ እየደረሱ ነው" ይላል።
አንዳንድ የቴክኖሎጂ መራቀቅ ውጤቶች ሲታዩ እምብዛም ባይጎረብጡም፤ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያስገድዱም አሉ።
ዶሊ እአአ ከ1996 እስከ 2003 ድረስ የኖረች በግ ናት። በጓን ከሌሎች በጎች የሚለያት በተፈጥሮ የተወለደች አለመሆኗ ነው።
ከሌላ በግ በተወሰደ ሕዋስ ነው የተሠራችው። ይህ ሒደት (Cloning) ብዙ ጥያቄ ያጭራል። ዶሊ ክሎን እንደተደረገችው በሰዎች አምሳያ ሰው ሊሠራ ይሆን?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደረጉ ሙከራዎችን ለመገደብ የሚሞክሩ አገራት ቢኖሩም፤ ምርምሮቹ በሌሎች አገራት እንደሚቀጥሉ ባለሙያው ያስረዳል።
በምሥጢር የቴክኖሎጂ ሙከራዎችን ማድረግ የሚቻልባቸው አገራት ምን እንደሚሠሩ ለማወቅ ደግሞ ቀላል አይሆንም።
ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው በቴክኖሎጂ ታግዘው የሰውነት አካል እንዲያገኙ የማድረግ ቴክኖሎጂ ተፈጥሯዊ ገደቦችን ለማለፍ የሚውልበት ዕድልም እንዳለ ይታመናል።
ነገሩን በቀላሉ ለመረዳት በድጋሚ መነጽርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ከሩቅ ማየት የማይችሉ ሰዎች በመነጽር ታግዘው ዕይታቸው ይስተካከላል። የመነጽር ሚና ከዚህም በላይ ሆኖ እንደ ኮምፒውተር ስክሪን የሆነ መነጽር ተሠርቶ ገበያ ላይ ውሏል።
መነጽር፤ ዐይን ላይ በሚደረግ ኮንታክት ሌንስ እንደተለወጠው ሁላ፤ ዐይን በተፈጥሮ ያለውን ገደብ እንዲያልፍ 'ኤዲት' ይደረግ የሚል ጥያቄ መነሳቱ እንደማይቀር ኅሩይ ይናገራል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የሰው ልጅ ፍላጎት አያልቅም። ሁሌም አዲስ ፍላጎት ሲኖረው ለዕይታ የተሠራው መነጽር አገልግሎቱ እያደረገ ይሄዳል ማለት ነው" ሲል ያስረዳል።
ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በብዛት ከሚያፈሱበት ዘርፍ አንዱ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም።
የሰውነት ክፍሎችን 'ማሻሻል' ከተቻለ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ደግሞ ዕድሜንስ ማራዘም ይቻላል? የሚለው ይሆናል።
ሰዎች በሕመም እንዳይሰቃዩ የዘረ መል ምህንድስና ማድረግ ከፍ ሲል ተፈጥሯዊ መዋቅርን ወደመለወጥ ወይም 'ማስተካከል' መሻገሩ አይቀርም በሚል አገራት ከፍተኛ ቁጥጥር ከሚያደርጉባቸው ዘርፎች አንዱ ነው።
የሰው ልጆች ሰውነት እና አእምሮ ከተፈጥሯዊ አቅሙ እንዲሻገር በማድረግ የላቁ ሰዎች (Super Humans) መሥራት ልብ ወለዳዊ ሐሳብ መሆኑ ያከትም ይሆናል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የዘረ መል ምህንድስና እና ናኖቴክኖሎጂን በማዋሀድ የላቀ አካላዊ እና አእምሯዊ ብቃት ያላቸው ሰዎችን መገንባትን የሚያቀነቅኑ ባለሙያዎች (Transhumanists) ገናና እየሆኑ መጥተዋል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ቀደም የሚታሰቡ የማይስሉ ነገሮች አሁን ላይ እየቀረቡ መምጣታቸውን ኅሩይ ይገልጻል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ከሰብአዊነት እና ሥነ ምግባር አንጻር ይነሳ የነበረው ጥያቄ ቀስ በቀስ እየረገበ ይመስላል።
"የሞራል ግንቦች እየተናዱ ነው። ከምጣኔ ሃብት እድገት ጋር በተያያዘም ማለቂያ የሌለው የሰው ልጅ ፍላጎት ነገሮችን ወደፊት እየገፋ ነው" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አካላት ያሉት (Cyborg) ልብ ወለዳዊ ገጸ ባህሪ መሆኑ የሚቀርበት ዘመን ላይ መድረስ እንደቀደመው ዘመን አስደንጋጭ ላይሆን ይችላል።
በቴክኖሎጂ ታግዞ የሰው ልጆችን 'ማሻሻል' የሚለውን እንቅስቃሴ ከሚያቀነቅኑ ተቋማት 'ሂውማኒቲ ፕላስ' ይጠቀሳል።
የሰዎችን ዕድሜ ከማራዘም አልፎ፤ ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው ለረዥም ጊዜ ማቀዝቀዣ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ እና ለወደፊት ዓለም የተሻለች ስትሆን 'ከሞት የመቀስቀስ' ሐሳብን እንደ አማራጭ ያቀርባል።
የሰዎች ሕዋሳት ከሞቱ በኋላ እንደ አዲስ 'ማስነሳት' ሳይንስ አሁን ላይ ዕውቅና የሚሰጠው ባይሆንም፤ ለወደፊት የሚመጣው ቴክኖሎጂ ይሄንን ሊያሳካ ይችላል በሚል ተስፋ የሚደረግ ንቅናቄ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ አቅም 'የላቀ' የማድረግ ሳይንስ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ባለሙያዎች ዋነኛ መከራከሪያቸው የፍትሐዊነት እና እኩልነት ጉዳይ ነው።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ለናጠጡ ሃብታሞች ተደራሽ ሲሆኑ፤ የወደፊቷ ዓለም አሁን ካለውም በላይ መድልዎ የሚንሰራፋባት ልትሆን እንደምትችል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
ኅሩይም ይሄንን ሐሳብ ይጋራል። "ፈጣኑ ሯጭ ገንዘብ የሚገዛው ከሆነ ወይም በሌላም ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚችለው ሃብታም ከሆነ ድሃው መወዳደሪያ አይኖረውም" ይላል።
ሰብአዊነት እና እኩልነት ባልሰፈነበት እንዲሁም የመደብ ልዩነት በሰፋበት ዓለም ቴክኖሎጂ ሲቀድም "የፍትሕ መዛባትን" ያስፋፋል ብሎ ያምናል።
ቴክኖሎጂ እየሄደበት ያለውን ፍጥነት ስንመለከት፤ ከዚህ ቀደም ከሚወስድበት ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት የበለጠ እያደረገ ሲመጣ የተፈጥሮ ገደብን የሚጥሱ ሰዎች ማየታችን አይቀርም።
ቴክኖሎጂ የሚፈጥረው የመደብ ልዩነት የምጣኔ ሃብት ልዩነትን ተከትሎ መድልዎን የሚያሰርጽ ይሆናል በሚልም ባለሙያዎች ፍርሃታውን መግለጻቸውን ቀጥለዋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም